በኩዌት የቅድስት መንበር ተወካይ 'የተራዘመ ጦርነት ቀድሞውኑ በችግር ውስጥ የሚገኘውን ክልል አይጠቅምም' ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከየካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ በባህረ ሰላጤ ውስጥ ሁሉም የውጭ ዜጎች የሆኑ አምስት ሰዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ከእነዚህም አንዱ በኩዌት፣ ሶስቱ በኤምሬትስ እና አንደኛው ደግሞ በባህሬን መሆኑ ተመላክቷል።
የካቲት 23 ሰኞ ዕለት በዱባይ፣ አቡ ዳቢ፣ ዶሃ እና ማናማ አዳዲስ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን፥ ኩዌት በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አከባቢ ከባድ ጭስ ሲታይ እንደነበረም ተገልጿል።
ከኢራን የሚሰነዘረው ጥቃት የጸጥታ ስጋት ተብለው የሚታሰቡትን እነዚህን የአረብ ባሕረ ገብ ግዛቶች እያናወጠ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በኩዌት፣ ባህሬን እና ኳታር የቅድስት መንበር ሐዋሪያዊ ተወካይ ሊቀ ጳጳስ ዩጂን ኑጀንት ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአከባቢው ስላለው ሁኔታ እና የቤተ ክርስቲያንን የሰላም ፍላጎት ገልፀዋል።
እርሳቸው በሚገኙበት በኩዌት ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል የጠየቁት ሊቀ ጳጳሱ ሁኔታው አስገራሚ እና ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ነው መሆኑን ጠቁመው፥ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ በተሰሙት ተከታታይ ፍንዳታዎች እና የማያቋርጥ ሳይረን ተከትሎ በተከሰቱት ፍንዳታዎች ምክንያት ሌሊት ሌሊት የተሟላ እንቅልፍ እንደማይተኙ የገለጹ ሲሆን፥ የካቲት 23 ጠዋት በኩዌት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት እንደደረሰበት ለማወቅ እንደቻሉ እና እንደ እድል ሆኖ ምንም ዓይነት ሞት ባይኖርም በኤምባሲው ውስጥ የእሳት ቃጠሎን ጨምሮ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል።
የካቲት 24 ሁለት የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች “አሊ አል ሳሌም” ከሚባለው አየር ማረፊያ አጠገብ በጥይት ተመተው እንደነበር መስማታቸውን ጠቁመው፥ ይሄንን ስፍራ በደንብ እንደሚያውቁት ምክንያቱም በየጊዜው ወደዚያ ሄደው መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያሳርጉ እና ከጎኑ የጣሊያን ጦር ሰፈር መኖሩን አስታውሰዋል።
ሊቀ ጳጳሱ በእርግጥ በተወሰነ ደረጃ አስፈሪ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ለመረጋጋት እየሞከሩ እንደሆነ ገልጸው፥ በገዳሙ አካባቢ ምንም ጉዳት እንዳልተመለከቱ፣ በሻዓብ ወረዳ ውስጥ ጸጥታ በሰፈነበት የከተማው ክፍል ያለው ብቸኛ ኤምባሲ የቅድስት መንበር እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የዲፕሎማቲክ አውራጃ በሆነውና የኢራን ኤምባሲም ጭምር የሚገኝበት አከባቢ በጣም ቅርብ እንደሆነ የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ወታደራዊ ሰፈሮች እና የአየር ማረፊያዎች ዋና ዒላማዎች መሆናቸውን እና የኩዌት አየር ማረፊያ ተርሚናል 1 በመጀመሪያው ቀን በድሮን መመታቱን አስታውሰዋል።
ባህሬን እና ኩዌት በጦርነቱ እየተጎዱ መሆናቸው እና እነዚህ በሃይማኖቶች መካከል ውይይትን እና ሰላማዊ አብሮ መኖርን በሚያበረታቱ ክልሎች ውስጥ እንደዚህ አይነት ነገር መፈጠሩን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ሊቀ ጳጳስ ዩጂን፥ እየሆነ ባለው ነገር ሁሉም ሰው መደንገጡን ጠቅሰው፥ እየተካሄደ ያለው ውይይትና ድርድር ፍሬያማ ይሆናል ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበር፣ ነገር ግን የካቲት 21 ጦርነቱ ሲነሳ በእውነት መገረማቸውን ተናግረዋል።
እንደ እድል ሆኖ ባለፈው እሁድ በተካሄደው በመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ክልል ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን፣ እንዲሁም ለውይይት እና ድርድር ያቀረቡት ጥሪ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቶ እንደነበር እና ይሄንን ጥሪ በሰፊው አጋርተው እንደነበር ገልጸው፥ የሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር የሆኑት ብፁዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ በዚህ ወቅት ህዝቡን ለጸሎትና ለኅብረት በመጋበዝ ያስተላለፉት መልዕክትም በተመሳሳይ ሁኔታ ተቀባይነት አግኝቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
በየደቂቃው ጥቃት እና የበቀል እርምጃው እየተጠናከረ ባለበት በዚህ ወቅት ምን ሊከሰት እንደሚችል የተጠየቁት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይሄንን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችሉ ሁሉንም ዓይነት አማራጮች እንዲጠቀሙ ለማበረታታት ከባለሥልጣናት እና አምባሳደሮች ጋር እንደሚገናኙ ጠቁመው፥ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ጦርነት አንዴ ከተጀመረ መቼ እንደሚያበቃ ማንም ሰው አያውቅም ብለዋል።
