የኢዮቤልዩን ዓመትን ለማክበር ከ33 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ወደ ሮም መምጣታቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ሰኞ ታኅሳስ 27/2018 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፥ በቅዱስ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓልን ለማክበር ከ185 አገራት ወደ ሮም የመጡት ምዕመናን ቁጥር ወደ 33.5 ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑ ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ይህን የተናገሩት የተገባደደውን የጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ. ም. አስመልክተው በቫቲካን በሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባጋሩት አኃዛዊ መረጃዎች ሲሆን፥ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት በይፋ የተገባደደውም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር ታኅሳስ 28/2018 ዓ. ም. በዘጉበት ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ ታውቋል።
በኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ነጋዲያን ከመላው ዓለም ወደ ሮም መምጣታቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ተናግረው፥ አስቀድሞ ወደ ሮም ይመጣሉ ተብሎ በሮማ ትሬ ዩኒቨርሲቲ የተገመተው የምዕመናን ቁጥር 31 ሚሊዮን እንደ ነበር ገልጸው፥ ነገር ግን ከተገመተው በልጦ መገኘቱን ተናግረዋል።
ለኢዮቤልዩ ዓመት የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን ለማድረግ እና መሠረተ ልማቶችን ለማመቻቸት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር በቅርበት የተተባበሩት የአካባቢው ሲቪል ባለስልጣናት በመግለጫው ላይ ተገኝተዋል።
ምዕመና ይህን ቅዱስ ዓመት ለማክበር ከዓለም ዙሪያ ወደ ሮም መምጣታቸው የተነገረ ሲሆን፥ በተለይም ከአውሮፓ የመጡት 62% እንደሆኑ እና በተሳታፊዎች ብዛት ጣሊያን በመጀመሪያ ደርጃ ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል። በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሰሜን አሜሪካ የነጋዲያኗ ቁጥርም 17% እንደሆነ የተገጸ ሲሆን፥ ከጣሊያን ቀጥሎ አብዛኛዎቹ የመጡት ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከስፔን፣ ከብራዚል እና ከፖላንድ እንደሆኑ ታውቋል።
ወደፊት የሚመለከት የመንፈሳዊነት ኢዮቤልዩ
“ወደ ሮም የተጓዙ ምዕመናን ቁጥርም ሆነ በዓመቱ ውስጥ የተከናወኑ 35 ዋና ዋና ክስተቶች በዋናነት የሰዎችን ሕይወት በመንካት እና በጥልቀት በማደስ እውነተኛ ትርጉማቸውን ሙሉ በሙሉ ይዘዋል ባይባልም የኢዮቤልዩ ዓመት መንፈሳዊ ገጽታ ለጸሎት እና ለለውጥ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ሕዝብ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ለማየት አስችሎናል” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ ተናግረዋል።
አራቱ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች ማለትም የቅዱስ ጴጥሮስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ፣ የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ እና የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ እና ሌሎች የጸሎት ቦታዎች እንደ ቅዱስ ደረጃዎች የመሳሰሉት ቦታዎች ታይቶ የማይታወቅ የምዕመናን ተሳትፎን አስመዝግበዋል” ብለው፥ “ምዕመናኑ በገቧቸው ኑዛዜዎች አማካይነት በኢዮቤልዩ በዓል በኩል ሙሉ ይቅርታ እና ምሕረት ወደ ሁሉም ዘንድ ደርሷል” ሲሉ አስረድተዋል።
