ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን   (ANSA)

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በኢራን ውስጥ በተፈጸመው ግድያ የተሰማቸውን ከፍተኛ ሐዘን ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፥ በኢራን ውስጥ በሰልፈኞች ላይ በተፈፀመው ግድያ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ ቬንዙዌላ ወደ መረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ማገገም እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደምትሸጋገር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው የቅዱስ ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ ቅዱስ አጽም ለምዕመናን ይፋ በሆነበት ቅዳሜ ጥር 9/2018 ዓ. ም. ያቀረቡትን መስዋዕተ ቅዳሴ ተከትሎ በሮም በሚገኘው የዶመስ ማርያ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስት ካገኟቸው ጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

ኢራንን እያናወጣት ባለው ማለቂያ በሌለው አሳዛኝ ክስተት ያላቸውን ስጋት ገልጸው፥ “በራስ ሕዝብ መካከል ቁጣን ማስነሳት እንዴት ይቻላን?” ብለው፥ ክስተቱ ብዙ ሞትን ያስከተለ አሳዛኝ እንደሆነ ተናግረው  ሰላማዊ መፍትሄ እንደሚገኝለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ከቬነዙዌላ ጋር ስምምነት ለማድረግ የተደረገ ሙከራ

ቬነዙዌላን በማስታወስ ሲናገሩ፥ ቅድስት መንበር ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄን ለማግኘት ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ተናግረዋል።

“ከማዱሮ እና ከሌሎች የአገዛዙ ተወካዮች ጋር ስምምነት በማድረግ ማንኛውንም ደም መፋሰስ የሚያስወግድ መፍትሄ ለማግኘት ሞክረው ሳይሳካላቸው እንደቀረ ተናግረዋል።

አሁን ያለው ከፍተኛ አለመረጋጋት ተወግዶ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እና ወደ ኢኮኖሚ ማገገም ልትሸጋገር እንደምትችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የግሪንላንድን ጉዳይ ለመፍታት የብዙ አገራት ውይይት ማድረግ

ስለ ግሪንላንድ እና በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ስለተፈጠሩት ውጥረቶች የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የብዙ አገራት የጋራ ውይይት ዋጋ ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።

“በኃይል የሚወሰዱ መፍትሄዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ አይችሉም” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ ከጦርነቱ በኋላ ያለውን እና ዛሬ ቀስ በቀስ እየተዳከመ የሚገኘውን የትብብር መንፈስ አስታውሰዋል።

አለመግባባቶችን በኃይል መፍታት እና አቋምን በኃይል ማስከበር ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው፥ይህም በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ጦርነት እንደሚያስከትል አስረድተዋል።

ወጣቶችን መርዳት

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በመጨረሻም፥ በጣሊያን ላ ስፔዚያ ከተማ በስለት ተወግታ የሞተችው ወጣት ተማሪ አሳዛኝ ሁኔታን በማስታወስ፥ ትምህርት ዓመፅን በማስቀረት ዋና ምላሽ ሊሆን እንደሚችል አፅንዖት ሰጥተዋል።

አስፈላጊ ከሆኑ የደህንነት እርምጃዎች ጎን ለጎን የትምህርት ሥርዓትን ወጣቶች እንደ አዎንታዊነት እንዲያስቡት እና እንዲያደንቁት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

19 Jan 2026, 10:13