ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ፥ ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ፥ 

ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፥ “የክርስቲያኖች አንድነት ለዓለም የሰላም መሣሪያ ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አብያተ ክርስቲያናት የአንድነት ጎዳናን እንዲከተሉ በማለት ያቀረቡትን ጥሪ በማስመልከት በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ክርስቲያኖች ለአንድነታቸው እንዲጸልዩ የተመደበውን የጸሎት ሳምንት ከእሑድ ጥር 10-17/2018 ዓ. ም. በማክበር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ አንድነትን የመፈለግ ክርስቲያናዊ ተልዕኮ ትርጉም አብራርተዋል።

ለአንድነት የሚደረጉ ጥረቶችን እና ስለ ዓለም ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያቀረቡትን ጥሪ እንዲያብራሩ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፥ ይህን በተመለከተ አብያተ ክርስቲያናት ስላላቸው ሚና አፅንዖት ሰጥተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ኮክ በማብራሪያቸው “የክርስቲያኖች የአንድነት እንቅስቃሴ የኅብረተሰብ አለመግባባት የሚንጸባረቅበት ባይሆንም ነገር ግን ራሱ የአንድነት ምልክት በመሆን ኅብረተሰቡን ሊረዳ ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።

በልዩነት በተሞላ ዓለም ውስጥ የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ቢኖሩም በአንድ መንፈስ ለመኖር ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ “ክርስትና የተከፋፈለ ከሆነ ለኅብረተሰቡ ብዙ ሊያቀርብ አይችልም” ብለዋል።

ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች እንደጻፈው “በጥሪአችሁ መሠረት ለአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካል እና አንድ መንፈስ አለ” የሚለው የዘንድሮውን የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ጭብጥ ያዘጋጀችው የአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች የተገለጸ ሲሆን፥ “የጭብጡ ምርጫ እጅግ ምሳሌያዊ ነው” ሲሉ ብጹዕ ካርዲናል ኮክ ተናግረዋል።

“ይህ ቅዱስ ጳውሎስ አንድነትን በማስመልከት የጻፈው ጥልቅ ልመና ነው” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ “ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን መልዕክት በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ እንደጻፈው ስናስብ ለእሱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እናያለን” ብለዋል።

2030 ዓ. ም. (እ.አ.አ) የማሰላሰያ እንጂ የጊዜ ገደብ አይደለም

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2030 ዓ. ም. “Confessio Augustana” ወይም “የቅዱስ አጎስጢኖስ ኑዛዜ” 500ኛ ዓመት የሚከበር መሆኑን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፥ ዓመቱ የማሰላሰያ እንጂ ገደብ የተቀመጠበት አለመሆኑን አስረድተዋል።

“በክርስቲያኖች የአንድነት እንቅስቃሴ ውስጥ የጊዜ ገደቦችን አልጠቅስም” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ የጊዜ ገደብ የሚደነገገው በመንፈስ ቅዱስ እንጂ በእኛ አይደለም” ብለው፥ ይሁን እንጂ 2030 ዓ. ም. (እ.አ.አ) ክርስቲያኖች በመካከላቸው በቆየው መለያየት ላይ በማሰላሰል እንደገና የሚያጤኑበት ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል።

ማርቲን ሉተር ሁሉም የክርስትና እምነቶች እዲታደሱ የሚፈልግ ቢሆንም፥ የሃይማኖት ምሁሩ ዎልፍሃርት ፓነንበርግን የቤተ ክርስቲያን መከፋፈል የተሃድሶ እንቅስቃሴ ውድቀት እንደሆነ የተናገረውን ብጹዕ ካርዲናል ኮክ ጠቅሰው፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ቤተ ክርስቲያን እንጂ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አይፈልግም” ብለዋል።

የኒቂያ ጉባኤ አስፈላጊነት

በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ በማብራሪያቸው ማጠቃለያ፥ በቅርቡ 1,700ኛ ዓመቱን ያከበረውን የኒቂያ ጉባኤ ዘላቂ ጠቀሜታ አፅንዖት በመስጠት እንደተናገሩት፥ የኒቂያ ጉባኤ ዛሬም ጠቃሚ እንደሆነ በመግለጽ፥ “አንድነት የሚገኘው በጋራ እምነታችን ብቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

21 Jan 2026, 14:04