ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በካርዲናሎች ምክር ቤት ልዩ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ላይ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በካርዲናሎች ምክር ቤት ልዩ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ላይ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በመጭው ሰኔ ወር ሌላ የካርዲናሎች ምክር ቤት ጉባኤን እንደሚጠሩ አስታወቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በታኅሳስ 29/2018 ዓ. ም. ከብጹዕን ካርዲናሎች ጋር የመጀመሪያ ጉባኤያቸውን በቫቲካን ማካሄዳቸው ተገልጿል። ቅዱስነታቸው በካርዲናሎች ምክር ቤት ልዩ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ባደረጉት ንግግር ላይ እንደገለጹት፥ የምክር ቤቱን ጉባኤ በተከታታይ በዓመት አንድ ጊዜ ለመጥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ይህን የገለጹት ከካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ቀደም ብሎ እንዲካሄድ በተጠየቀው መሠረት እና በጥቅምት ወር 2021 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደውን ጠቅላላ ጉባኤን ባጸደቁበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በታኅሳስ 29/2018 ዓ. ም. በጠሩት የካርዲናሎች የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ  የደቡብ አፍሪካው ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብሪስሊን፣ የፊሊፒንስ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዴቪድ እና የኮሎምቢያው ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ረዳ አፓሪሲዮ ጠዋት እና ከሰዓት በኋላ ያካሄዱትን ጉባኤ በማስመልከት በሰጡት አስተያየት የአንድነት ስሜት የታየበት ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

ብጹዓን ካርዲናሎቹ የመጀመሪያውን ዙር ጉባኤያቸውን ካካሄዱ በኋላ በመጭው ሰኔ ወር የቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዓመታዊ በዓል ከመከበሩ ቀደም ብሎ ለሁለት ቀናት ለሚካሄደውም ጠቅላላ የካርዲናሎች ጉባኤ ቀጠሮ የያዙለት ሲሆን፥ በቫቲካን ውስጥ በሚካሄደው በዚህ ልዩ የካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ላይ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ብጹዓን ካርዲናሎች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር እንደሚሰበሰቡ ይጠበቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሰኔ ወር ሌላ ሁለተኛ ዙር ጉባኤ እንደሚካሄድ ለመራጭ እና መራጭ ላልሆኑ 170 ብጹዓን ካርዲናሎች ያስታወቁት ረቡዕ ታኅሳስ 29/2018 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተካሄደው ሦስተኛው እና የመጨረሻው ክፍለ ጊዜ ላይ ባደረጉት የመጨረሻ ንግግር እንደ ነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከመጭው የካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ቀደም ብሎ ሌሎች ጠቅላላ ጉባኤዎች በተከታታይ እንዲካሄዱ መወሰኑን ባብራሩበት ወቅት፥ በየዓመቱ ከሦስት እስከ አራት ቀናት የሚቆዩ የካርዲናሎች ዝግ ጉባኤዎችን ለማካሄድ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፥ ይህም የወደፊት ጉዟችን ቅድመ ሁኔታ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም በጥቅምት ወር 2021 ዓ. ም. የሚካሄደው ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ባለፈው መጋቢት ወር መነገሩን በማረጋገጥ በወቅቱ በአካል የተገኙትን እና መገኘት ሳይችሉ ቀርተው በጸሎት የደገፉትን በሙሉ አመስግነዋል። የጠቅላላ ጉባኤ ጊዜን ከማረጋገጣቸው በተጨማሪ፥ ብጹዓን ካርዲናሎቹ ለነበራቸው ተሳትፎ እና ለሰጡት ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ በጉባኤው ለመገኘት ላደረጉት ጥረት ለአረጋውያን ካርዲናሎች ልዩ የምስጋና ቃል አቅርበዋል።

