ሞንሲኞር ማርኮ ስፕሪዚ፥ የቫቲካን ሠራተኞች መብትን ለማስከብር እንደሚሠሩ ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሐዋርያዊ መንበር የሠራተኛ ማኅበር (ULSA) ላይ የተካሄደው ጥናት ዋና ዓላማ በቫቲካን ሠራተኞች እና በቅድስት መንበር ሥር የሚገኙ ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች መካከል ያለው ግንኙነት ከግጭት፣ ከፉክክር እና ቅሬታ ይልቅ የውይይት፣ የመደማመጥ እና የትብብር መርሆችን ማጎልበት እንደሆነ ተገልጿል።
ሞንሲኞር ማርኮ የሠራተኛ ቢሮ ከሠራተኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለማዳመጥ ዘወትር ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፥ በቅርቡ የተደረገውን ጥናት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፥ ጡረተኞችን ጨምሮ በጥናቱ የተካተቱ ከ6,000 በላይ ሠራተኞች በቫቲካን የሠራተኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን እርካታ ማጣት፣ ኢፍትሃዊነትን እና የመተማመን እጦት ሁኔታዎችን አውግዘዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባለፈው ታኅሳስ ወር ያጸደቁትን አዲሱን የሐዋርያዊ ሠራተኛ ማኅበር ውል ያስታወሱት ሞንሲኞር ማርኮ ስፕሪዚ፥ ይህም የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮን ተግባራዊ በማድረግ በቅድስት መንበር በሚገኙ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች፣ መምሪያዎች፣ በቫቲካን አስተዳደር እና በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ ለሚሠሩት ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸውን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል።
ለተግባራዊነት የቀረቡት ለውጦች እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ የገለጹት ሞንሲኞር ማርኮ፥ የሠራተኛ ጽ/ቤት ውክልና እና ተልዕኮ ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና ከተከታዮቹ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ራዕይ ጋር በሚስማማ መልኩ የአንድነት እና የማሳደግ ተልዕኮ ሆኖ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉን አፅንዖት ሰጥተዋል።
አንድነት ማለት በተመሳሳይ አቅጣጫ መጓዝ፣ የጋራ ኃላፊነት መሰማት እና በቅድስት መንበር ተልዕኮ ውስጥ መካፈል ማለት ነው” ያሉት ሞንሲኞር ማርኮ፥ “ይህ ማለት ለሠራተኞች የሚሰጥ ጥበቃን መቀነስ ማለት ሳይሆን ይልቁንም በውይይት እና በጋራ መተማመን መንፈስ ማስተዋወቅ እና መከተል ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
በቅርቡ በቫቲካን የሠራተኛ ማኅበር ላይ የተደረገውን ጥናት መመልከታቸውን የገለጹት ሞንሲኞር ማርኮ፥ ከ5% በታች የሆኑ ሠራተኞችን ባካተተ ዝቅተኛ ናሙና ላይ የተደረገ ጥናት እንደሆነ ገልጸው፥ “ትኩረት ባለመሰጠቱ፣ ውይይት ባለመደረጉ ወይም ሕጎች ባለመከበራቸው የሚያማርር የአንድ ሠራተኛ ድምጽ እንኳ ቢሆን ድምጾችን በሙሉ በቁም ነገር እንመለከታቸዋለን” ብለዋል።
“የሠራተኛው መብት በምንም ዓይነት መልኩ የማይጣስ መሆኑን ለማረጋገጥ እንሠራለን” ያሉት ሞንሲኞር ማርኮ፥ እንዲሁም ስልጠናዎችን ለመስጠት፣ በአንድ ተልዕኮ ውስጥ የመሳተፍ ግንዛቤን ለማሳደግ እና ክህሎቶችን ለማሻሻል ቁርጠኞች መሆናቸውን አስረድተዋል።
በመሆኑም ጥናቱን በቁም ነገር እና በአክብሮት እንደሚመለከቱት ገልጸው፥ ሠራተኞቹ ራሳቸው እንደሚሉት ገንቢ እና ቀጣይ ውይይቶችን በማድረግ ሁሉንም ሪፖርት በቁም ነገር እንሚመለከቱት አስረድተዋል።
