ፈልግ

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

በኢዮቤልዩ ዓመት መጨረሻ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1975 የተጀመረው የቅዱስ በሮች የመዝጋት ልማድ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ2000 ዓ. ም. በተከበረው የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ወቅት ቀለል ያሉ ማሻሻያዎችን ማድረጋቸው ይታውሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰብዓ ሰገል የተገለጠበት የመታሰቢያ ዕለት ታኅሳስ 28/2018 ዓ. ም. የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በይፋ በርን ዘግተዋል። ይህም በሮም በሚገኙ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች መካከል የመዝጋት ሥነ-ሥርዓት የተፈጸመበት የመጨረሻው ባዚሊካ እንደሆነ ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1975 ዓ. ም. የተጀመረው ቅዱስ በር የመዘጋት ልማድ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሲፈጸም የቆየ ሲሆን፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ2000 ዓ. ም. (እ.አ.አ) በተከበረው ታላቁ የኢዮቤልዩ ዓመት ቀለል ያሉ ለውጦችን ማድረጋቸው ሲታወስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ ታኅሳስ 28/2018 ዓ. ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ የመሩት ሥነ-ሥርዓት አጭር እና ብዙ ምዕመናን ያልተገኙበት እንደ ነበር ተመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሥነ-ሥርዓቱን የመሩት የቅዱስ ዓመት የምስጋና ጸሎት በመድገም ሲሆን፥ ጸሎቱም “ይህ ቅዱስ በር ቢዘጋም እግዚአብሔር ሆይ! የአንተ ምህረት በር በፍጹም አልተዘጋም” የሚል እንደ ነበር ትውቋል።

የመለኮታዊ ጸጋ ሃብቶች ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ጥሪን በማቅረብ፥ “በምድራዊ ጉዞአችን መጨረሻ ላይ የሕይወት ዛፍ ፍሬን ለማግኘት የቤትህን በር በልበ ሙሉነት እናንኳኳለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቀጥለውም፥ “የዳዊት ቁልፍ ሆይ” የሚለውን ዜማ በማቅረብ ወደ ባዚሊካው ቅዱስ በር ከደረሱ በኋላ ተንበርክከው ለጥቂት ጊዜ በጸጥታ ጸሎት ካደረሱ በኋላ ሁለቱን ታላላቅ የነሐስ በሮችን ዘግተዋል።

ይህ ምልክት የኢዮቤልዩ ጊዜ የሚያበቃ ቢሆንም ነገር ግን የእግዚአብሔር ምሕረት ዘወትር ክፍት መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል።

የቅዱስ በር መዘጋት ከተጠናቀቀ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰብዓ ሰገል የተገለጠበት መታሰቢያ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል።

ቀጣዩ የቅዱስ በር መዝጋት ሥነ-ሥርዓት

የቅዱስ በር መዝጋት ሥነ-ሥርዓት የሚካሄደው ከአሥር ቀናት ገደማ በኋላ ሲሆን፥ ይህም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት በሚያወጣው ልዩ ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸም ይሆናል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የሌሎች ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች ቴክኒሻኖች ቅዱስ በርን ለመዝጋት በባዚሊካው ውስጥ ከጡብ የተሠራ ግድግዳን ይገነባሉ።

በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ባሕላዊው የብረት ዘንግ ግድግዳው ውስጥ የሚገባ ሲሆን ከዚህም ጋር መዝጋቱን የሚገልጽ ኦፊሴላዊ ሠነድ፣ በኢዮቤልዩ ዓመት የተቀረጹ ሳንቲሞች እና የቅዱስ በር ቁልፎች አንድ ላይ ይቀመጣሉ።

07 Jan 2026, 12:40