አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ፥ ነፃ ሕይወት ያለ ቅድመ ሁኔታ የሚያፈቅር መሆኑን አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ በዐብይ ጾም ወቅት አራተኛ እና የመጨረሻ ስብከታቸው የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ምድራዊ ሕይወት ፍጻሜን በማስታወስ፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የራሱን ደካማነት እና ትንሽነት መማር እንደቻለ ገልጸው፥ መገለል፣ ሕመም ወይም ሞት እንኳን ቢሆን ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል እንደሌለ ተናግረዋል።
አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ በተገኙበት እና “የእግዚአብሔር ልጆች ነፃነት” በሚለው የዐብይ ጾም የመጨረሻ ጭብጥ ላይ በማስተንትን ስብከታቸውን አቅርበው፥ አራቱም የዐብይ ጾም ወቅት ስብከታቸው በወንጌል በመለወጥ ጉዞ ላይ በነበረው የአሲሲው ድሃ ሰው ምስል የተመሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
ቅዱስ ፍራንችንስኮስ በድህነት ሕይወቱ በእግዚአብሔር ተመርቷል
ፍራንችስካዊው ካኅን አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ በስብከታቸው፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ በእግዚአብሔር በመመራት የሕይወት ተጨባጭነትን እና ድህነትን እንደተማረ አስረድተዋል።
ሌላው ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆን መንፈስ ቅዱስን በግልጽ መቀበል መቻሉን ገልጸው፥ በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ጣሊያናዊው ፍራንሲስካዊ ካኅን የሴላኖ ቶማስ ቅዱስ ፍራንችስኮስ “ወደ ሕያው ጸሎት ተለውጧል” ማለቱን አስታውሰው፥ ይህም “መላው የሕይወት መንገዱ ቀጣይነት ያለው ጸሎት ነው” ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
የፍጹም ደስታ ጉዞ
ይሁን እንጂ በእነዚያ የመጨረሻ ዓመታት ቅዱስ ፍራንችስኮስ በታላቅ ፈተና ውስጥ አልፏል” ያሉት አባ ፓሶሊኒ በመቀጠልም፥ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር ማደጉን እና መለወጡን ገልጸው፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከዚህ ተለይቶ ከንቱነት እንደተሰማው እና እንዲያውም እንደ ሞኝ ተቆጥሮ እንደ ነበርም አስታውሰዋል።
ቅዱስ ፍርንችስኮስ ከእርሱ ጋር ከነበረው ሌላው ወንድም ሊዮ ጋር በቅድስት ማርያ ዴሊ አንጀሊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ “እውነተኛ እና ፍጹም ደስታ” የሚለውን ምሳሌ በመጋራት ለእርሱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የኩራት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ውብ ነገሮችን እንዲዘረዝር ጠይቆታል።
በመጨረሻም ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወንድም ሊዮ “በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ ፍጹም ደስታ የለም” ብሎ እንዲጽፍ እንደጠየቀው ተናግረው፥ “ማንኛውም ዓይነት መገለል፣ ውርደት እና አለመግባባት ሰላማችንን ሊነጥቁን በማይችሉበት ጊዜ እውነተኛ ደስታ ይገለጣል” ሲሉ አብራርተዋል። እውነተኛ ደስታ በአሉታዊ ሁኔታዎች ውስጥ ምላሽ በምንሰጥበት ጊዜ እና በመገለል ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ደስታ ራስን ከእውነታው መለየት ሳይሆን ነገር ግን በጉዳትም ጊዜ መቀበልን መማር እንደሆነ ገልጸው፥ የክርስትና ሕይወት ነገሮች እንዴት እንደሚጓዙት ማወቅ ሳይሆን ተጨባጭ በሆነ መንገድ መኖርን መምረጥ እንደሆነ አስረድተዋል።
