በኩዌት የምትገኘው የአረቢያ እመቤታችን ቤተክርስቲያን ወደ ንዑስ ባዚሊካ በኩዌት የምትገኘው የአረቢያ እመቤታችን ቤተክርስቲያን ወደ ንዑስ ባዚሊካ   (Copyright (c) 2024 demesafrankc/Shutterstock. No use without permission.)

በኩዌት የአረቢያ እመቤታችን ቤተክርስቲያን ወደ ንዑስ ባዚሊካ ማዕረግ ከፍ እንድምትል ተገለጸ!

የቫቲካን ዋና ጸኃፊ የሆኑት ካርዲናል ፒትሮ ፓሮሊን ለሁለት ቀናት ጉብኝት ወደ ኩዌት ሊጓዙ እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን እዚያም ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር ይገናኛሉ እና የአረቢያ እመቤታችንን ቤተክርስቲያንን ወደ ንዑስ ባዚሊካ ማዕረግ ደረጃ ከፍ እንደምያደርጉ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

እ.አ.አ ሰኔ 28/2025 ዓ.ም ቫቲካን በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኩል በሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር ውስጥ የምትገኘውን እጅግ ጥንታዊ የሆነችውን የአረቢያ እመቤታችንን ቤተክርስቲያን ወደ ንዑስ ባዚሊካ ከፍ ለማድረግ መወሰናቸውን አስታውቀው እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን የቫቲካን ዋና ጸኃፊ ካርዲናል ፒትሮ ፓሮሊን ሐሙስ ዕለት ጥር 07/2018 ዓ.ም ወደ ኩዌት በመሄድ መስዋዕተ ቅዳሴን በማሳረግ እና ማዕረጉን ለመስጠት ወደ ኩዌት እንደሚጓዙ ይጠበቃል፣ ይህም የንዑስ ባዚሊካ ክብር የተቀበለች በባህረ ሰላጤው ክልል ውስጥ የመጀመሪያው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ያደርጋታል።

ካርዲናሉ ከኩዌት የሲቪል ባለስልጣናት ጋር ይገናኛሉ እና በኩዌት ከተማ በሚገኘው የቅድስት ቤተሰብ ንዑስ ካቴድራል ከአካባቢው የካቶሊክ ማህበረሰብ ጋር ይገናኛሉ ሲል X በተሰኘው የቲውተር ገጽ ላይ በወጣው የቫቲካን ጽ/ቤት መግለጫ ላይ ስፍሯል።

የሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር ባህሬን፣ ኩዌትን፣ ኳታርን እና ሳውዲ አረቢያን ያቀፈ ሲሆን በጳጳስ አልዶ ቤራርዲ፣ የሚመራ ነው።

በአህማዲ የሚገኘው እና የሰሜናዊው ሐዋርያዊ አስተዳደር “እናት ቤተክርስቲያን” ተብሎ የሚታሰበው የአረቢያ እመቤታችን ንዑስ ባዚሊካ ትሑት ሥሮች ያሏት ሲሆን ቀደም ሲል የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በነበረበት ቦታ ላይ ይገኛል።

ሕንፃው እ.አ.አ በታህሳስ 1948 ዓ.ም የካርሜላይት ማሕበር አባቶች እና የጳጳስ ኡባልዶ ቴኦፋኖ ስቴላ ሥራ አማካኝነት ወደ ጊዜያዊ ጸሎት ቤት ተለውጧል።

የኩዌት የነዳጅ ኩባንያ ከጳጳሱ ጋር በመተባበር በነዳጅ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመስራት ወደ ኩዌት የመጡ ስደተኞች መንፈሳዊ እንክብካቤ ለመስጠት ቋሚ የቤተክርስቲያኗን ሕንፃ ለመገንባት በገንዘብ ፋይናንስ አድርጓል።

ንዑስ ባዚሊካ የአረቢያ እመቤታችን ምስል - በመጀመሪያ ለቀርሜሎስ ተራራ እመቤታችን የተሰጠ - ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዩ 12ኛ እ.አ.አ በ1949 ዓ.ም የባረኳት እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ እ.አ.አ በ2011 ዓ.ም ዘውድ የጫኑባት ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ተያይዞ ከደረሰን ዜና ለመረዳት ተችሏል።

በእመቤታችን ጥበቃ ስር ያለ የስደተኛ ማህበረሰብ

እንደ ጳጳስ ቤራርዲ ገለጻ፣ ንዑስ ባዚሊካ ለስደተኛ ሠራተኞች በእመቤታችን ጥበቃ ስር የካቶሊክ እምነታቸውን የሚተገብሩበትን ቦታ መስጠቱን ቀጥሏል ያሉ ሲሆን "የታላቅ አምልኮ መቅደስ ነው" ብለዋል ጳጳሱ። "እዚህ፣ እንደዚህ ዓይነት ውክልናዎች የተከለከሉበት በብዛት ሙስሊም በሆነ ክልል ውስጥ፣ የማሪያን ምስል መኖሩ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ይህንን ጥልቅ ትርጉም ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ሲሉ ጳጳሱ አክለው ገልጸዋል።

የአረቢያ እመቤታችን የሰሜን እና የደቡብ ሐዋርያዊ አስተዳደሮች ጠባቂ ሆና ትሰራለች ያሉት ጳጳሱ የእመቤታችን በዓል የሚከበረው ካርዲናል ፓሮሊን ምስሏን የያዘችውን ቤተክርስቲያን ማዕረግ ከሰጡ ከሁለት ቀናት በኋላ በሚውልበት በሁለተኛው እሁድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

"ይህች ቤተክርስቲያን በአካባቢው 'አበባ' ናት" ብለዋል ጳጳስ ቤራርዲ። “በኢራቅና በኩዌት መካከል በተደረገ ጦርነት ወቅት እንኳን የእመቤታችን ምስል የዚያች ትንሽ ቤተክርስቲያን ጠባቂ እና መሸሽ ለማይችሉ ሁሉ ጠባቂ ሆኖ ቆይቷል” ያሉት ጳጳሱ ንዑስ ባዚሊካዎች ከሊቀ ጳጳሱ እና ከሮም መንበር ጋር ልዩ ግንኙነት አላቸው፣ እናም ማዕረጉ የሚሰጠው በአምልኮ እና በእረኝነት ሕይወት ውስጥ ልዩ ጠቀሜታ ላላቸው አብያተ ክርስቲያናት ሲሆን፣ ለታሪካዊ፣ ለመንፈሳዊ እና ለሥነ ሕንፃ ጠቀሜታቸው ጎልተው ይታያሉ ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

Photogallery

በኩዌት የአረቢያ እመቤታችን ቤተክርስቲያን ወደ ንዑስ ባዚሊካ
15 Jan 2026, 11:38