ፈልግ

በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የተመራው መስዋዕተ ቅዳሴ በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የተመራው መስዋዕተ ቅዳሴ  

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን እግዚአብሔር የጦር መሣሪያን ዝም እንዲያሰኝና ለሰው ልጆች እርቅን እንዲያወርድ ተማጸኑ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን እ.አ.አ. በ 1926 ዓ.ም. የተመሰረተው እና የወታደሮችን ሃይማኖታዊ ሕይወት ለመንከባከብ የተቋቋመውን ‘ወታደራዊ አገልግሎት ጉባኤ’ 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ የተካሄደውን መስዋዕተ ቅዳሴ መምራታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የጣሊያን ‘ወታደራዊ አገልግሎት ጉባኤ’ 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ሮም በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ የተካሄደውን ሥርዓተ ቅዳሴ የመሩ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 1926 የተመሰረተው ይህ ጉባኤ ለጣሊያን ወታደራዊ ሰራተኞች እና ለቤተሰቦቻቸው መንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ እርዳታ ለመስጠት እንደተቋቋመ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የካራቢኒየሪ፣ የጣሊያን ጦር፣ የጋርዲያ ዲ ፊናንዛ፣ የአየር ኃይል እና የባህር ኃይል አባላት መገኘታቸው ተገልጿል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ጦርነት በተከሰተባቸው አከባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን በመማጸን “ሁላችንም እንደምናውቀው አሁን ባለንበት የጦርነት ወቅት የጦር መሳሪያዎች ጸጥ እንዲሉ እና ለሰው ልጆች በሙሉ እርቅ እንዲወርድ አምላካችንን እንማጸናለን” ብለዋል።

የአገልግሎት እና የመስቀል አመክንዮ
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊው በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈሪሳውያንን ባህሪ የገለጸበትን ታሪክ በማስታወስ፥ ይህ ታሪክ በወታደራዊ አውድ ውስጥ ለሚያገለግሉት ካህናት መነሻ ይሆናል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን አክለውም “የወንጌሉ ቃል ‘በሌሎች’ ላይ ክስ መስርቶ የሚቀር ሳይሆን፥ ነገር ግን ለእያንዳንዳችን የሥነ ምግባር መለኪያ ይሆናል” ያሉ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት በአገልግሎት ውስጥ ለተገለጸው የሥልጣን ተዋረድ፣ እንዲሁም ወደማይጨቆነው ወይም ትኩረትን ወደማይፈልግ ነገር ግን አጋዥ እና የመደገፍ ባህሪ ላለው መገኘት ትሑት እንድንሆን ጥሪ ያደርግልናል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ መስቀሉ “የክርስቲያን ባለ ሥልጣናት ሁሉ ምሳሌ” መሆን እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተው ያሳሰቡ ሲሆን፥ በዚህ አመክንዮ ውስጥ የማህበራት እና ጉባኤዎችን ተልእኮ በዛሬው ዓለም አቀፋዊ አውድ ውስጥም መረዳት የሚቻለው፣ በቀጣይ ግጭቶች እና የስነ-ምግባራዊ ማስተዋልን ውስብስብ በሚያደርጉ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ውስጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ የሰላምን ባህል ማበረታታቷን እንደማታቆም ጠቁመው፥ ሰላም እንዲወርድ የፍትህ፣ የውይይት እና የመብት ጥበቃ ሁኔታዎችን በትዕግስት መገንባት እንደሚገባ ቤተክርስቲያኒቷ ተረድታለች ብለዋል።

በዝምታ የማዳመጥ ወጥነት
ካርዲናል ፓሮሊን ወደ ዕለቱ የወንጌል ምንባባት በመመለስ በፈሪሳውያን አመለካከት ውስጥ የመጀመርያው “ስብራት” ወጥነት የጎደለው መሆኑን ጠቁመው፥ ስለዚህ የወታደራዊ አገልግሎት ተልዕኮ “ጸጥ ያለ ወጥነት ያለው፣ ከመፍረድ በፊት የማዳመጥ ችሎታ ያለው፣ ያለ ጣልቃ ገብነት የሚደገፍ፣ እንዲሁም ያለ ሥነ ምግባር ጉድለት ስለ እግዚአብሔር የመናገር ችሎታን” የሚያካትት እንደሆነ አብራርተዋል።

ሁለተኛው "ስብራት" የሕጉን ግንዛቤ የሚመለከት መሆኑን የጠቆሙት ካርዲናሉ፥ በወንጌሉ ክፍል ውስጥ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተገለጸው ፈሪሳውያን “ከባድ ሸክሞችን አስረው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ” ብለዋል።