የሙሉ ሕይወት ተስፋ
በወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የአኗኗር ዘይቤን አስይቷል ያሉት አባ ፓሶሊኒ፥ በጥላቻ እና በስደት ውስጥ የሚገኝ ሕይወት በስሙ ሙሉ የአዲሱ ሕይወት እንደሆነ ያሳያል ብለዋል። ይህ በይፋዊ አገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ስለ ብፀዕና ባስተማረው ሕግ ሳይሆን ቃል ኪዳን በሆነው ግልጽ ትምህርቱ ማሳየቱን ገልጸው፥ እነዚህም የሥነ ምግባር ፍጹምነት ሳይሆን፣ በእውነታው ልብ ውስጥ ቀድሞውኑ በሥራ ላይ ያለው የደስታ መገለጥ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ብፁዓን ከእውነታው እንድንሸሽ ወይም ደስታን ለወደፊት ጊዜ እንድናስተላልፍ የማይጋብዙ መሆናቸውን የገለጹት አባ ፓሶሊኒ፥ ደካማ እና ያልተጠናቀቀ ቢመስልም የምንኖረውን ነገር በጥልቀት እንድንኖር የሚጠይቁን መሆናቸውን ገልጸው፥ ወደ ሙሉ ሕይወት የሚወስደው መንገድ በተጨባጭ ልምዳችን፣ በማንነታችን እና በምን ውስጥ እያለፍን እንደሆነ ያስረዱናል ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ነፃነት በውጫዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ አይደለም
“ብፁዓን ይህ ሕይወት በሙላት የምንቀምስበት ቦታ እንደሆነ ይነግሩናል ያሉት አባ ፓሶሊኒ፥ “ብፁዓን የጀግንነት መንገድን እንደማይገልጹ ተናግረው፥ ጥረትን፣ ብቸኝነትን እና ስደትን ቢጠይቅም ነገር ግን ለመኖር ለተሰጠን ነገር ትሑት ፈቃደኞች ለመሆን ያስችሉናል” ብለዋል። ይህ ማለት ሕይወትን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ወይም በሐሳብ መግለጽ ሳይሆን ነገር ግን በአሳዛኝ እና በሚያምር ተጨባጭነቱ መገናኘት እንዳለበት አሳስበዋል።
የወንጌላዊነት ደስታ ቁስሎችን እና ሕመሞችን እንደማያስወግድ የገለጹት አባ ፓሶሊኒ፥ በቁስሎች ውስጥ በማለፍ እና በመለወጥ ወደ ትልቁ ፍቅር እንደሚስወደን ተናግረዋል። በዚህ እውነታ ውስጥ ባለው ታማኝነት ውስጥ አዲስ ነፃነት እንደሚወለድ እና ከአሁን በኋላ በውጫዊ ሁኔታዎች ላይ እንደማይመካ አስረድተዋል።
የፍቅር ውጤቶች
አባ ፓሶሊኒ አስተንትኖአቸውን በመቀጠልም፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ የስቃይ ምስጢር በምዕመናን ሕይወት ውስጥ ይንጸባረቃል” የሚለውን የሚስጥራዊ ክስተቶች ጭብጥ በመጥቀስ፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስን በ ላ ቨርና ተራራ ላይ የደረሰውን መገለል አስታውሰዋል።
“እግዚአብሔር እንድንሰቃይ አይፈልግም” ያሉት አባ ፓሶሊኒ፥ “አንድን ሰው በጥልቀት ሲነካ ህመምን ሳይጨምር ነገር ግን በታሪኩ ውስጥ ያለውን ነገር እየለወጠ የፍቅር ምልክት እና ውጤት ያደርገዋል” ብለው፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወደ ላ ቨርና ተራራ ላይ የወጣው በድካም በተሞላ አካል እንደሆነ ገልጸው፥ ወደ ዓይነ ስውርነት እየተለወጥ በነበረው ሕመም እና ከአቅም በላይ በሆነ ማኅበር ውስጥ በሚገኝ ታላቅ ፈተናን የተሸከመ ነፍስ ይዞ እንደሆነ አስረድተዋል። በዚያም እግዚአብሔር ጣልቃ የሚገባው አዳዲስ ቁስሎችን በመፍጠር ሳይሆን በሕይወት ውስጥ ያሉትን ቁስሎች በመለወጥ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሕመም የመጨረሻ ቃል የለውም!
