ፈልግ

በኒውዮርክ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ዓርማ በኒውዮርክ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ዓርማ  (©Lewis Tse Pui Lung - stock.adobe.com)

ቅድስት መንበር የእምነት ነፃነት ምርጫ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ስትል አስታወቀች

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ተልዕኮ፥ መሠረታዊ የእምነት ነፃነት ሲከለከል “እምነት ለፍርሃት ሊጋለጥ፣ ውይይት በጥርጣሬ ሊተካ እና ጭቆና ደግሞ ዓመፅን ሊያስከትል ይችላል” ሲል አስጠነቀቀ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሕፈት ቤት የቅድስት መንበር ቋሚ ተልዕኮ፥ ዓለም አቀፍ እስልምና ጠል እንቅስቃሴን ለመዋጋት መጋቢት 7/2018 ዓ. ም. በተደረገው ከፍተኛ ዝግጅት ላይ መግለጫ አውጥቷል።

ዝግጅቱ የተጀመረው እስልምና ጠል እንቅስቃሴን ለመዋጋት ቁርጠኝነት የታየበትን ተነሳሽነት በመቀበል የቅድስት መንበር ልዑካን ለተባበሩት መንግሥታት የሥልጣኔ ጥምረት እና የእስልምና ትብብር ድርጅት ቋሚ ታዛቢ ተልዕኮ ደረጃውን የጠበቀ ዝግጅት በማድረጉ ለእስልምና ትብብር ቋሚ ታዛቢ ተልዕኮ ያቀረበውን ምስጋና በመግለፅ እንደሆነ ታውቋል።

እየጠፋ የመጣው የአንድነት ትስስር

የቅድስት መንበር ቋሚ ተልዕኮ በመግለጫው፥ “በሙስሊሞች፣ በአይሁዶች፣ በክርስቲያኖች እና በሌሎች ባህላዊ ሃይማኖቶች ተከታዮች ላይ ያነጣጠሩ አለመቻቻሎች፣ መድልዎች እና ጥላቻውዎች እየጨመሩ የመጡት ለሃይማኖት ወይም ለእምነት ነፃነት የመብት እውቅና ካለመስጠት እና ካለመከላከል ነው” ሲል አስረድቷል።

“ይህ መብት ምርጫ የሚሰጠው አይደለም ሲል” የገለጸው ቋሚ ተልዕኮው፥ “ለእምነት ነፃነት የመብት እውቅናን መስጠት ለማንኛውም ፍትሃዊ ማኅበረሰብ የማዕዘን ድንጋይ ነው” ሲል አስገንዝቧል። መግለጫው አክሎም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 10/2025 ዓ. ም. በችግር ውስጥ ለወደቀች ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ለሚያደርጉ የድርጅት ተጠሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ “የሰው ልጅ ነፃነቱን ሲነፈግ ለእውነት ጥሪ በነፃነት ምላሽ የመስጠት አቅሙ ይጠፋል” ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን አስታውሷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማስጠንቀቂያቸው፥ “በዚህ ምክንያት ማኅበረሰቦችን የሚደግፉ የሥነ ምግባር እና መንፈሳዊ ትስስር ቀስ በቀስ መፍረስን፣ እምነት ለፍርሃት መጋለጥን፣ ውይይት በጥርጣሬ መተካትን እና ጭቆና ለዓመጽ መጋለጥን ያስከትላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ግለሰቦችም ሆኑ ማኅበረሰቦች ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል

መግለጫው በመቀጠልም፥ በዓለም ላይ የእስልምና ጠል እንቅስቃሴ ቀጣይነት፣ የሃይማኖት ነፃነትን ለመከላከል አስቸኳይ አስፈላጊነትን የሚያስታውስ እንደሆነ ገልጾ፥ በሙስሊሞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እና መድልዎ ከግለሰብ በላይ መላውን ማኅበረስብ የሚጎዳ መሆኑን አስረድቷል።

እንዲሁም የማኅበረሰቦችን መንፈሳዊ፣ ሥነ ምግባራዊ እና ማኅበራዊ መዋቅርን በመጉዳት ሰብዓዊነት በአሁኑ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ በተለይ የሚፈልገውን የመተማመን እና የአንድነት ትስስርን እንደሚያዳክም አሰርድቷል።

“ዛሬ ይህ መድልዎ በበይነ መረብ ላይም እየተስፋፋ ነው” ያለው መግለጫው፥ “ጥላቻን የሚዘሩ ትረካዎች በፍጥነት ሊሰራጩ እና የሕዝብን ግንዛቤ ሊቀርጹ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ መግለጫው ገልጾ፥ ቅድስት መንበር ይህን ለመዋጋት በተለይም ዲጂታል ሚዲያን ማንበብ እና መጻፍ፣ ሰዎች የተሻሉ ሂሳዊ አስተሳሰብ ክህሎቶችን እና የመንፈስ ነፃነትን እንዲያዳብሩ ለመርዳት የተሰጡ የተሻሉ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲኖሩ ጥሪ አቅርቧል።

መግለጫው በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የ “Nostra Aetate” ወይም “የእኛ ዕድሜ” የተሰኘ ሐዋርያዊ ሠነድ ስድሰኛ ዓመት መታሰቢያን በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 28/2025 ዓ. ም. ያደረጉትን ንግግር በመጥቀስ፥ “በዚህ ጊዜ ውይይት መሣሪያ ወይም ዘዴ እንዳልሆነ ነገር ግን የሕይወት መንገድን የሚያዳምጥ እና የሚናገር የልብ ጉዞ ነው” ማለታቸውን አስታውሷል።

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ተልዕኮ እንዳብራራው፥ “ልዩነቶች ከመከፋፈል ይልቅ የብልጽግና ምንጭ እንዲሆኑ እና ምንም ሃይማኖት እንዳይበዘበዝ ወይም መሳሪያ እንዳይሆን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብሏል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እስልምና ጠል አስተያየቶች መጨመራቸውን መረጃዎች አሳይተዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. ከአውሮፓ ኅብረት መሠረታዊ መብቶች ኤጀንሲ የወጣ አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው፥ በአውሮፓ ኅብረት አገራት ውስጥ ከሁለት ሙስሊሞች አንዱ የዘር መድልዎ እንዳጋጠመው፥ በተለይም በሥራ እና በመኖሪያ ቤቶች አቅርቦት ላይ እንደ ነበር አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ የእስልምና ጠል እንቅስቃሴዎችን ለመዋጋት በየዓመቱ በመጋቢት 15 የሚከበረው በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በ60 የእስልምና ኅብረት ድርጅት አባል ሀገራት የተደገፈው ውሳኔ ከፀደቀ በኋላ እንደ ጎርጎሳውያኑ በ2022 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል።

ዘንድሮው ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት በዓሉ “ከደንቦች ወደ ተግባር፣ በሃይማኖት ወይም በእምነት ላይ የተመሠረተ እስልምና ጠል እንቅስቃሴ እና መድልዎን መፍታት እና ለሰብዓዊ መብቶች ያለው ትስስር” በሚሉ ርዕሥ መከበሩ ታውቋል።

 

18 Mar 2026, 15:30