ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥  

የጦር ወንጀለኝነትን ለመከላከል ውጤታማ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ተባለ

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ የመንግሥታቱ ድርጅት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ስለመከላከል እና ቅጣት መጣልን በማስመልከት ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ ጥር 11/2018 ዓ. ም. በኒውዮርክ ለጉባኤው ባደረጉት ንግግር፥ በሰብዓዊነት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች ውጤታማ እና ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት ገንቢ ውይይት በማድረግ አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተው፥ የሰውን ሕይወት ቅድስና መጣስ መቀጠሉን አስታውሰው “በብዙ ሁኔታዎች እየጨመረ የመጣ ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ውጤታማ የሆነ የጋራ ምላሽ አለመስጠት ዋጋን ማስከፈሉ አይቀርም” ያሉት አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ “ሕጻናትን፣ ሴቶችን፣ አናሳ ቁጥር ያላቸው ጎሳዎችን እና የሃይማኖት አባላትን ሰብዓዊ ክብር እና ሞራል በእጅጉ በሚጎዳ መንገድ ስደት፣ ጥቃት እና ሞት ይደርስባቸዋል” ብለዋል።

ቅድስት መንበር የዝግጅት ኮሚቴውን ሥራ በደስታ ተቀብላ የሰውን ልጅ ከሚያጋጥሙት ጉልህ ተግዳሮቶች አንዱን ለመቋቋም ለሚያደርገው ጥረት ያላትን አድናቆት ገልጻለች።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በንግግራቸው፥ “ዋናው ጉዳይ ለእነዚህ ወንጀሎች እውቅና መስጠት ሳይሆን ወንጀሎችን ለመከላከል እና ሲከሰቱ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ ውጤታማ እርምጃዎችን ማዘጋጀት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በባሕላዊው ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የጦር ወንጀሎች የተከለከሉ መሆናቸውን እና ማንኛውም የወደፊት ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የተመሠረተ እና ለተጎጂዎች እና ለምስክሮች ተገቢ ጥበቃ ማድረግ መሠረታዊ የጋራ አቋም እንደሆነ ተናግረዋል።

ወደ ውጤታማ ምላሽ የሚመራ ገንቢ ውይይት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በውይይት ውስጥ ለመሳተፍ ጥቅም ላይ በሚውሉት ቃላት እና ፅንሰ-ሃሳቦች ላይ ስምምነት ሊኖር ይገባል” ማለታቸው እና “የቃላትን ትርጉም እንደገና ማግኘት ምናልባት በዘመናችን ካሉት ዋና ዋና ተግዳሮቶች አንዱ ሊሆን ይችላል” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻም እንደዚሁ፥ “ዓለም አቀፍ ትብብር የእንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች ዓለም አቀፍ ገጽታዎችን በመፍታት እና ግዴታቸውን በብቃት ለመወጣት አቅም የሌላቸውን መንግሥታት በመደገፍ ቁልፍ ሚና ይጫወታል” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ “እንዲህ ዓይነቱ ትብብር የተሟሉ የፍትህ ሂደቶችን እና መሠረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ሙሉ ክብር መርሆዎችን ከማዳከም ይልቅ ማጠናከር አለበት” ብለዋል።

“ዋናው ትኩረት በተጎጂዎች ላይ መሆን አለበት” ያሉት አቡነ ገብርኤል፥ ምክንያቱም “ድምፃቸው መሰማቱን እና ስብዕናቸው መከበሩን ማረጋገጥ አለብን” ብለው፥ ፍትሃዊ ሂደቶች እና መሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ አለብን” ሲሉ አክለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ በሰብዓዊነት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች ውጤታማ እና ዘላቂ ምላሽን የሚሰጥ ገንቢ ውይይት እንደሚኖር ቅድስት መንበር ተስፋ እንደምታደርግ አፅንዖት ሰጥተዋል።

 

21 Jan 2026, 14:00