ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት 

በአሜሪካ እና በአውሮፓ መካከል ያለው ውጥረት ዓለም አቀፍ ግንኙነትን እያባባሰው መምጣቱ ተገለጸ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በአሜሪካ እና በአውሮፓ መካከል ያለውን ውጥረት በማስመልከት ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ብጹዕነታቸው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ “ክርክር ውስጥ ሳይገቡ እና ተጨማሪ ውጥረት ሳይፈጥሩ በአወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ መወያየት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን “ወጣቶችን ከመጭው ጊዜ ጋር ለማገናኘት የሚደረግ ዓለም አቀፍ ውይይት” በሚል ርዕሥ በሮም ረቡዕ ጥር 21/2018 ዓ. ም. በተካሄደው ስብሰባ ጎን ለጎን በአሜሪካ እና በአውሮፓ መካከል ያለውን ውጥረት በማስመልከት ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ አስድርገዋል።

“ውጥረቶች ጤናማ ካለመሆናቸው የተነሳ ቀድሞውኑ አስቸጋሪ የሆነውን የዓለም አቀፍ ሁኔታ የሚያባብሱ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ” ብለው፥ አስፈላጊው ነገር ወደ ክርክር ሳይገቡ እና ውጥረቶችን ሳያባብሱ በአወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ቀውስን በማስወገድ አምናለሁ” ብለዋል።

ብጹዕነታቸው ቃለ ምልልሳቸው ያደረጉት በሮም ቅዱስ አንጦንዮስ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለ25ኛ ዙር በተከበረው “የነፃ ሃሳብ ግምገማ” መታሰቢያ ላይ እንደሆነ ታውቋል።

ለጋዛ የሰላም ቦርድ የቀረበ ግብዣ

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን “ለጋዛ የሰላም ቦርድ” የቀረበውን ግብዣ በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በርካታ አገራት በጉዳዩ እንዲሳተፉ መጋበዛቸውን አስታውሰው፥

ጣሊያንም የቦርድ አባላትን ለመቀላቀል ወይም ላለመቀላቀል እያሰበች እንደምትገኝ መረጃው እንዳላቸው ተናግረው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ግብዣውን እንደተቀበሉት እና ጉዳዩን በአግባቡ ገምግሞ ምላሽ ለመስጠት የተወሰነ ጊዜን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕነታቸው የጋዛ የሰላም ቦርድን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ቅድስት መንበር በገንዘብ እንደማትሳተፍ እና ይህን ለማድረግ በማትችልበት ደረጃ እንደማትገኝ ገልጸው፥ ቫቲካን ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ መሆኗን በመጠቆም፥ ጥያቄው ኢኮኖሚያዊ እንደማይሆን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ሕግን ማክበር

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዳቮስ ባደረጉት ንግግር አውሮፓን እንደሚወዷት ነገር ግን እየወሰደች ያለውን አቅጣጫ እንደማይወዱ ገልጸው፥ ይህም የእርሳቸው አመለካከት እንደሆነ፥ ዋናው ነገር ዓለም አቀፍ ሕግን ማክበር እና ይህም “ከግል ስሜቶች ባሻገር አስፈላጊ እና ሕጋዊ ነጥብ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የፕሬስ ነፃነት እና በጋዜጠኝነት ላይ ያለ እምነት

ስለ ፕሬስ ነፃነት የተጠየቁ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “በሚዲያ ላይ እምነትን መጣል እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ ነገር ግን ፕሬስን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መጠቀምን ማረጋገጥ እኩል አስፈላጊ እንደሆነ፣ “ከመከፋፈል ወይም ከማውደም ይልቅ መገንባትን የሚፈልግ ሚዲያን በኃላፊነት መጠቀም አስፈላጊ ይመስለኛል” ብለዋል።

ውብ ሀገር ቬነዙዌላ

“ቬነዙዌላ ውብ ሀገር ናት” ያሉት ብጹዕነታቸው በመዲናዋ ካራካስ ሐዋርያዊ እንደራሴ ሆነው ለአራት ዓመታት በማገልገላቸው እጅግ እንደተደሰቱ ገልጸው፥ ወደ አገሪቱ በተላኩበት ወቅት ከፍተኛ የፖለቲካ ችግሮች እንደ ነበሩ፣ የአገሪቱ ካቶሊካዊ ጳጳሳት በፕሬዚዳንት ቻቬዝ የፖለቲካ አቅጣጫ ትችት ሲሰጡ ስለ ነበር በመካከላቸው ውጥረት ነግሦ እንደ ነበር አስታውሰዋል።

ቬነዙዌላ ዛሬ እርግጠኛ መሆን በማንችልበት አዲስ የፖለቲካ መስመር ላይ እንደምትገኝ እና በዚህ የተነሳ የወደፊቱን መተንበይ ከባድ እንደሆነ ተናግረው፥ ዋናው ነገር በቀውስ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ፍላጎት ምላሽ መስጠት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ኢራን እና “ሦስተኛው የዓለም ጦርነት”

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ቤተ ክርስቲያን ስለ ግጭቶች ያላትን አመለካከት በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ቀውስ በሕዝብ መካከል በቃላት የማይነገር ስቃይ እንደሚያመጣ ተናግረው፥ የቅድስት መንበር ትኩረት ከሁሉ በፊት በሰዎች ላይ እንደሆነ ገልጸው፥ “ማሰብ ያለብን ብዛት ሳይሆን ሕይወትን ነው” በማለት በኢራን ውስጥ የተደረጉ ተቃውሞዎችን በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ ሁኔታን ለመግለጽ የተጠቀሙበት፥ “በየቦታው አልፎ አልፎ የሚካሄዱ ሦስተኛው የዓለም ጦርነቶች” የሚለው አገላለጽ ትክክለኛ መሆኑን አምነዋል።

ስለ ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ስጋት አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “ቅድስት መንበር ዘወትር ትጥቅ ለማስፈታት እና ለጦር መሣሪያዎች ቅነሳ እንደምትሠራ ተናግረው፥ ምክንያቱም የጦር መሣሪያዎች ካሉ ጥቅም ላይ መዋላቸው የማይቀር በመሆኑ፥ ቅድስት መንበር የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች መጠቀምን ብቻ ሳይሆን ባለቤትነትም ከሥነ-ምግባር ውጭ መሆኑን እንደምትገነዘ ተናግረዋል።

የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የተፈጠረውን ግጭት መፍታት ለመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ቁልፍ እንደሆነ ተናግረው፥ ይህ አንዴ ከተፈታ ሌሎች ችግሮችም እንደሚፈቱ ያላቸው ተስፋ ገልጸው፥ ቅድስት መንበር ከሥስር ዓመታት ወዲህ ለፍልስጤም እውቅና መስጠቷን እና ቅድስት መንበር የምትደግፈው “ሁለት መንግሥታት” የሚል ይህ የመፍትሔ ሃሳብ ዛሬም ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

“በሁለት መንግሥታት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሕዝቦች” የሚለው ሃሳብ አሁንም ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው፥ ዋናው ስምምነት ላይ መድረስ እና ለፍልስጤም ሕዝብ ተስፋ መስጠት ነው" ብለዋል። በመጨረሻም በጋዛ የሰላም ቦርድ ምን እንደሚከሰት ለማወቅ መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረው፥  “ፍልስጤማውያን በአገራቸው ውስጥ በሰላም የመኖር መብትን የሚያረጋግጥ አካሄድ ማግኘት ያስፈልጋል” ብለዋል።

 

22 Jan 2026, 15:25