ብጹዕ ካርዲናል ዴ ሜንዶንካ፥ ሥነ-ግጥም ሰላምን እንደሚደግፍ አስታወቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ ካርዲናል ደ ሜንዶንሳ ዓለም አቀፍ የሥነ-ግጥም ቀንን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ ሥነ-ግጥም ጥልቅ ከሆኑ የማዳመጥ ዓይነቶች አንዱ እንደሆነ ገልጸው፥ ከዝምታ የሚመነጭ እና ምናልባትም ገጣሚዎች ከጸሐፊዎች በላይ ከአጽናፈ ዓለሙ ከሚታዩ እና ከማይታዩት ነገሮች ጋር ራሳቸውን ለማስማማት የሚችሉ ተርጓሚዎች እንዲሆኑ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።
ካርዲናል ሆሴ ቶሌንቲኖ ዴ ሜንዶንካ፥ ገጣሚዎች ከፍጥረት ጋር በሚያደርጉት ምስጢራዊ ውይይት ድምጻቸው እንደሚቀረጽ እና ከዚህም በላይ በውስጣቸው በሚሰጡት ቦታ ግጥምን ወደ ሰላም ትምህርት እንደሚለውጡ አስረድተው፥ “የሚርገበገቡ የቢራቢሮ ክንፎች” የሚል ግጥም በማስታወስ የቃላት መርገብገብ በሰው ልብ ውስጥ የትርጉም፣ የብርሃን ወይም የጨለማ ኃይልን እንደሚያቀጣጥል ገልጸው፥ “ግጥም ሰላማዊ እና ትጥቅን የሚያስፈቱ ቃላትን የሚሰጥ ቀዳሚ የሰላም ጥበብ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዝደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ቶሌንቲኖ ዴ ማንዶካ ይህን የተናገሩት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት “ዩኔስኮ” እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1999 ዓ. ም. የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሥነ-ግጥም ቀን በተከበረበት እና ዓለማችን በጦርነት እየተሰቃየ በሚገኝበት ወቅት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል።
ከወደፊት ሁኔታ ጋር የተደረገ ስምምነት
ብጹዕ ካርዲናል ዴ ሜንዶንሳ ጥንታዊ ትስስር የግጥም ጥበብን ከእውነት ጋር እንደሚያገናኝ በመጥቀስ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፈረንሳዊ ገጣሚ ቻርለስ ባውዴሌርን በማስታወስ፥ “ልብን በማጋለጥ እና እርቃኑን በመተው ከታላላቅ የሰው ልጆች ጥያቄዎች ጋር ቅርብ እንደሆነ ገልጸው፥ ታላቁ ገጣሚ ፖል ሴላ “እውነተኛ ግጥሞችን የሚጽፉት እውነተኛ እጆች ብቻ ናቸው” ማለቱን አስታውሰዋል።
ግጥም በዘመኑ ቀውሶች መካከል የመንፈስ ጽናትን የሚያመለክት እንደሆነም ተነግሯል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “አዲስ የተስፋ ካርታዎችን መሳል” ባሉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ላይ የግጥም አስፈላጊነትን ሲያስታውሱ፥ “የትምህርትን ሰብዓዊነት የሚተካ ምንም ዓይነት ስልተ ቀመር የለም፤ ግጥም፣ ፌዝ፣ ፍቅር፣ ሥነ-ጥበብ፣ ምናብ፣ የግኝት ደስታ እና የትምህርት መሳሳትም ቢሆን ለዕድገት ዕድል ሊሆን ይችላል” ማለታቸው ይታወሳል።
በዚህ ረገድ ብጹዕ ካርዲናል ዴ ሜንዶካ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል። “ስልተ ቀመር ያለፉትን እርምጃዎች እንደገና የሚደግም አእምሮ የሌለው ዘዴ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ ሥነ-ግጥም ግን እስካሁን ያልተሞከረውን መንገድ ወደማይታወቅ መንገድ የሚወስድ እና በዓለም ውስጥ የሚገኝ ያልተሰማ ቃል ፍለጋ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“አንድ ሰው ግጥም መግጠም ሲጀምር ከእርሱ ምን ሊመጣ እንደሚችል አያውቅም” ብለው አለማወቅ በራስ ግንባታ ውስጥ የሰው ልጅ ካፒታል እንደሆነ አስረድተዋል። የስልተ ቀመር ትልቁ አደጋ ከሰው ልጅ ሊገኝ የሚችለውን የማየት ችሎታን መግታት እንደሆነ ገልጸው፥ ስልተ ቀመር በእርስ በርስ ግንኙነት፣ በስጦታ እና በምስጢራዊ የመገመት ችሎታ ዘወትር ስለ ትላንት የሚናገር ሲሆን ሥነ-ግጥም ግን ከወደፊት ሁኔታ ጋር ስምምነት አለው” ሲሉ አስረድተዋል።
የገጣሚዎች ብቸኛነት
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሥነ-ግጥም ለዘላለም ይኑር!” ሲሉ በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ ሥነ-ግጥም ሰው በመሆን ውስጥ ያለውን አስፈላጊነት እና በካህናት ስልጠና ውስጥ የሚጫወተውን ሚና እንደያስታውስ ተናግረዋል።
