ፈልግ

በላቲን አሜሪካ የማዕድን ቁፋሮ ማገድን በማስመልከት በቫቲካን የተሰጠ መግለጫ  በላቲን አሜሪካ የማዕድን ቁፋሮ ማገድን በማስመልከት በቫቲካን የተሰጠ መግለጫ  

በላቲን አሜሪካ የአገሬው ተወላጆች እና ቤተ ክርስቲያን የማዕድን ቁፋሮን ማገድ መጀመራቸው ተገለጸ

በላቲን አሜሪካ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች እና የአገሬው ተወላጆች መብት ተሟጋቾች በላቲን አሜሪካ ውስጥ ማኅበረሰቦችን የሚጎዱ የማዕድን ሥራዎችን ለማስወገድ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተነገረ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ኢግልሲያስ ማይኔሪያ” የሚባለው በላቲን አሜሪካ ውስጥ የአገሬው ተወላጆች መብቶችን የሚደግፉ ድርጅቶች የአብያተ ክርስቲያናት እና ተሟጋች ድርጅቶች የጋራ አውታረ መረብ ሲሆን በማዕድን ቁፋሮ የተጎዱ ማኅበረሰቦችን ለመደገፍ የሚሠራ እንደሆነ ታውቋል። ድርጅቱ ከቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ጋር በመሆን የአካባቢ ማኅበረሰቦችን ከሚጎዳ የማዕድን ማውጣት ተግባር ለመላቀቅ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ማስጀመሩን ዓርብ ዕለት በቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል በኩል አስታውቋል።

ከፔሩ የመጡት የአይማራ መሪ ዮላንዳ ፍሎሬስ የአገሬው ተወላጆች በሚገኙባቸው ግዛቶች ውስጥ ከማዕድን ቁፋሮ ጋር የተያያዙ የአካባቢ እና የጤና ስጋቶች መኖራቸውን ገልጸው፥ ማኅበረሰቦች የአካባቢ ብክለትን እና ከባድ የሆኑ የብረት ማዕድናት የሚያስከትሏቸውን ተፅእኖዎች ለመመርመር እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።

በቫቲካን ቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል በኩል ምስክርነታቸውን የሰጡት ዮላንዳ ፍሎሬስ ተፅእኖዎችን ለመገምገም እና ማዕድናትን የማውጣት ሥራዎችን በገንዘብ የሚደግፉትን መለየት እንዲችሉ ድጋፍ ጠይቀዋል። እንዲሁም የትምህርት ዕድል፣ ሐዋርያዊ ድጋፍ እና የአገሬው ተወላጆች የሚያቀርቡት ጥያቄዎች የበለጠ ተሰሚነት እንዲኖራቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ዝምታ አማራጭ ሊሆን አይችልም

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ ካርዲናል ፋቢዮ ባጆ ማዕድናትን የማውጣት ሥራ ብዙውን ጊዜ ከአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር ሳይመካከሩ እና የሥነ-ምህዳር ገደቦችን ሳያጤኑ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በማዕድን ኢንዱስትሪ ውስጥ ሥራውን የማገድ መርሃ ግብር የቴክኒክ ወይም የፋይናንስ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የአስፈላጊ ለውጥ ተጨባጭ ምልክት መሆን እንደሚፈልግ አብራርተው፥ ሰብዓዊ ክብርን ከመጠበቅ እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ለመንከባከብ ካለው ቁርጠኝነት እና እምነታችን ጋር የተጣጣመ ተግባር እንደሆነ አስረድተዋል።

“በህጋዊም ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ በሚከናወኑ የማዕድን ቁፋሮ ምክንያት ተግዳሮቶች እና ግጭቶች በቀጥታ የሚያጋጥማቸውን ማኅበረሰቦች ማዳመጥ አስፈላጊ ነው” ብለው “ግልጽ የሆኑ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች ሲከሰቱ ዝም ማለት አንችልም” ብለዋል።

በቀላሉ የሚታለሉ እና የሚበዘበዙ ድሃ የአካባቢ ማኅበረሰቦች

ሰብዓዊ መብቶችን፣ የአገሬው ተወላጆችን፣ ስደተኞችን እና ማኅበራዊ ፍትህን በመከላከል የሚታወቁት በጓቲማላ የሁዌቴናንጎ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አልቫሮ ራማዚኒ በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዳበረውን “የውዳሴ ላንተ ይሁን” ሁሉ አቀፍ ኢኮሎጂያዊ ጽንሰ-ሀሳብ እና ለድሆች ቅድሚያ የሚሰጠው አማራጭ የሚጠይቀውን የህልውና መሠረታዊ መርህ አስታውሰዋል።