“በወታደራዊ አውድ ውስጥ የቤተክርስቲያኒቱ መገኘት፣ አስቀድሞውኑ በዲሲፕሊን እና በከባድ ሀላፊነቶች ተለይቶ ይታወቃል” ያሉት ካርዲናሉ፥ በዚህም ምክንያት የቤተክርስቲያኗ መገኘት ሸክም ላይ ሸክም የሚጨምር ሳይሆን፥ ካህናት አገልጋዮች የተጠሩት የመተንፈሻ እና የማስተዋያ ቦታ እንዲኖር የሚያደርጉ፣ እንዲሁም ታዛዥነት የጎደለው እና ተግሣጽ ወደ ሥነ ምግባራዊ አካሄድ እንዳይለወጥ ኅሊናን የሚያበሩ አጋሮች ናቸው ብለዋል።

የሰው ልጅ በጣም የተቀደሰ ቦታ
የሁለተኛው የቫቲካን ምክር ቤት ጉባኤ ሃዋሪያዊ መተዳደሪያ ደንብ በሆነው ‘ጓዲየም ኤት ስፔስ’ (Gaudium et Spes) መሰረት “ሕሊና” የሚለው ቃል ሲገለጽ “አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ በሚሆንበት ወቅት በጣም ምስጢራዊ ማዕከሉ እና የተቀደሰ ቦታው” መሆኑን እንደሚገልጽ በመጥቀስ፥ በዚህም መሰረት የቤተክርስቲያን ተግባር ይህን የማይደፈር የሰው ልጅ ቦታ መጠበቅ እና ብርሃን እንዲኖረው ማድረግ ነው ብለዋል።

ከዚህ በመነሳት ከወታደራዊ አባላት ጋር አብረው የሚኖሩ የካህናት ተልዕኮ እንደሚፈጠር እና ካህናቱ “ኃላፊነትን እና ውስጣዊ ነፃነትን ማስተማር” እንዳለባቸው የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በሚያገለግሉባቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የወታደሮችን ተግባራት የሚያሳዩት አደጋን የመፍራት እና የመስዋዕትነት ቁስል በሚኖርበት ሁኔታ የልባም እና ታማኝ አገልጋይ ካህናት በስፍራው መገኘት የቤተክርስቲያን የእናትነት ተጨባጭ ምልክት ይሆናል ብለዋል።

የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ ክብር ማክበር
በፈሪሳውያን ህዝባዊ ሕይወት ውስጥ ሦስተኛው “ስብራት” ባላቸው የታይታነት ባህሪ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን እና ፈሪሳዊያኑ ሁሉንም ነገር የሚያደርጉትን “በሌሎች ዘንድ እንዲደነቅላቸው” በመሻት እንደሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማስጠንቀቁን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የታይታነት ፍለጋ፣ ለግላዊ ምስል መጨነቅ እና የመታየት ፍላጎት ለወታደራዊ አገልግሎት ካህናት ፈተና ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊው “ከእናንተም የሚበልጠው የእናንተ አገልጋይ ይሁን” የሚለውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት አስታውሰው፥ በዚህ አካሄድ ካህኑ ለጥሪው ታማኝ በመሆን፣ መዋቅሮችን በማጠናከር ወይም ታይታነትን በመፈለግ ሳይሆን በሳል ማስተዋልን በማጎልበት እንዲሁም ጥንካሬን እና ሃላፊነትን በአንድ ላይ ማዋሃድ የሚችል፣ ለመንግስት ታማኝ በመሆን እና የእያንዳንዱን ሰው የማይናቅ ሰብዓዊ ክብር በማክበር አገልግሎቱን እንዲፈጽም ያስችለዋል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን አክለውም ግጭቶች የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር አደጋ ላይ የሚሆንበት አከባቢ ስለሆነ በጦርነት ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን “ወታደራዊ ሕሊናን መንከባከብ እና ማገልገል” በጣም አስፈላጊ ነገር መሆኑ አመላክተዋል።

በግጭት ላይ ድል መቀናጀት
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ ሰላምን አስመልክተው ጸሎት ያደረጉ ሲሆን፥ “በትንሳኤው ሁሉንም ዓመፅ አሸንፎ ዓለምን ከራሱ ጋር ያስታረቀ ጌታ አገልግሎታችሁን የታመነ የፍትህና የሰላም ምልክት ያድርግላችሁ” በማለት ለአገልጋዮቹ ጸልየዋል።

ከሚያዚያ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የጣሊያን ወታደራዊ አገልግሎት ጉባኤ ሃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ ጂያን ፍራንኮ ሳባ በበኩላቸው ጥቂት ቃላትን ያጋሩ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ ለብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሰላምታ ባቀረቡት ወቅት በዓለም አቀፍ ተልእኮዎች ላይ የተሰማሩ ወታደሮችን አስመልክተው እንደትናገሩት “የዓለምን ግጭቶች በምንመለከትበት ጊዜ ድምጻችን ለቆሰሉት፣ በውጭ ሃገራት ለሚሠሩ ወታደራዊ ሠራተኞች፣ ለቤተሰባቸውና ለሃገራት መሪዎች ጸሎት ይሆናል” በማለት ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

06 Mar 2026, 10:07