አባ ፓሶሊኒ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ቅንዋት ወይም ቁስሎች የውስጥ ለውጥ ምልክትን የሚያሳዩ እንደሆኑ ተናግረው፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከ ላ ቨርና ተራራ የወረደው በታወቀ አካል እና በነፃ ልብ እንደሆነ ገልጸው፥ ሕመም ባይጠፋም ነገር ግን የመጨረሻ ቃል እንደሌለው እና ይህም ለእኛ ዛሬ መልካም ዜና እንደሆነ አስረድተዋል። “ስቃይ የማይጠፋ ቢሆንም እኛን ለማደናቀፍ ኃይል የለውም” ብለው፥ “በልባችን ውስጥ ምንም እና ማንም ሊወስደው የማይችለው ሰላም እንዳለን እናውቃለን” ብለዋል።
የመለወጥ የመጨረሻ ዕድል
ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከመሞቱ በፊት ባሉት ወራት ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን የልመና ተግባር ይፈጽም እንደ ነበር እና ይህም ዳቦን ለማግኘት ሳይሆን ለመጽናናት፣ ለቅርብነት እና ለርህራሄ እንደሆነ አስረድተው፥ መቀበልን በመማር በአሲሲ ጳጳስ ቤት ውስጥ የተደረገለትን እንክብካቤ መቀበሉን አስታውሰዋል። ይህም ለመኖር እና ለመሞት ሌሎች ሰዎች እንደሚያስፈልጉት የሚያውቅ ሰው ድህነት እንደ ሆነ አስረድተው፥ ሞትን እህቴ ብሎ ሲጠራት ይህ ቃል የመጽናኛ ዘይቤ ሳይሆን ነገር ግን የረጅም ጉዞ የእርቅ ፍሬ እንደሆነ አስረድተዋል። ምክንያቱም ወደ ዕብራውያን የተጻፈው መልዕክት እንደሚለው፥ “ዲያብሎስ በሕይወታችን ሁሉ የሞት ፍርሃት ባሪያዎች ያደርገናል” የሚለውን አስታውሰዋል።
ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በውስጣችን አዲስ ሕይወት ሲፈጥር ያ ፍርሃት ቀስ በቀስ እንደሚጠፋ እና ሞት ፊቱን እንደሚለውጥ አስረድተው፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወደ ሕይወቱ ፍጻሜ እየተቃረበ መሆኑን ሲያውቅ እራሱን በዓለም ውስጥ እጅግ ውድ ወደሆነው ወደ ፖርዚዩንኮላ ማምጣቱን ተናግረው፥ እዚያም ከሮማዊው ጓደኛው ጃኮፓ ዴይ ሴቴሶሊ መጎበኘቱን እና በጣም የሚወዳቸውን ጣፋጮችን እንዲያመጣለት መጠየቁን ተናግረዋል።
ወንጌላዊ ድህነት የቅዱስ ፍራንችስኮስ የመጨረሻ ተግባር እንደሆነ የተናገሩት አባ ፓሶሊኒ፥ “በድካም ውስጥ መታየትን የሚቀበል ሰው፥ መቀበል የመስጠት ንፁህ መንገድ እንደሆነ እና ራስን እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲወደድ መፍቀድ ትልቁ ነፃነት መሆኑን ከተማረ በኋላ መሞቱን አስታውሰዋል።
በምድር ላይ ራቁቱን መሆን
ቅዱስ ፍራንችስኮስ ክርስቲያናዊ ጀግና ሳይሆን ችግረኛ ሰው ሆኖ መሞቱን አባ ፓሶሊኒ አስታውሰው፥ እርቃኑን በባዶ መሬት ላይ እንደተኛ እና ይህ የሕይወቱ ሙሉ ፍጻሜ እንደሆነ አስረድተዋል።