“ሁሉም ነገር በፍጥነት እየተካሄደ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ነገር ግን አሁንም እያንዳንዱን መንገድ መሞከር እንደሚገባ እና ረጅም ጦርነት ማንንም እንደማይጠቅም፣ በተለይም በርካታ ግጭቶች ውስጥ በነበረ ክልል ውስጥ አደገኛ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሥር የሰደደ የጥላቻ ሁኔታ ሲፈጠር ዲፕሎማሲውን እንዴት ማደስ እንደሚቻል ያብራሩት ሊቀ ጳጳስ ዩጂን፥ የጦር መሳሪያዎች ጩኸት እያሰሙ ባለበት በአሁኑ ወቅት የዲፕሎማሲ እና የድርድር ባህላዊ መንገዶችን መሞከር እንደሚገባ ገልጸው፥ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መግለጫ በኢራን ውስጥ ከአዲሱ አገዛዝ ጋር ውይይት እንደሚደረግ በማመልከቱ ውይይት ሊጀመር እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
“ከሁሉም ወገኖች ጋር ምክንያታዊ ውይይት ለማድረግ ተስፋ እናደርጋለን” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ የኢራን ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ ስለሆነ ለጊዜው ይህ በጣም ከባድ እንደሆነ አመላክተው፥ በሀገሪቱ ውስጥ ብዙ አንጃዎች በመኖራቸው የጂኦፖለቲካዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ለመረዳት አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸው፥ በየደረጃው ውይይት መሞከር እንደሚገባ እና ይሄንን ጦርነት ለማቆም ብቸኛው መንገድ ዲፕሎማሲ እንደሆነ አስምረውበታል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. በ 2022 ባህሬንን በጎበኙበት ወቅት ጦርነትን ሲገልጹ “በሰው ልጅ የአትክልት ስፍራ ውስጥ፣ ሙሉውን ከመጠበቅ ይልቅ በሚሳኤል፣ በቦምብ እና በእሳት እንጫወታለን፥ ይህም አሳዛኝ የህፃንነት ገጽታ ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ እነዚህ ቃላት አሁን ባለንበት ሁኔታ ላይ የሚያስተጋባው መልዕክት ካለ የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ዩጂን፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቃላት ትንቢታዊ እንደሚመስሉ ገልጸው፥ እነዚህ ቃላት ለሁሉም ሰው የሚናገሩ ኃይለኛ ቃላት መሆናቸውን እና ለዘመናት የሰው ልጅ በርካታ ግጭቶች ውስጥ መግባቱን አስታውሰው፥ ነገር ግን በመጨረሻ ወንድማማችነትን እና የጋራ የሆነ ነገርን መፈለግ እንደሚገባ በአጽንዖት አሳስበዋል።
ቤተክርስቲያኒቱ በዚህ ክልል ውስጥ ለዘመናት እንደነበረች ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ሁሉም አገር ሰላም እና ስምምነትን መሻቱ እንደማይቀር እና ለዚህም ዘወትር ጸሎት እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ጦርነት የተጀመረበትን አራተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እዚሁ ኩዌት በሚገኘው ካቴድራል ሥርዓተ ቅዳሴ መደረጉን እና ከአራት ቀናት በኋላ ደግሞ ጦርነት መነሳቱን አስታውሰዋል።
አሁን ባለንበት የዐቢይ ጾም እና የረመዳን ወቅት ጸሎት ብቻ አስፈላጊ እንደሆነ ያመላከቱት ብፁዕነታቸው፥ ክርስቲያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች በጾምና በጸሎት ጊዜ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውሰው፥ “እግዚአብሄር የሰላም ስጦታ እንዲሰጠን እንማጸናለን” ብለዋል።
ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እና በጦርነቱ ምክንያት ለተደናገጡ ምዕመናን ያላቸውን መልዕክት ምን እንደሆነ የተጠየቁት ሊቀ ጳጳሱ፥ ብፁዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ እና እሳቸው ተጠሪ በሆኑባቸው በሦስቱ ሃገራት፥ ማለትም ኩዌት፣ ባህሬን እና ኳታር ውስጥ ከሚገኙ የሰበካ ካህናት ጋር በየቀኑ እንደሚገናኙ ገልጸው፥ እነሱን ለማበረታታት እና ለመደገፍ ሙከራ እንደሚያደርጉ እና አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አሁንም ድረስ ክፍት ቢሆኑም የተወሰኑት ግን ዝግ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሃዋሪያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ዘወትር ጠዋት 1፡30 ላይ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያከብሩ፣ ከሰዓት በኋላ 11፡00 ሰዓት ላይ ደግሞ ስለ ሰላም እንደሚጸልዩ፣ በዋትስአፕ የጸሎት ቡድኖችም ጭምር እንዳሉ ያስታወሱ ሲሆን፥ ሁሉም ሰው እንዲረጋጋ እንደሚያበረታቱ ገልጸው፥ “ሁላችንም ይሄንን ስጦታ እንድናገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን አማላጅነት እንለምናለን” ብለዋል።
ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መሰጠት በእንደዚህ ዓይነት አውድ ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ዩጂን፥ በአከባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ‘የአረቢያ እመቤታችን’ ተብላ የምትታወቀው ቅድስት ድንግል ማሪያም መሠረታዊ ነገር መሆኗን ጠቁመው፥ ምዕመናን ለእሷ ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው፣ ሙስሊሞችም ጭምር በቁርኣን ውስጥ ብዙ ጊዜ ለተጠቀሰችው ማርያም ታላቅ ፍቅር እንዳላቸው አስታውሰው፥ በዚህ አስደናቂ ጊዜ የሰላም ንግሥት ለሆነችው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም አበክረው እንደሚጸልዩ ገልጸው፥ “ጦርነቱ የሚቆመው ለልጇ በምታደርግልን አማላጅነት ነው” በማለት አጠቃለዋል።