ዋና ተግባራቸው እነዚህን ሪፖርቶች መመርመር እና በሕግ እና በቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ ብርሃን መገምገም እና ከሚመለከታቸው አስተዳደሮች ጋር መወያየት እንደሆነ ተናግረው፥ ይህም ለሁሉ ሰው ጥቅም ሊሆኑ የሚችሉ መፍትሄዎችን ለማሰስ የቴክኒክ የሥራ ቡድኖችን እና ጊዜያዊ ኮሚሽኖችን መፍጠርን እንደሚያካትት ገልጸው፥ ይህም ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆን በውስጧ ኢፍትሃዊነት መኖሩን መቀበል የማትፈልግ ቅድስት መንበርንም የሚያካትት መሆኑን አስረድተዋል።
የጥናት ውጤቶችን ተቀብለን በግለሰብ ደረጃ ተጨባጭ ጉዳዮች በመመልከት ደንቦች መሻሻላቸውን ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ እና ይህ ተልዕኮ እንደ ክርስቲያን እና እንደ ካህናት ሕሊናቸውን የሚፈታትን በመሆኑ በቁም ነገር የሚመለከቱት መሆኑን ተናግረዋል።
ሠራተኞችም እንደ አስተዳደሩ ሁሉ በየቀኑ በደርዘን የሚቆጠሩ ጉዳዮችን ይዘው እንደሚቀርቡ እና ብዙ ሥራ እንዳላቸው የተናገሩት ሞንሲኞር ማርኮ፥ ለማኅበሩ የዳሰሳ ጥናት ምላሽ ከሰጡት መካከል 80% የሚሆኑት ሐዋርያዊ የምዕመናን ሠራተኛ ማኅበር (ADLV) አባላት ሲሆኑ፥ ከእነዚህ ውስጥ ሁሉም ሳይሆኑ 71% የሚሆኑት ብቻ የተሰጣቸውን ጥያቄ መመለሳቸውን አስታውሰዋል።
ይህንንም ከተፎካካሪነት እይታ አንፃር እንደማይመለከቱት ተናግረው፥ ሐዋርያዊ መንበር የምዕመናን ሠራተኛ ማኅበር (ADLV) አስፈላጊ እና ገንቢ ሚና የሚጫወት በመሆኑ የሚያበረታቱት፣ የሚያሳድጉት እና ለሚያደርገው ነገር በሙሉ እንደሚያመሰግኑት አስረድተዋል።
ለፍትህ መስፈርቶች ተገቢ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ ሁሉንም ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች በደንቦቹ እና በማኅበራዊ አስተምህሮ ብርሃን እንደሚቀበሉት እና እንደሚደግፉት ገልጸው፥ እንዲሁም የከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች ለቫቲካን አስተዳደር ኃላፊነት ያላቸው እና እነዚህን ጥያቄዎች የምናቀርብላቸው ሁሉ ለውይይት ክፍት መሆናቸውን አክለዋል።
እንዲሁም በቢሮአቸው የሚገኘውን ሐዋርያዊ የምዕመናን ሠራተኛ ማኅበር (ADLV) ተወካዮችን ከጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አመራር ጋር አንድ ላይ የሚያሰባሰቡ ቴክኒካዊ የሥራ ቡድኖችን ማቋቋማቸውን ተናግረው፥ በዚህ መንገድ ወደፊት በመጓዝ ለውይይት መንገድ ሊሆኑ የሚችሉ ፍትሃዊ መፍትሄዎችን ለማግኘት የጋራ ጥረት ማድረግን እንደሚቀጡ አስረድተዋል።
የልዩነት እና የግጭት መንገድ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ራዕይ እና ከቅድስት መንበር ሚስዮናዊ አቀራረብ መገለሉን የተናገሩት ሞንሲኞር ማርኮ፥ ለቅድስት መንበር የሚሠሩ ሰዎች ተልዕኮአቸውን በመቀበል ለግጭት ቦታ እንደማሰጡ፥ ይልቁንም እንደ ኦርኬስትራ ቡድን እያንዳንዱ የራሱን ድርሻ መጫወት እንዳለበት ተናግረዋል።
የሠራተኛውን ችግር በጽሞና በማዳመጥ ምላሽ የሚገኝበትን ስምምነት ለማምጣት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረው፥ ይህም የዕለት ተዕለት ተልዕኳቸው እንደሆነ ገልጸው፥ አንዳንድ ጊዜ ዘዴዎቹ የተለያዩ ቢሆኑም ለሁሉም ሰው ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ከሠራተኞች ጋር ከተደረጉት በርካታ ስብሰባዎች የተገኘውን ልምድ መሠረት በማድረግ የታየው ስሜት እርካታ የሌለበት ሳይሆን በአጠቃላይ እጅግ አዎንታዊ እንደሆነ ተናግረው፥ በመላው ዓለም እና በጣሊያን ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በርካታ ሰዎች ከሥራቸው መገለላቸውን ገልጸው፥ ነገር ግን በቅድስት መንበር ማንም ሰው ከሥራው እንዳልተባረረ እና ደሞዙም እንዳልተቀነሰበት ተናግረዋል።
