ካርዲናል ፓሮሊን፥ ቤተ ክርስቲያን ተዓማኒነቷን የምትገልጸው በስልጣን ሳይሆን በወንጌል ምስክርነት መሆኑን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ቤተ ክርስቲያን ተዓማኒነቷን የምታስመሰክረው በስልጣን፣ በምዕመናኖቿ ብዛት ወይም በምትወጥናቸው እቅዶቿ ሳይሆን ነገር ግን በእምነቷ ሕያው ምስክርነት፣ በእውነተኛ የነፃነት፣ የፍትህ እና የምሕረት ተግባራትን በተጨባጭ ስትገልጽ ነው” ብለዋል።
ብጹዕነታቸው ይህንን የተናገሩት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክተኛ ሆነው ቅዱስ አንስጋር በዴንማርክ የወንጌል ተልዕኮ የጀመረበት 1,200ኛ ዓመት ለማክበር በኮፐንሃገን ካቴድራል እሑድ ጥር 17/2018 ዓ. ም. በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ እንደሆነ ታውቋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “የቅዱስ ብሩክ ማኅበር መነኩሴ በ9ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ሰሜን አውሮፓ የሄደው ዕቅዱን ለመዘርጋት እና በዚህም ስኬታማ ለመሆን ሳይሆን ነገር ግን ለኢየሱስ ክርስቶስ ባለው ታማኝነት ላይ የተመሠረተ የወንጌል ተልዕኮን ለመፈጸም መሆኑን ተናግረው፥ የመጀመሪያ ተግባሩ የነበረው አንዳንድ ሰዎችን ከባርነት ቀንበር ነጻ ማውጣት ነው” ሲሉ አስታውሰዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በማከልም “የመነኩሴው ዋና ዓላማ በአዳዲስ የባርነት ዓይነቶች፥ በኢኮኖሚያዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ባርነት ውስጥ የወደቁትን ነጻ ለማውጣት እንደሆነ ገልጸው፥ ማግለል እና ንቀት በሚታይበት በዛሬው ዓለም ውስጥ የመነኩሴው እርምጃ አዲስ ጠቀሜታ አለው” ሲሉ ተናግረዋል።
በእግዚአብሔር ይቅር የመባል ደስታ
ቀደም ሲል የተጀመረው የጥንካሬ ትስስር፣ ቀጣይነት ያለው ሐዋርያዊ እንክብካቤ እና ወንጌላዊ ቅንዓት ከአሥራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን በፊት የአንስጋርን ተልዕኮ እንዳበረታታው አፅንዖት ሰጥተው፥ “መነኩሴው ይህን ተልዕኮ የጀመረው በራሱ ሕይወት ውስጥ ካለው ልዩ የነፃነት ተሞክሮ በመነሳት ነው” ብለዋል።
በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ከኢሳ. 52:7-10 ተወስዶ የተነበበውን መሠረት ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “መልዕክቱ ስለ ሌላ ሳይሆን መልዕክተኛው በሚናገራቸው ሃሳቦች ወይም ማብራሪያዎች ሳይሆን መልካሙን ዜና የሚሰሙትን ሰዎች ልብ በመለወጥ እና ነፃ በማውጣት ማዳን የሚችል ነው” ብለው፥ በተመሳሳይ መልኩ አንስጋር በእግዚአብሔር ይቅር በመባል ደስታን በማግኘት እና ያንን ደስታ ለሌሎች ለማካፈል እንደፈለገ ገልጸው፥ “ይዞት የተጓው የምሥራች ቃልም ይህ ነበር” ብለዋል።
ኢየሱስን የመከተል ድፍረት
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ዛሬ ዴንማርክ እና ስዊድን ተብለው በሚጠሩ አገራት ሕዝቦች የመጀመሪያው ክርስቲያን ሚስዮናዊ በነበረው የቅዱስ ብሩክ ማኅበር መነኩሴ በአባ አንስጋር ስም በተሰየመች ቤተ ጸሎት ውስጥ ባደረጉት ንግግር፣ የመነኩሴውን ታሪካዊ ጊዜያትን በማስታወስ፥ ዛሬ በጀርመን ውስጥ ወደምትገኝ ኮርቢ የፈረንሳይ ገዳም ገና በሃያ ዓመት የልጅነት ጊዜ መግባቱን አስታውሰዋል።
ከዚያም ንጉሠ ነገሥት ሉዊስ ፒዮስ የጥምቀት ምስጢር አዲስ የተቀበለውን የዴንማርክ ንጉሥ ሃራልድ ክላክን በሐዋርያነት የሚያገለግሉ ካኅናትን በጠየቀ ጊዜ በዴንማርክ የወንጌል ተልዕኮውን ለመፈጸም ድፍረት ማግኘቱን ገልጸዋል።
