ፈልግ

የቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ጉዱላ ካቴድራል 800ኛ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ የቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ጉዱላ ካቴድራል 800ኛ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ 

ካርዲናል ፓሮሊን፥ “አውሮፓ ክርስቲያናዊ ድፍረትን በድጋሚ ልታገኝ ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በቤልጂየም መዲና ብራስልስ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ጉዱላ ካቴድራል 800ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ቃለ-ምዕዳን አሰምተዋል። ጥር 4/2018 ዓ. ም. በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በተከበረው በዓል ላይ ደካማነት እና አቅጣጫ ማጣት በሚታይበት የአውሮፓ መንፈሳዊነት ላይ በማትኮር ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ አውሮፓ ክርስቲያናዊ ድፍረትን በድጋሚ እንድታገኝ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ከታነጸ ስምንት መቶ ዓመታትን ባስቆጠረው ካቴድራል ውስጥ ለተሰበሰቡት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ምዕመናን እና የቤልጂየም ንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “የክርስትና እምነት ከታሪክ ውጭ ሳይሆን በውስጡ በሚገኙ ተጨባጭ ቦታዎች እና በእውነተኛ ማኅበረሰቦች በኩል የሚያድግ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ይህ የ13ኛው ክፍለ ዘመን የጎቲክ የሕንጻ መዋቅር ከመገንባቱ ከረጅም ጊዜ በፊት በቅዱስ ሚካኤል ስም የታነጸች ጸሎት ቤት እና የመካከለኛው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በብራስልስ ውስጥ ጥልቅ የክርስትና መሠረት እንደ ነበረ ይመሰክራል ብለዋል።

“ይህ አዝጋሚ ዕድገት በአንድ ቅጽበት ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይሆን ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በአደራ የተሰጠውን የሚቀበልበትን፣ የሚጠብቅበትን እና የሚጠቀምበትን የቤተ ክርስቲያንን አመሠራረት የሚያሳይ ነው” ሲሉ በማስገንዘብ፥ ካቴድራሉ ከስምንት መቶ ዓመታት በላይ የከተማዋን እና የአገሪቱን ክርስቲያናዊ ሕይወት አብሮ በመያዝ የዘመኑን ጥያቄዎች የሚመልስ እምነትን ያካተተ እንደሆነ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን መስዋዕተ ቅዳሴውን ሲመሩ
ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን መስዋዕተ ቅዳሴውን ሲመሩ

ቅዱሳን ሚካኤል እና ቅዱስ ጉዱላ ሁለት የቤተ ክርስቲያን  ምሳሌዎች

በብራስልስ ከተማ የሚገኘውት የቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ጉዱላ ካቴድራል የተመሠረተው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1226 ዓ. ም. ሲሆን፥ የብራባንት መስፍን ሄንሪ ዳግማዊ ፈረንሳይን እና ጀርመንን በሚያገናኙ መስቀለኛ መንገዶች ላይ ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት በወሰኑበት ጊዜ እንደ ነበር ይታወሳል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ሁለት የካቴድራሉ ባልደረባ ቅዱሳን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ጉዱላ ዛሬም በሚያስደንቅ ሁኔታ ጥንካሬን እና ማስተዋልን እንዲሁም ታማኝነትን በማስታወስ ጠቃሚ ተልዕኮ እንዳላቸው ገልጸው፥ አንድ ላይ በመሆን እውነትን እና አገልግሎትን፣ ጽኑነትን እና ገርነትን በኅብረት ለማቆየት የተጠራች ቤተ ክርስቲያን ገጽታን ያሳያሉ ብለዋል።

ብራስልስ እና የአውሮፓ ደካማነት

ለብዙ የአውሮፓ ኅብረት ተቋማት መኖሪያ የሆነው የብራስልስ ከተማ ግጭቶችን እና ልዩነቶችን በማስታረቅ ችሎታው የተገኘ ከተማ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ይሁን እንጂ አውሮፓ እራሷ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ እና ባሕላዊ በሆኑ ፍርሃቶች እና ስብራት የተነሳ ጥልቅ የድካም ወቅትን እያለፈች ትገኛለች” ብለዋል።

ዋጋ የሌላት ቤተ ክርስቲያን ናትን?

እንደ ሮበርት ሹማን፣ ኮንራድ አደናወር እና አልሲዴ ዴ ጋስፔሪ ያሉ ሰዎችን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ እነዚህ ሰዎች በጦርነቱ ወቅት የአውሮፓ የእርቅ መሐንዲሶች እንደ ነበሩ ገልጸው፥ የአውሮፓን ተቋማት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን እርስ በርስ የመተማመን ስሜት እንደገና መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

“በራስ አለመተማመን ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያንም ፈተና ነው” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ “ትልቁ አደጋዋ የቁጥር መቀነስ ሳይሆን አስፈላጊነቷን ማጣት ነው” ብለው፥ “የክርስትናን ምስክርነት የሚያዳክመው የቁጥር ማነስ ሳይሆን የወንጌላዊነት ድፍረት ማጣት ነው” ሲሉ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስጠንቅቀዋል፣

“ቤተ ክርስቲያን ከታሪክ በላይ አይደለችም፤ በቀላሉም ከታሪክ ጋር አትዋሃድም”  ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “የምትጓዘው፣ የምትለየው እና የምታገለግለው በታሪክ ውስጥ ሆና ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ለብራስልስ፣ ለቤልጂየም እና ለአውሮፓ የቀረበ ጸሎት

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በቃለ-ምዕዳናቸው ማጠቃለያ ባቀረቡት ጸሎት፥ ቤተ ክርስቲያንን፣ የብራስልስ ከተማን፣ ቤልጂየምን፣ አውሮፓን እና በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አደራ ሰጥተዋል።

ብጹዕነታቸው በመጨረሻም የቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ጉዱላ ካቴድራል ለሁሉም ሰው ክፍት በመሆን የኅብረት ቦታ ሆኖ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸው ይህም ፍትሃዊ፣ ኃላፊነት ያለው እና የተስፋ ህሊናን የሚጠብቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

 

13 Jan 2026, 15:43