በዚህ ምክንያት ሠራተኞች ከሁሉም በላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ማመስገናቸውን አስታውሰው፥ ወረርሽኙ በቅድስት መንበር ፋይናንስ ላይ ተጽዕኖ ቢያደርግም በሠራተኞች ላይ ጉዳት አለማስከተሉን ገልጸው፥ በሌሎች በርካታ ትናንሽ የዕለት ተዕለት ተግባሮች ማለትም የሕፃናት ማቆያ አገልግሎት፣ የበጋ ወቅት የዕረፍት ጊዜ፣ የሱፐርማርኬት አገልግሎት፣ በሠራተኛው ማኅበረሰብ እውነተኛ ተደራሽነት ላይ ያተኮሩ የአካል ጉዳተኞች መመሪያዎች፣ ለጡረተኞች የሚሰጥ ትኩረት እና ከሞላ ጎደል ነፃ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት በማጠናከር ላይ ተጽዕኖ አለማሳደሩን አስረድተዋል።
በአጭሩ ብዙ ሰዎች በቫቲካን ተቀጥረው ለመሥራት የሚፈልጉት ሕክምናው እና ሌሎች አገልግሎቶች ጥሩ በመሆናቸው እንጂ እርካታ ማጣታቸውን ያዩበት ሁኔታ እንደሌለ ገልጸው፥ ነገር ግን ትኩረት እና መሻሻል የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እንዳሉ መገንዘባቸው ገልጸዋል።
የደመወዝ ደረጃዎችን በትክክል ከሚከናወኑ ተግባራት ጋር ማስተካከል፣ ቀደም ባሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ወይም በሃብት መቀነስ ምክንያት ማንም ሰው ሥራውን እንዳያጣ የሚያደርጉ አስፈላጊው ማስተካከያዎች እንዳልተደረጉ እና በዚህ ምክንያት በደል ለደረሰባቸው ሠራተኞች ፍትህ ለማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሠራተኛውን መብቶች የሚጎዱ እርምጃዎችን ሪፖርት ለማድረግ እና ይግባኝ ለማለት የሚያስችሉ ሕጋዊ ጥበቃዎች መኖራቸውን የገለጹት ሞንሲኞር ማርኮ፥ የማጥቃት ጉዳዮች ካሉ በእርግጠኝነት ሪፖርት መደረግ እንዳለባቸው እና ምክንያቱም በሥራው ዓለም ሞራላዊ የፍትህ መስፈርቶች “Rerum Novarum” ወይም “አዳዲስ ነገሮች” ከሚለው የርዕሠ ሊቃነ ሊዮ 13ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ጀምሮ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላኛው ደግሞ እውነቱን ማረጋገጥ መሆኑን የተናገሩት ሞንሲኞር ማርኮ፥ በእርግጥ ሠራተኛን ጉዳት እንደደረሰበት የሚገልጹ ክሶች ቢኖሩ ኖሮ፣ ይህ የማይከሰት መሆኑን ለማረጋገጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመጀመሪያው ጣልቃ ስለሚገቡ ሊከሰት እንደማይችል አስረድተው፥ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ዛሬ በመላዋ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በሐዋርያዊ መንበር ውስጥ ሲኖዶሳዊነትን በማስተዋወቅ የማኅበር እና የአንድነት መንፈስ ማበረታታቸውን ገልጸዋል።
በተቻላቸው መጠን ከሠራተኞች ጋር በግልም ሆነ በማኅበር በኩል እንዲሁም ሠራተኞችን ከሚቀጥሩ አካላት ጋር ውይይትን የበለጠ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸው ተናግረው፥ በተጨማሪም በሠራተኞች እና በአስተዳደር መካከል የሚደረግ ውይይት በወንጌል እና በቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ብርሃን ላይ የተመሠረተ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የኅብረት መንፈስ ለሠራተኞች መብቶች ክብር በመስጠት እና ድልድይ በመሆን የበለጠ ገንቢ እና ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ የሚጥሩ መሆናቸውን፥ የሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ ማኅበር (ULSA) ፕሬዝዳንት ሞንሲኞር ማርኮ ስፕሪዚ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አብራርተዋል።