2026.01.16 Rito della Muratura della Porta Santa dell Basilica di San Pietro 2026.01.16 Rito della Muratura della Porta Santa dell Basilica di San Pietro  (@Vatican Media)

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚልካ ቅዱስ የኢዮቤልዩ በር በታላቅ ሥነ-ሥርዓት መታሸጉ ተገለጸ

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ መሪ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ እና የጳጳሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች ዋና አስተባባሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲያጎ ጆቫኒ ራቬሊ የባዚሊካውን ቅዱስ በር የኢዮቤልዩ መጨረሻ የሚገልጽ ሥነ-ሥርዓት በመምራት አሽገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከአሥር ቀናት በፊት በሮም የሚገኙ ዋና ዋና ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች ቅዱስ በሮች ከተዘጉ በኋላ የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲልካ ቅዱስ በር በመጨረሻ መዝጋታቸው ይታወሳል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አስተዳዳሪ ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ ከጳጳሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች ዋና አስተባባሪ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲያጎ ጆቫኒ ራቬሊ ጋር በመሆን ዓርብ ጥር 8/2018 ዓ. ም. ምሽት ተካሄደውን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር የማሸግ ሥነ-ሥርዓት መርተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ባለፈው የኢዮቤልዩ ዓመት 2025 ዓ. ም. በቅዱስ በር ያለፉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያንን በማስታወስ ባቀረቡት አጭር የመክፈቻ ጸሎት፥ ነጋዲያኑ በእምነት ጠንክረው የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ከሆኑት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ኅብረት እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ ለሥነ-ሥር ዓቱ  ተብሎ የተሠራ የነሐስ ሳጥን ግድግዳ ውስጥ ኢስያስቀምጡ
ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ ለሥነ-ሥር ዓቱ ተብሎ የተሠራ የነሐስ ሳጥን ግድግዳ ውስጥ ኢስያስቀምጡ   (@Vatican Media)

የማሸጊያው ሥነ-ሥርዓት

“ሳምፒትሪኒ” ወይም የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች በባዚሊካው ውስጥ 3,200 የሚያህሉ ጡቦችን የያዘ ግድግዳ ገንብተው ቅድስት በርን አሽገዋል።

በግድግዳው ውስጥ ለበዓሉ ተብሎ የተሠራ የነሐስ ሳጥን ወይም ኮንቴይነር የተቀመጠ ሲሆን፥ ሳጥኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2025 ዓ. ም/ቱን መደበኛ የኢዮቤልዩ ዓመት ለመክፈት እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለመዝጋት የተጠቀሙበት እጄታ የተቀረጹበት እንደሆነ ተመልክቷል።

ሳጥኑ ከኢዮቤልዩ ዓመት፣ ከሁለቱ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2016 ዓ. ም. የምሕረት ዓመት ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን የያዘ መሆኑ ታውቋል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መከፈቱን እና መዘጋቱን የሚያረጋግጥ የብራና ጽሑፍ ያለበት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዘመን የመጀመሪያ ዓመት ሁለት ሜዳሊያዎች፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዘመን የመጨረሻ ዓመት የሚገልጽ ሜዳሊያ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 ዓ. ም. የምሕረት ኢዮቤልዩ እና በ2025 ዓ. ም. የተስፋ ዘመን መካከል ያሉ አሥር ዓመታትን የሚያስታውሱ ሌሎች ሜዳሊያዎች እና በ2025 ዓ. ም. አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እስከሚመረጡበት ያለውን ጊዜ የሚያሳይ ሜዳሊያ ይገኝበታል።

የኢዮቤልዩ ዓመትን የሚያስታውሱ መንፈሳዊ ቁሳቁሶች  ሳጥኑ ውስጥ ሲቀመጡ
የኢዮቤልዩ ዓመትን የሚያስታውሱ መንፈሳዊ ቁሳቁሶች ሳጥኑ ውስጥ ሲቀመጡ   (@Vatican Media)

ይህ ከነሐስ የተሠራው ዝግ እና የታሸገ ሳጥን በሌላ ሁለተኛ ሳጥን ውስጥ የተቀመጥ ሲሆን፥ በዚህ ጊዜ ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ እና የጳጳሳዊ ሥነ-ሥርዓት ዋና አስተባባሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲያጎ ጆቫኒ ራቬሊ የሥነ-ሥርዓቱን የመጨረሻ ምዕራፍ የሚያመላክቱ ሁለት የሸክላ ጡቦችን አስቀምጠዋል።

ከዚያም ሁለቱ ብጹዓን ጳጳሳት የአባታችን ሆይ ጸሎት ካቀረቡ በኋላ የመጨረሻውን ቡራኬን በመስጠት የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓትን ፈጽመዋል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መከፈቱን እና መዘጋቱን የሚያረጋግጥ የብራና ጽሑፍ
የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መከፈቱን እና መዘጋቱን የሚያረጋግጥ የብራና ጽሑፍ   (@Vatican Media)

 

 

17 Jan 2026, 15:51