በጓቲማላ በአገሬው ተወላጆች መሬት ላይ የሚፈጸመው የማዕድን ቁፋሮችን በመጥቀስ ለአካባቢው ሕዝብ ስለሚሰጠው ጥቅም፣ ስለሚኖረው ተጽእኖ እና ስጋት አንስተዋል። ኩባንያው መሬቱን ከአገሬው ተወላጆች በእጅግ ዝቅተኛ ዋጋ ከገዛ በኋላ መደበኛ የሕግ እንቅስቃሴን መጀመሩን ካርዲናሉ ተናግረው፥ ነገር ግን የአካባቢውን ሕዝብ የማይጠቅም እና በፍትህ መስፈርት የማይመራ መሆኑን አስረድተዋል።

ለገንዘብ ማባበያ አለመፍራት

የብራዚል ጳጳስ አቡነ ቪሴንቴ ፌሬራ በላቲን አሜሪካ የማዕድን ቁፋሮ መስፋፋት ከማዕድን፣ ከጂኦፖሊቲካዊ እና ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ አስረድተዋል። “አረንጓዴ ካፒታሊዝም” ተብሎ የሚጠራውን የተሳሳተ መፍትሄ እና ለላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን ሕዝቦች ተጨማሪ ስጋቶችን የሚፈጥሩ ተለዋዋጭ የግጭት ሁኔታዎች በማለት ገልጸዋል።

የአገሬው ተወላጆች ግዛቶች ዓለም አቀፍ የኃይል መዋቅሮችን ለማስቀጠል ብርቅዬ መሬቶች በሚጠይቁት አዲስ የወታደራዊ ኒዮኮሎኒያሊዝም ዒላማ እየሆኑ መምጣታቸውን እና በተጎዱ ማኅበረሰቦች ላይ የገንዘብ ጫናም እንደሚደርስ አስጠንቅቀዋል።

አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ

የቅድስተ ቅዱሳን ቤዛ ሚስዮናዊ እህት እና የኦስትሪያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተልዕኮ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ የሆኑት እህት አኔሊሴ ሄርዚግ፥ የማዕድን ኢንዱስትሪዎች በሚያስከትሉት ውጤቶች በተጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕፃናትን ከጉዳት መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸው፥ በፖሊሲ እና በተግባር ላይ ለውጦች እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ እመቤታችን ማርያም ሚስዮናዊ እህት ማማሊፋር ፖሬኩም በበኩላቸው የተቀናጀ የሥነ-ምህዳር ርህራሄ ብቻ ሳይሆን ስልታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል። የወደፊት ጉዞ እምነትን እና ኢኮኖሚያዊ ምርጫዎችን ማመጣጠን እንደሚገባ ያሳሰቡት እህት ማማሊፋር፥ ለትርፍ ሲባል የተሰዉ የሰማዕታት ግዛቶችን በመጥቀስ፥ አክለውም የሥነ ምህዳር ቀውስ ቀስ በቀስ ማስተካከያዎችን እንደሚጠይቅ እና ትንቢታዊ አመራርን እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

የማዕድን ቁፋሮን ማገድ እንደ ሥነ ምግባር እና ውጤታማ ስትራቴጂ መመልከት

የኮምቦኒ ማኅበር ሚስዮናዊ እና የኔትወርኩ አስተባባሪ አባ ዳርዮ ቦሲ በመጨረሻም በቫቲካን የተጀመረው መርሃ ግብር ለመረጃ ልውውጥ፣ ለማዕድን ቁፋሮ እና ለፋይናንስ ሂደቶች ጥናት ቦታ እንዲሆን የታሰበ መሆኑን እና ትብብርን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

በብራዚል ውስጥ ከትላልቅ የማዕድን ቁፋሮ ሥራዎች ጋር የተያያዙ የአካባቢ ጉዳት ምሳሌዎችን ጠቅሰው፥ በዓለም ዙሪያ ከባንኮች እና ከኢንቨስትመንት ፈንዶች በአሥር ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ዶላር ከዓለም አቀፍ ፋይናንስ የተቀበሉ ኩባንያዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

በዚህ መሠረት በርካታ ማኅበራዊ እና የቤተ ክርስቲያን ድርጅቶች የማዕድን ቁፋሮን መከልከል የመብት ጥሰቶችን ለመፍታት እንደ ሥነ ምግባራዊ እና ውጤታማ ስትራቴጂ አድርገው መቁጠር መጀመራቸውን አስረድተዋል።

 

 

21 Mar 2026, 14:57