ከታኅሳስ 29/2018 ዓ. ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የብጹዕን ካርዲናሎች ጉባኤ መካከል ጥልቅ መግባባት እና ኅብረት መኖሩን ተገንዝቤአለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ይህም  የእያንዳንዳቸውን ዳራ እና ልምዶች ልዩነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሻለ የጋራ እውቀትን ለማሳደግ የተመረጠ ዘዴ እንደ ነበር አስረድተዋል። ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ልምድ የተወሰዱ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ እና ተሃድሶ እንዲሁም በጉባኤው ያልተመረጡት ሌሎች ሁለት ርዕሠ ጉዳዮች፥ ሥርዓተ አምልኮ እና ስብከተ ወንጌል ከጉባኤው ርዕሠ ጉዳዮች ጋር በቅርበት የተሳሰሩ በመሆናቸው ሊረሱ እንደማይገባ አሳስበዋል።

ጉባኤው በመጨረሻም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም ሆነ በብጹዓን ካርዲናሎች ኅብረት በኩል የዓለምን ጠቅላላ ሁኔታ በትኩረት የተመለከተ ሲሆን፥ ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱን ምላሽ እጅግ አስቸኳይ በማድረግ በጦርነት እና በዓመፅ እየተሰቃዩ ወደሚገኙት የምትቀርብ እንደሚያደርጋት ተገልጿል።

ቬነዙዌላን በተመለከተ

በዚህ ረገድ ጠቅላላ የብጹዓን ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤው ጭብጦች የተለያዩ ቢሆኑም፥ በስብከተ ወንጌል አኳያ በተለይም ከላቲን አሜሪካ ካርዲናሎች ቬነዙዌላን በማስመልከት ቀርቦ የጸደቀው አብላጫ ድምጽ ሲኖዶሳዊነትን እና ተልዕኮን የተመለከተ እንደ ነበር ተመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ታኅሳስ 26/2018 ዓ. ም. በመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት ያደረጉትን ንግግር ያስታወሱት በኮሎምቢያ የቦጎታው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሆሴ ረዳ አፓሪሲዮ፥ ቅዱስነታቸው በቬንዙዌላ ውስጥ ለሚሆነው ነገር ያላቸውን ጥልቅ ስጋት ገልጸው፥ ውይይትን በማበረታታት እና ስምምነትን በመፈለግ ሰላምን ማምጣት እንደሚገባ፣ ትጥቅን ለማስፈታት የሚጥር፣ የሕዝቦችን ሰብዓዊ መብቶች እና የአገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚጥር ሰላምን ለመገንባት እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።

“የቅዱስነታቸው የዕለቱ መልዕክት በእነዚህ ቀናት ውስጥ እንዳሰላስል ዕድል ሰጥቶኛል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ረዳ፥ ርዕሡ የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ኦፊሴላዊ ጭብጥ ባይሆንም ነገር ግን በቬነዙዌላ እየሆነ ስላለው ነገር መጨነቅ፣ ስለሚወሰደው አቅጣጫ፣ የላቲን አሜሪካ ጂኦፖለቲካ እንዴት እየተለወጠ እንደሚገኝ እና ቤተ ክርስቲያን ከሕዝቡ ጋር እንዴት እንደምትጓዝ ጥያቄዎችን መጠየቅ የማይቀር ነው” ብለው፥ የቬንዙዌላ ጉዳይ በልባችን የምንይዘው፣ ሁላችንንም የሚያሳዝን እና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ መልካም ለውጦች የምንፈልጋቸው ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

የጉዞ አጋር ሲኖዳላዊነትን ሕያው ማድረግ

በጉባኤው ወቅት ንግግር ያደረጉት ሦስት ካርዲናሎች በጉባኤው ወቅት የቀረቡ ጭብጦችን እና ጠቅላላ ሂደቱን በማስመልከት ባቀረቡት ሪፖርት፥ የቋንቋ ቡድኖች በሲኖዶሳዊነት ላይ በእጅጉ ማትኮራቸውን ገልጸው፥ ይህም በጉዞው አጋርነት፣ በሐዋርያዊ ሥልጣን አጠቃቀም፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ዝግጅት በቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ሥራ ውስጥ በመንጸባረቅ የበለጠ ዓለም አቀፋዊነት እንዲኖረው እና ቀጥለውም ሀገረ ስብከቶች እና የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች የሚያጋጥሟቸውን ተገዳሮቶች ለማሸነፍ የሚያግዝ የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ወንጌልን ስበኩ” የተሰኘ ሐዋርያዊ ምክረ ሃሳብ እንደገና አንብበዋል።

