የኢዮቤልዩ ዓመት ቅዱስ በሮች ቢዘጉም የኢየሱስ ልብ ለምዕመናን ዘወትር ክፍት እንደሆነ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አስተዳዳሪ ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ ከጳጳሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች ዋና አስተባባሪ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲያጎ ጆቫኒ ራቬሊ ጋር ሆነው ዓርብ ጥር 8/2018 ዓ. ም. ምሽት የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የኢዮቤልዩ ቅዱስ በር የማሸግ ሥነ-ሥርዓት መምራታቸው ይታወሳል።
ብጹዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ እና ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲያጎ ጆቫኒ ራቬሊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. በተከበረው የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት ውስጥ በሮም በሚገኙ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች ቅዱስ በሮች በኩል ያለፉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን እና የኃጢአት ሥርየትን እንዲያገኙ መጸለያቸው ይታወሳል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አስተዳደር ዋና ጸሐፊ ሞንሲኞር ኦራዚዮ ፔፔ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር ግድግዳን የማሸግ ሥነ-ሥርዓት የተፈጸመው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የባዚሊካውን ቅዱስ በር ታኅሳስ 28/2018 ዓ. ም. ከዘጉት በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
ሞንሲኞር ኦራዚዮ ፔፔ፥ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር የመዝጋት ትርጉም ምንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ፥ የቅዱስ ዓመት መዝጊያ የመጨረሻ ተግባር መሆኑን ተናግረው፥ ከውስጥ በግድግዳ የተዘጋው የባዚሊካው ቅዱስ በር ከውጪ በኩል ከነሐስ የተሠራ በር እንዳለው እና ይህ በር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መዘጋቱን አስታውሰዋል።
ሥነ-ሥርዓቱ ቴክኒካዊ ብቻ ሳይሆን የጸሎት ጊዜም እንደሆነ የገለጹት ሞንሲኞር ኦራዚዮ ፔፔ፥ ቅዱሱ በር ከሁሉም ተምሳሌታዊ ባህሪው ጋር መንፈሳዊ እውነታ እንደሆነ እና በዚህ በር በኩል በማለፍ ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ተሞክሮ የሚገነዘቡበት እጅግ አስፈላጊ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነም አስረድተዋል።
የተገነባው ግድግዳ ድርብ መሆኑን የተናገሩት ሞንሲኞር ኦራዚዮ ፔፔ፥ የመጀመሪያው ግድግዳ የኢዮቤልዩ ዓመት እና የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ዓርማ ያለባቸውን ወደ 3,200 የሚጠጉ ጡቦችን እንደሚያካትት አስረድተዋል።
ስለዚህ የመጀመሪያው ደረቅ ግድግዳ የተሠራው ከነሐስ ከተሠራው በር ጋር ቅርበት ያለው መሆኑን እና በቅርብ ቀናት ውስጥ የተገነባው ሁለተኛ የድንጋይ ግንብ ግድግዳ መሃሉ ሥነ-ሥርዓቱ በሚጠናቀቅበት ጊዜ ሳጥን የሚቀመጥበት ትንሽ ክፍተት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
ሳጥኑ የነሐስ በር ቁልፎችን፣ የመዝጊያ ሠነድን፣ የአሁኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሜዳሊያዎችን፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የተባረኩ መቁጠሪያዎችን፣ ከአሁኑ ርዕሠ ጳጳሳት ሐዋርያዊ የመሪነት ሥልጣን ጋር ግንኝነት ያላቸውን አንዳንድ ሳንቲሞችን እና ሜዳሊያዎችን እንዲሁም የባዚሊካው አስተዳዳሪ ጳጳስ ለታሪክ የሚያስቀምጣቸውን እና በሚቀጥለው የኢዮቤልዩ ዓመት እንደገና ሲከፈት የሚወጡ አራት ጡቦችን እንደሚያካትት ታውቋል።
የማሸጊያ ሥነ-ሥርዓቱ በጳጳሳዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት የሚከናወን አጭር ሥነ-ሥርዓት መሆኑን የገለጹት ሞንሲኞር ኦራዚዮ፥ በበዓሉ ላይ የሚደገሙ ጸሎቶች በቫዚሊካው ዋና አስተዳዳሪ እንደሚመሩ እና በዚህ ወቅት ሊቀ ጳጳስ ራቬሊን ጨምሮ ሌሎች የሥነ-ሥርዓቱ አዘጋጆች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ቀደም ብዬ የተጠቀሱትን መንፈሳዊ ዕቃዎች የያዘው ከእንጨት እና ከእርሳስ የተሠራው ሳጥን በግንብ እንደሚዘጋ እና ይህ ግድግዳ በሚቀጥለው የኢዮቤልዩ ዓመት መጀመሪያ ላይ እንደገና እንደሚከፈት አስረድተዋል።
በቅዱስ በር የግድግዳ ማቆም ሥነ-ሥርዓት ላይ የሚገኙ ምዕመናን በሥነ-ሥርዓቱ እጅግ እንደሚማረኩ እና በአጭር የግል ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸም ቢሆንም የባዚሊካው ታሪክ አካል እነሆነ ተናግረው፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መዝጊያ ላይ ክህሎታቸውን እና የእጅ ሞያቸውን በተጨባጭ ያሳዩ የቀድሞው ሠራተኞችን የሚያሳት በርካታ ፎቶግራፎች እንዳሉ ሞንሲኞር ኦራዚዮ ተናግረዋል።
የኢዮቤልዩ ዓመት በዓል ለቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሠራተኞች ምን እንደሆነ የተጠየቁት ሞንሲኞር ኦራዚዮ፥ የባዚሊካው ሠራተኞች እና መላው ማኅበረሰብ ከሁሉም በላይ ከዓለም አካባቢዎች ወደ ባዚሊካው የሚመጡ በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ጎብኚዎችን የሚቀበሉበት ጊዜ እንደሆነ አስረድተው፥ እንደ ክርስቲያን በሕይወታቸው ውስጥ ፍጹም ለውጥ ማምጣት ለሚፈልጉት የእግዚአብሔርን አቀባበል የሚገልጽ እንደሆነ ተናግረዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ ዓመት ውርስ በአንድ በኩል ቅዱስ በር ሲዘጋ በሌላ በኩል ደግሞ ዘወትር ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተናግረው፥ የምዕመናን ፍሰት በእርግጠኝነት የሚቀንስ ቢሆንም የቅዱስ ጴጥሮስን መቃብር ለመጎብኘት ለሚመጡ ምዕመናን እንደ ንግደት ሥፍራ፣ እንደ ቤተ መቅደስ፣ በሕይወታቸው ውስጥ የማይረሳ ጊዜ ሆኖ እንደሚቀር ገልጸዋል።
ዘንድሮ በእግር የመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የተናገሩት ሞንሲኞር ኦራዚዮ፥ ይህ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ መጨመሩን እና እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እና የእርሱን ተሞክሮ ማግኘት ወደሚቻልባቸው ቦታዎች ለመድረስ ፍላጎት እንዳለ አስረድተዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር ቢዘጋም የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ዘወትር ክፍት እንደሆነ ተናግረው፥ ተስፋቸውም ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የሚመጡ ምዕመናን በልባቸው የሚይዙትን እና ለሕይወታቸው አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ዝግጁዎች መሆን እንደሆነ ገልጸዋል።