ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ዕረፍት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ሲመሩ ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ዕረፍት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ሲመሩ  

ካርዲናል ኮክ፥ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ የእግዚአብሔርን መልክ እንድንፈልግ ማስተማራቸውን ገለጹ

በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ ለቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ዕረፍት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያነት የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ መርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው በቫቲካን ውስጥ ባቀረቡት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ክርስቲያኖች በምድራዊ ሕይወታቸው ውስጥ የእግዚአብሔርን መልክ እንዲፈልጉ ምኞት የነበራቸው መሆኑን አስታውሰዋል።

“የዘላለም ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ያለው ከሆነ በምድራዊ ሕይወታችን ውስጥ ራሳችንን ለእርሱ ማዘጋጀት ተገቢ ነው” ሲሉ መናገራቸውንም አስታውሰዋል።

በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ዕረፍት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴን በቫቲካን ውስጥ ታኅሳስ 22/2018 ዓ. ም. አቅርበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ የክርስትና ሕይወት ዋና ዓላማ በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በራሳቸው ሕይወት በምሳሌያዊ መንገድ ማሳየታቸውን እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ እና ከእርሱ ጋር አንድነትን መመሥረት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

የእግዚአብሔርን መልክ መፈለግ

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ታኅሳስ 31/2022 ዓ. ም. ወደ ፈጣሪያቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

ብጹዕ ካርዲናል ኮክ በዕረፍታቸው ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ዘወትር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተገናኙ ቁጥር የእግዚአብሔርን መልክ ይፈልጉ እና ያገኙት እንደ ነበር ተናግረው፥ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱን በእርሳቸው በኩል ገልጦ እውነተኛውን መልክ አሳይቶአቸዋል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፥ “የናዝሬቱ ኢየሱስ” የተሰኙትን እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2007 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ውስጥ ባሳተሟቸው ሦስት ጥራዞች አማካይነት የእግዚአብሔርን መልክ ለማግኘት የግል ፍለጋ ማድረጋቸውን አክለዋል።

በመስዋ ዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ በርካታ ካኅናት እና ምዕመናን
በመስዋ ዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ በርካታ ካኅናት እና ምዕመናን

ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጻሜን ወደ አዲስ ጅምር ይለውጠዋል

ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፥ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በዓመቱ መጨረሻ ላይ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፥ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” የሚለውን የወንጌላዊው ዮሐንስ መቅድም እንዲነበብ ሐሳብ ማቅረቡን አስታውሰዋል።

በዚህ የወንጌል ምንባብ ላይ በማሰላሰል ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ይህ የወንጌል ምንባብ እጅግ ውብ እና ልብ የሚነካ እንደሆነ ገልጸው፥ “የክርስትና እምነት በዓመቱ የመጨረሻ ቀን ላይ የሰው ልጅ ሕይወት ምድራዊ ፍጻሜ ጨርሶ መጨረሻ ሳይሆን ነገር ግን አዲስ ጅምር እንደሆነ እና የአንድ ሰው ምድራዊ ሕይወት የመጨረሻ ቀን ከእግዚአብሔር ጋር የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ከ2005–2017 ዓ. ም. የጻፏቸው እና ነገር ግን ያልታተሙ ጥቅሶችን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ሞትን “የሁሉም የሰው ልጅ ግንኙነቶች መፍረስ፣ የፍቅር እና የወዳጅነት መጥፋት በሞት ተሞክሮ ውስጥ እጅግ አሳዛኝ እውነታ ነው” ሲሉ መግለጻቸውን አስታውሰዋል።

ሆኖም ግን ተስፋ የሚከፈተው በዚያ እንደሆነ በማስረዳት፥ ሙሉ በሙሉ beተተወ ቦታ ላይ እንደ አዲስ እንድንጀምር የሚያደርገን የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ እንደ ሆነ፥ እንደ አዲስ መጀመር የሚቻለው እግዚአብሔር በፍጹም ብቸኛ እና የሰው ልጅ ግንኙነቶች ላይ የራሱን ፍቅር ሲገልጽ ብቻ ነው” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ኮክ በመቀጠልም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 2/2010 ዓ. ም. በቱሪን የሚገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስ ከፈን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት አስተንቶ ላይ፥ “ፍቅር ወደ ሲኦል ወርዷል” በማለት ያቀረቡትን የአንድ መስመር ጽሑፍ አስታውሰዋል።

ይህም ከሕማማት ሳምንት ቅዳሜ ሥነ-ሥርዓት ጋር የተገናኘ ቃል ኪዳን እንደሆነ እና ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ፍቅሩን ወደ ሞት ሥፍራ በማምጣት በሞት መካከል ሕይወትን እንደሚሰጥ እና በምድራዊ ሕይወት መጨረሻ ላይ አዲስ ጅማሬን የሚያስጀምር መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት፥ የሕይወታቸው ፍጻሜ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መገኘት እንዲከናወን መጠየቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በቫቲካን ውስጥ የሚገኝ የር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ መካነ መቃብር
በቫቲካን ውስጥ የሚገኝ የር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ መካነ መቃብር   (@VATICAN MEDIA)

የእግዚአብሔር ቤዛነት በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ይፈጸማል

ይህ ሥራ የኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በመጨረሻው ቀን እያንዳንዱን የሰው ልጅ ሕይወት እንደሚነካ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“እንዲሁም በእያንዳንዱ ግለሰብ ሞት ውስጥ ይፈጸማል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሞት ሲገባ በፍቅሩ እሳት የሞትን መነጠል በማስወገድ ዛሬም ቢሆን ፍቅሩን ወደ ሰው ሞት ውስጥ በማምጣት ከእግዚአብሔር ጋር አዲስ ኅብረት ያስተዋውቃል” ሲሉ አስረድተዋል።

“ይህ እግዚአብሔር እንደ ስጦታ የሰጠን ዘላለማዊነት ነው” ሲሉ ካርዲናል ኮክ ተናግረው፥ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ላለው የማይጠፋ የፍቅር ግንኙነት የዘላለም ሕይወት ይገባናል” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ኮክ በመጨረሻም፥ ይህን ተስፋ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ከተጻፈው ከኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻ ጸሎት ጋር በማገናኘት፥ ኢየሱስ አብ እንዲያከብረው የጠየቀውን ጸሎት በመጥቀስ ስብከታቸውን ደምድመዋል።

እንደዚሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በእርግጥ ከዚህ ልመናቸው ጋር በዘላለም ሕይወትውስጥ በመቀላቀል በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መገኘት የሕይወታቸውን ፍጻሜ ለራሳቸው ይጠይቃሉ” ሲሉ፥ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ካርት ኮክ ተናግረዋል።

 

03 Jan 2026, 15:13