ኢየሱስን ለመከተል ሲሉ የለመዱት ቦታዎችን እና ሰዎችን ጥለው የሚሄዱትን አገልጋዮች ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ አባ አንስጋር ግን ፈጽሞ ወደ ሌላ ቦታ ሳይሄድ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ያስደነቀ ድፍረት እና እምነት ማሳየቱን አስታውሰው፥ የአንስጋር ተከታይ እና የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ ቅዱስ ሬምበርት፥ አንስጋር ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲል ከባድ የሕይወት ምርጫዎችን ሲያደርግ የተመለከቱት ሰዎች እንደሚገረሙ ገልጸው፥ የቅዱስ ብሩክ ማኅበር መነኩሴ አባ አንስጋር እንደ ክርስቲያን ከወንጌል ጋር በሚስማማ መንገድ ክርስትናውን በተጨባች መኖሩን ተናግረዋል።
የተለወጡ ልቦች
“አባ አንስጋር በከፍተኛ ተቃውሞ የተሸነፈ ቢመስልም ስኬቱ ግን እርሱ የፈለገው አልነበረም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆርንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ መልዕክት ላይ “የመስቀል ሞኝነት” ያለው በእርሱ ላይ መታየቱን አስተውሰው፥ “የኃይል፣ የተፅዕኖ እና የስኬት ዋጋን በሚያሳይ ዓለም ውስጥ የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሸነፈ ይመስላል” ብለዋል።
“ነገር ግን ይህ ሞኝነት የእግዚአብሔር ጥበብ ነው” ሲሉ ያስረዱት ብጹዕነታቸው፥ ራሱን ሙሉ በሙሉ መስጠት የሚችል ፍቅርን ያሳያል” ብለው፥ በተመሳሳይ ሁኔታ የአባ አንስጋር የሕይወት ታሪክ ቤተ ክርስቲያን የምታድገው በቁጥር ሳይሆን የታማኝነት፣ የጽናት እና የፍቅር ሕይወት በሚኖሩ ምዕመናን ውስጥ እንደሆነ እና የወንጌል ተልዕኮ የሚጀምረውም በተለወጠ ልብ ነው” ብለዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዚህ አውድ ቅዱስ አስጋርን ለማስታወስ በተዘጋጀው የኢዮቤልዩ ክብረ በዓላት ላይ የተሳተፉት ሁሉ ወንጌላዊ ድፍረታቸውን እንዲያድሱ እና ታሪክ ደክሞ በሚታይበት ተስፋን እንዲሰንቁ አሳስበዋል። እድገት የሚገኘው አንድ ከሚያደርግ ፍቅር እና እጅግ ደካማ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን በእግዚአብሔር ዘላቂ ተግባር ላይ በመታመን መሆኑን እንዲመሰክሩ ጋብዘዋል።
ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መጓዝ
“ዛሬ ዴንማርክ አባ አንስጋር ሲመጣ እንዳገኛት አረማዊ ምድር አይደለችም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የአገሪቱ ታሪክ በክርስቲያናዊ ቅርሷ በማይጠፋ ሁኔታ የተመሰለ ነው” ብለው፥ የካቶሊክ ማኅበረሰብ ከሉተራኖች እና በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች ሁሉ ጋር በአገልግሎት፣ በወንድማማችነት እና ለሰው ልጅ ክብር አስተዋጽኦ ያበረክታሉ” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን “በእርሱ አንድ ነን” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሐዋርያዊ ሥልጣን መሪ ጭብጥ በመጥቀስ ቅዱስ አንስጋር የኢየኡስ ክርስቶስ ተከታዮች ተልዕኮ የጀመረው በተለወጠ ልብ እንደሆነ እና የቤተ ክርስቲያን ተዓማኒነት የሚለካው በቁጥር ወይም በስኬት ሳይሆን ነገር ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመጓዝ እና በማንኛውም ሁኔታ ከእርሱ ጋር በቅርበት በመቆየት ችሎታ መሆኑን በመግለጽ ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።