ከዚህ ነጥብ በመነሳት ብጹዕ ካርዲናሉ ደ ሜንዶካ “በአንዳንድ ብቸኛ የሥነ-ግጥም የሕይወት ታሪኮች ውስጥ ትልቅ ትምህርት አለ” ሲሉ አረጋግጠዋል። ለራስ ታማኝ ሆኖ ለመቆየት እና በየቀኑ በቋሚ ውጥረት ውስጥ ሁሉንም ታላላቅ የሕይወት ልምዶችን ወደ ግጥማዊ ገጽታ መቀየር ማለትም ወደ ንቃተ ህሊና እና የግንዛቤ ገጽታ ለማምጣት የሚሞክር ፖርቱጋላዊው ገጣሚ ፈርናንዶ ፔሶአን ጠቅሰዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በታይላንድ እና ጃፓን ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሲመለሱ፥ ምዕራቡ ዓለም ነገሮችን በግጥም ዓይን መመልከትን ከምሥራቁ ዓለም መማር ይችላል” ሲሉ መናገራቸውን ካርዲናሉ አስታውሰው፥ “ግጥም ከሕይወት በፊት የሚደረግ የአምልኮ ሥርዓት፣ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ቅርብ መሆናችንን የምናውቅበት፣ ለአስተንትኖ እና ለዝምታ አድናቆትን የምንስጥበት በመሆኑ መንፈሳዊ ትምህርት ሊሆን ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።
የግጥም አስተማሪነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዘንድሮ በየካቲት ወር በተካሄደው መንፈሳዊ ልምምድ መደምደሚያ ላይ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ጆን ሄንሪ ኒውማን እና “የጄሮንቲየስ ህልም” በሚል ርዕሥ የጻፉትን ግጥማቸውን በመጥቀስ፥ አንባቢው ሞትን እና የጄሮንቲየስን ፍርድን ለሞት ያለውን ፍርሃት እና በእግዚአብሔር ፊት የከንቱነት ስሜትን ለማስታወስ እንደ መሣሪያነት መጠቀሙን ገልጸዋል።
የሃይማኖት ምሁር እና ግጥም ወዳድ ቅዱስ ጆን ሄንሪ ኒውማን ብዙ የሚያስተምራቸው ነገሮች እንዳሉት የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ዴ ሜንዶካ፥ “ቅዱስ ጆን ሄንሪ ኒውማን በዘመናዊነቱ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት እና ለሰላም ትምህርት ጥልቅ ቁርጠኝነት እንዳለው፥ እያንዳንዱ ትውልድ በቀዳሚ ማረጋገጫው እውቀትን መቀበል እና ያንን ቅርስ ማስተዳደር፣ ውስጣዊ ማድረግ፣ ዓላማ እንዲኖረው እና በዓለም ላይ በኃላፊነት የመኖር ችሎታ ሊኖረው ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
በዚህ መልኩ ሥነ ጽሑፍ እና ግጥም አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶች ጠቅላላ ትምህርት ቤቶች እንደሆኑ ገልጸው፥ ጣሊያናዊው ገጣሚ ዴቪድ ማሪያ ቱሮልዶ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. ለወጣቶች ያደረገው ንግግር በማስታወስ የሰላም ጭብጥ እጅግ አብዮታዊ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስቸጋሪም እንደሆነ ተናግረዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ዴ ሜንዶንሳ በገለጻቸው፥ ሰላም ስለ አንድነት እንደሚያስተምር፣ ስለ ሰው ልጅ የጋራ ቅርስ እንደሚናገር ገልጸው፥ ግጥም በዚህ መልኩ ሁላችንም ወንድማማቾች መሆናችንን በማስተማር የአገራት ድንበር አልፎ የሰው ልጅ ታላቅ ማከማቻ ሆኖ ይኖራል” ሲሉ አስረድተዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ዴ ሜንዶንካ አክለውም፥ ሥነ-ጽሑፍ ሁለንተናዊነትን ስለሚያከብር እና ታላላቅ ሃሳቦችን እና እጅግ ውብ ምስሎች ስለሚያቀርብ፣ እንደ ጠቅላላ ትምህርት ቤትነት እንደሚቀርብ አስረድተዋል። “ብዙ ገጣሚዎች ግጥም እነዚህ ቅርጾች በሙሉ አስቀድሞ እንዳሉት እና እነርሱን ማዳመጥ እንደምንችል ያምናሉ” ብለው፥ “ግጥም የግል የሆነውን ነገር የሚቃረን ሳይሆን ነገር ግን አስተንትኖ እና አድናቆት ለሁሉም ሰው ጥሩ መሆናቸውን ያረጋግጣል” ብለዋል።
ያለ ዝምታ ግጥም የለም
“ግጥም ያለ ዝምታ ሊኖር አይችልም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ዴ ሜንዶንካ በመጨረሻም፥ “ዝምታ ብዙውን ጊዜ ገጣሚዎች የሚፈልጉት ቃል ነው” ብለው፥ “ግጥም በዝምታ ከተጀመረ በኋላ ሊያድግ እንደሚችል፣ በግጥም ውስጥ የዝምታ ድምፅ መኖሩን ሊያደምጡትም እንደሚችሉ አስረድተዋል።በመሆኑም ግጥም የፍለጋን ጥማትን እና መረበሽን የሚይዝ፣ እውነትን በትህትና የሚያኖር እንደሆነ ገልጸው፥ “ግጥም ሁሉን ነገር እንዴት መጠበቅ እንደሚገባ የሚያውቅ ነው” ሲሉ ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።