“የኢዮቤልዩ ዓመት ቢገባደም ነገር ግን ብዙ የተስፋ ምልክቶች አሁንም አሉ” ሲሉ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ “ሁሉም ሰው የሚፈልገውን የሰላም እና የመረጋጋት ጊዜን ለመደገፍ ያለን ዕድል እየሰፋ ይሄዳል” ብለው፥ “በአጭሩ ይህ ቅዱስ ዓመት ለሁሉም ሰው ተስፋን እንደገና ለማቀጣጠል ዕድል ለመስጠት በሚል ዓላማ ‘ተስፋ ቅር አያሰኝም’ በሚለው ውስጥ የተገለጸውን ግብ አሳክቷል” ብለዋል።
የ7,000 በጎ ፈቃደኞች ልግስና
የበርካታ በጎ ፈቃደኞች ያለመታከት ሥራ በጣም አስፈላጊ ነበር” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፥በኢዮቤልዩ ዓመት ውስጥ 5,000 ሰዎች አገልግሎት እንደሰጡ እና ሌሎች 2,000 የማልታ ሉዓላዊ የምዕመናን ማኅበር አባላት በአራቱ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች የመጀመሪያ ዕርዳታ አገልግሎታቸውን እንደሰጡ አብራርተዋል።
ውይይት እና ትብብር የሚለው የኢዮቤልዩ ዘዴ
በጣሊያን መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ አልፍሬዶ ማንቶቫኖ “የኢዮቤልዩ ዘዴ” ምንን እንደሚያካትት በሰጡት ማብራሪያ፥ ሌሎች አስተዳደሮችን ማስተባበር ያለበት የክልል አስተዳደር፣ ችግሮችን የሚፈቱ የቅንጅት ስብሰባዎች እና የእያንዳንዱ ተሳታፊ አካላት የሥራ ፍሬ ፍጥነትን መለወጥ አስችሏል” ብለው፥ ይህም ለመንፈሳዊ አገልግሎት የተቀመጠ የአስተዳደር ሥርዓት ማለት እንደ ሆነ አስረድተዋል።
ሁሉንም በእንግድነት የምትቀበል ዘላለማዊቷ ከተማ
የሮም ከንቲባ እና የኢዮቤልዩ ዓመት ልዩ የመንግሥት ኮሚሽነር አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ፥ ከተማቸው እና ነዋሪዎቿ ሙሉ በሙሉ እርካታን ለማግኘት ወደ ሮም የመጡትን በርካታ ምእመናን በደስታ ሲቀበሉ መመልከታቸውን ተናግረው፥ “ወደ ሮም የመጡ ምዕመናን ሮም ቱሪስቶችን ለማስተናገድ እና ለዜጎች አገልግሎት ለመስጠት ያላትን አቅም አላጎደለም” ብለው፥ በተቃራኒው የኢዮቤልዩ በዓል ዋና አንቀሳቃሽ ኃይል ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።
“የምዕመናን ደስታ፣ እምነት እና ተስፋ የሮማውያንን ልብ ነክቷል” ያሉት አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ፥ቁጥራቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ቢሆንም ነዋሪው እንግዳን ለመቀበል ያለውን ፍላጎት በተጨባጭ መግለጹን ተናግረው፥ በነሐሴ ወር በርካታ የኢዮቤልዩ በዓል ወጣቶችን ያስተናገደው ሰፊው የቶር ቨርጋታ የመሰብሰቢያ ሥፍራ የከተማው እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ አካል ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ጠቅሰዋል።
የጤና ባለሞያዎች እና የጸጥታ ኃይሎች አስተዋጽኦ
በጣሊያን የላሲዮ ክልል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ፍራንቼስኮ ሮካ ስለ “ኢዮቤልዩ ዘዴ” ሲያብራሩ እንደተናገሩት፥ “የኢዮቤልዩ ዘዴ” ከሁሉም ሠራተኞች ጋር የመረጋጋት ስሜት ያለው አስተባባሪ ቡድን ሥራው በእርጋታ እንዲሠራ ማድረጉን ገልጸዋል።
የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ወደ 580,000 ሊሚሆኑ ሰዎች የሕክምና ዕርዳታ መስጠቱን ተናግረው፥ ይህም ካለፈው ዓመት በ40,000 እንደሚበልጥ አስረድተው፥ በድንገተኛ ክፍሎች የሚደርጉ ጉብኝቶች ወደ 1,600,000 መድረሳቸውን እና ይህም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2024 ዓ. ም. ጋር ሲነጻጸር በ100,000 እንደሚበልጥ አስረደተዋል።
በመጨረሻም የሮም ከተማ ረዳት አስተዳዳሪ አቶ ላምበርቶ ጃኒኒ ስለ ዋና ከተማዋ የጸጥታ ኃይሎች ስምሪት ሲገልጹ፥ “የነጋዲያኑን ደህንነት እና መረጋጋት መጠበቅ ያስፈልግ እንደ ነበር ገልጸው፥ ይህም በወታደራዊ ኃይል ሳይሆን ችግሮችን አስቀድሞ በመከላከል ላይ ያተኮረ እንደ ነበር አስረድተዋል።