ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በካስቴል ጋንዶልፎ አረጋውያንን በጎበኙበት ወቅት የሚያሳይ የማህደር ምስል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በካስቴል ጋንዶልፎ አረጋውያንን በጎበኙበት ወቅት የሚያሳይ የማህደር ምስል   (ANSA)

‘እኔ ግን በፍጹም አልረሳችሁም’ በሚል ጭብጥ 6ኛው የዓለም የአያቶች እና አረጋውያን ቀን እንደሚከበር ተነገረ

ስድስተኛው የዓለም የአያቶች እና አረጋውያን ቀን በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 49 ቁጥር 15 ላይ በተመሰረተው ‘እኔ ግን በፍፁም አልረሳሽም’ በሚል ጭብጥ እንደሚከበር የቫቲካን የምዕመናን፣ ቤተሰብ እና ህይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ማክሰኞ ዕለት በሰጠው መግለጫ ይፋ ማድረጉ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 49 ቁጥር 15 ላይ የተመሰረተው ‘እኔ ግን በፍፁም አልረሳሽም’ የሚለው ሃሳብ ስድስተኛው የዓለም የአያቶችና አረጋውያን ቀን መሪ ቃል እንዲሆን መምረጣቸውን የቫቲካን የምዕመናን፣ ቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በላከው መግለጫ የገለጸ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 2021 በነፍስኄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተመሰረተው የዓለም ቀን የሃምሌ ወር አራተኛ እሁድ ላይ የሚከበር ሲሆን፥ ይህ ቀን ቤተክርስቲያኗ ከአረጋውያን ጋር ያላትን ቅርበት ለማጠናከር፣ እንዲሁም አረጋዊያን በቤተሰብ እና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚያደርጉትን አስተዋፅዖ ለማሳደግ እንደ አንድ እድል ሆኖ እንደሚያገለግል ተነግሯል።

ዘንድሮ የሚከበረው የዓለም ቀን በጎረጎሳዊያኑ ሐምሌ 26 እሁድ ዕለት የሚከበረው የቅዱሳን ዮአኪም እና አኔ ዓመታዊ ክብረ በዓል ጋር የሚገጣጠም ሲሆን፥ እያንዳንዱ ሰው በየሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚደረጉ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲያከብረው ቅዱስ አባታችን መጋበዛቸው ተገልጿል።

ከነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ የተወሰደው ይህ ጥቅስ ለሁሉም አያቶች እና አረጋውያን በተለይም በብቸኝነት ለሚኖሩ ወይም እንደተረሱ ለሚሰማቸው የማጽናኛ እና የተስፋ መልዕክት እንዲሆን የታሰበ ነው የተባለ ሲሆን፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ቤተሰቦች እና የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦች አረጋዊያኑን እንዳይረሷቸው እና በእነሱ ውስጥ ውድ የሆነ መገኘት እና በረከት መኖሩን እንዲገነዘቡ ለማሳሰብ እንደሆነ ተነግሯል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምርጫ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ያለው ፍቅር በእርጅና ጊዜ ውስጥ እንኳን እንደማይደበዝዝ ያሳያል የተባለ ሲሆን፥ የቫቲካን የምዕመናን፣ ቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናት፣ ማኅበራት እና የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦች ቀኑን በአካባቢያቸው አውድ ውስጥ የሚያስተዋውቁበት እና የሚያከብሩበትን መንገዶች እንዲፈልጉ የሚያበረታታ እና ለዚሁ ዓላማ የተወሰኑ የሃዋሪያዊ ሥራ ግብአቶችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል።

12 Feb 2026, 14:39