በጄኔቭ በቅድስት መንበር የተልዕኮ ቡድን በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ የሃይማኖት መሪዎች እና ዲፕሎማቶች በጄኔቭ በቅድስት መንበር የተልዕኮ ቡድን በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ የሃይማኖት መሪዎች እና ዲፕሎማቶች 

ቅድስት መንበር እና ዲፕሎማቶች የር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የሰላም ጥሪ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳሰቡ

በጄኔቭ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ተልዕኮ ቡድን ለሃይማኖት መሪዎች እና ለዲፕሎማቶች ያዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ጥር 20/2018 ዓ. ም. ተካሂዷል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ለ 2026 ዓ. ም. ያስተላለፉት የሰላም ቀን መልዕክት ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሥነ-ሥርዓቱን የተካፈሉት የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ እና የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለፍትህ፣ ለሰብዓዊነት ሕግ መከበር፣ በጋራ ውይይት እና በሰብዓዊነት ላይ ለተመሠረተ የአስቸኳይ ተስፋ አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተዋል።

በዓለማችን ውስጥ ጭካኔ የተሞላበት ግጭት ከጊዜ ወደ እየጨመረ በመጣበት ወቅት፥ በጄኔቭ የተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና ሐዋርያዊ እንደራሴ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ የሚመራ የተልዕኮ ቡድን 17ኛውን ዓመታዊ የሰላም ጉባኤ ረቡዕ ጥር 20/2018 ዓ. ም. አዘጋጅቷል። በሥነ-ሥርዓት ላይ ወደ 300 የሚጠጉ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች እና የሃይማኖት መሪዎች መገኘታቸው ታውቋል።

በስዊዘርላንድ ከሎዛን፣ ከጄኔቭ እና ፍሪቡርግ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት የተካሄደ በቅዱስ ኒኮላስ ደ ፍሉይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን፥ ሥነ-ሥርዓቱ “የመሣሪያ ትጥቅ የሌለበት ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የ2026 ዓ. ም. የዓለም የሰላም ቀን መልእክት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ተመልክቷል።

ድል ሳናደርግ ድል ማድረግ

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና ሐዋርያዊ እንደራሴ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ ለእንግዶቹ ባደረጉት የሰላምታ ንግግር፥ ሥነ-ሥርዓቱ የዓመፅ እና የግጭት አመክንዮን የሚቃወም መሆኑን ገልጸው፥ የመሣሪያ ትጥቅ የሌለበት፣ ትጥቅን የሚያስፈታ ሰላም እና ጦርነት ሳይሆን እርቅን እና ለትብብር የሚያሰለጥን ሰላም ሊሰፍን እንደሚገባ አሳስበው ዲፕሎማቶች የአስተሳሰብ እና የቃላት ጦርነት እንዲቃወሙ በማሳሰብ፥ ምዕመናንም እንዲሁ በእምነት ስም ጦርነትን ለመቀስቀስ የሚጠቀሙባቸውን የዓመፅ ቃላት እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የጥረትን ሚጠይቅ ተስፋ

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒርባቲስታ ፒዛባላ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዓመፅ እንዳይረታ በማሳሰብ፥ “በሰላም ላይ ተስፋ መቁረጥ ማለት በሰው ልጅ ዘንድም ሆነ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ጦርነትን እንደ መደበኛነት መቀበል ማለት ነው” ብለው፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን የሰላም መልዕክት ጥረትን የሚጠይቅ የተስፋ መልዕክት ነው” ብለዋል።

በንግግራቸው ቅድስት ምድርን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ፥ የተኩስ አቁም ስምምነት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ አፅንዖት ሰጥተው፥ “ያለ ፍትህ ዘላቂ ሰላም የለም፣ ለሌላኛው እንደ ሰው እውቅና ካልተሰጠው እውነተኛ ፍትህ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የሰብዓዊነት አስፈላጊነት

በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ፕሬዚደንት ሚርጃና ስፖልጃሪክን ስም በምክትል ፕሬዚደንት ጊልስ ካርቦኒየር የተነበበው መግለጫ፥ በዓለም ዙሪያ 130 የትጥቅ ግጭቶች መኖራቸውን ጠቅሶ ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ የሚሰጥ አክብሮት መቀነሱን አስታውቋል።

ወደ ሰላም የሚመሩ 100 እርምጃዎች ቢኖሩ ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው እርምጃ ሰብዓዊነት ነው” ሲል መግለጫው ተናግሮ፥ “ለሰብዓዊነት ሕግ አክብሮንት ማሳየት ሕይወትን ከጉዳት በማዳን ወደ ሰላም የሚውስዱ መንገዶችን ይጠብቃል” ብሏል።

ሁሉን አቀፍ ጥሪ

ከቁምስናው የፊሊፒን እና የአፍሪካ መዘምራን ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓቱ፥ በክርስቲያን፣ በአይሁድ፣ በሙስሊም እና በቡዳ እምነት መሪዎች በቀረቡት አስተያየቶች ላይ በማስተንተን የጄኔቫ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እና የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊነትን በማጉላት፣ ሥነ-ሥርዓቱ የሎዛን፣ ጄኔቫ እና ፍሪቡርግ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ቻርለስ ሞሮድ በመሩት የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ጸሎት ተጠናቋል።

 

31 Jan 2026, 16:22