በጉባኤው ወቅት ከተዋቀሩ ሃያ ቡድኖች መካከል አሥራ አንዱ መራጭ ያልሆኑ ካርዲናሎች፣ ዘጠኙ መራጭ ካርዲናሎች፣ በየሀገረ ስብከቱ እና በቅድስት መንበር እንደራሴዎች ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚገኙ አባላት መሆናቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ማቲዮ ብሩኒ አብራርተዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጉባኤውን በትኩረት ይከታተሉ ነበር”

ብጹዕ ካርዲናል ብሪስሊን በበኩላቸው “ልምዱ እጅግ የሚያበለጽግ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ የዓለምን ፍላጎቶች በጥልቀት ለመረዳት እና እርስ በርስ ለመተዋወቅ ዕድል ያስገኘ እንደ ነበር አስረድተዋል።በሚቀጥለው ሰኔ ወር ላይ ሌላ ጉባኤ መካሄዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሆነው በሚጫወቱበት ሚና ልንረዳቸው እንደምንችል የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከስምንት ወራት በኋላ የሚሰበስቡን ራሳችንን እንድናዳምጥ ስለ ፈለጉ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ረዳ፥ ይህም በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ የሚያጠነክር እንደ ሆነ ተናግረዋል። የጉባኤው ተካፋዮች በሙሉ መናገር በሚችሉበት መንፈስ ውስጥ የተደረገውን ውይይት እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጉባኤውን በትኩረት መከታተላቸውንም አድንቀው፥ የሰጡት ግብዓት እጅግ የሚያበለጽግ እንደ ነበር ተናግረዋል።

እርስ በርስ የመተዋወቅ አስፈላጊነት

በጉባኤው ከተዘረዘሩት በርካታ ጭብጦች በሲኖዶሳዊነት ላይ በተደረጉት ሁለት ውይይቶች በስፋት ከተመረመሩት ርዕሦች የተገኙት አዲስ ነገሮች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ብሪስሊን በምላሻቸው፥ አዲስነቱ በውይይቶች ውስጥ ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ ለመተዋወቅ እና ለመደማመጥ ዕድል የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ተናግረው፥ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጣን በመሆናችን፣ አንዳንዶች አዲስ ሌሎቹ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ እንደመሆናቸው ይህ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

የጆሃንስበርግ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብሪስሊን አክለውም፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቤተ ክርስቲያን ሃላፊነትን መጋራት፣ እርስ በርስ መደማመጥ፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡትን ካርዲናሎች ልምድ እና እውቀት መጠቀም ይፈልጋሉ” ብለው፥ ይህ ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ሊረዳቸው እንደሚችል፣ መገለጫዎቹ የተለያዩ ቢሆኑም ሥራው በመግባባት የተከናወነ ነው” ሲሉ ካርዲናል ረዳ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

የምዕመናን እና የሴቶች ሚና

የምዕመናን ተሳትፎ እና ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ሚናን በተመለከተ የፊሊፒንስ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዴቪድ እንደተናገሩት፥ “ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚና እና አገልግሎት እንዴት መለየት አንችልም?” ብለው፥ ሴት ዲያቆናትን በማስመልከት ኮሚሽኑ በቅርቡ ያሳተመውን የጥናት ውጤት በማስታወስ የሴቶች ጥያቄ የማያቋርጥ አሳሳቢ ጉዳይ እንደ ሆነ ተናግረዋል።

ቤተ ክኅነት በምዕመናን ላይ የሚያንጸባርቀውን በላይነት የጠቀሱት ብጹዕ ካርዲናል ዴቪድ፥ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የተወሰደውን “የክኅነት አገልግሎት” ሃሳብ እንደገና በማስጀመር፥ “ስለ ቤተ ክርስቲያን ስንናገር የቤተ ክርስቲያን ራስ ብቻ ሳይሆን አካልም አለ” ሲሉ ገልጸው፥ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ ውስጥ የመሳተፍ ኃይል አላቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

 

10 Jan 2026, 16:30