ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የገና በዓል ባከበሩበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የገና በዓል ባከበሩበት ወቅት   (@Vatican Media)

በጎረጎሳዊያኑ 2025 ከ3 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ቫቲካንን መጎብኘታቸው ተነገረ

በተገባደደው የጎረጎሳዊያኑ ዓመት በቫቲካን እስከ ሚያዝያ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ከ250,000 የሚበልጡ ምዕመናን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እና የሥርዓተ ቅዳሴ የአምልኮ መርሃግብሮች ላይ መገኘታቸው የተነገረ ሲሆን፥ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የተካሄደውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ምርጫን ተከትሎ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን በተለያዩ መስዋዕተ ቅዳሴዎች እና ዝግጅቶች ላይ መሳተፋቸው ተገልጿል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው፣ በመንፈሳዊ ተግባራቸው እና በሉዓላዊነት ሚናቸው የሚያግዙ የሃይማኖት አባቶች እና የምዕመናን ቡድን ኃላፊ የተለቀቀው መረጃ እንደሚያሳየው በጎረጎሳዊያኑ 2025 ዓ.ም. በቫቲካን 3,176,620 ሰዎች በጳጳሳዊ ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እና የአምልኮ ሥርዓቶች ላይ የተገኙ ሲሆን፥ በቡድኑ ይፋ የሆነው አሃዝ የአጠቃላይ፣ የኢዮቤልዩ እና ልዩ ጳጳሳዊ ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ታዳሚዎችን ያጠቃልላል ተብሏል።

ከጥር እስከ ሚያዝያ 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በነፍስኄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የጤና መታወክ ምክንያት በቫቲካን ውስጥ የተካሄዱ ዝግጅቶች አነስተኛ የነበሩ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በእነዚህ ጊዜያት 262,820 ሰዎች ቫቲካንን መጎብኘታቸው፥ 60,500 ሰዎች በወቅቱ በተደረጉ በስምንቱ ሳምንታዊ ጠቅላላ እና የኢዩቤልዩ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ መገኘታቸው፣ 10,320 ሰዎች በልዩ ሳምንታዊ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ መገኘታቸው፣ 62,000 ምዕመናን በሥርዓተ ቅዳሴዎች እና 130,000 ምዕመናን በመልአከ እግዚያብሔር ጸሎት ላይ ተገኝተዋል ተብሏል።

ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መመረጥ በኋላ ቁጥሮች ምን ይላሉ?

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በግንቦት 8 ለርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ከተመረጡ በኋላ 2,913,800 ሰዎች ቫቲካንን መጎብኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ 1,069,000 ምዕመናን በ36ቱ ሳምንታዊ እና የኢዩቤልዩ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንዲሁም 148,300 ሰዎች በልዩ ሳምንታዊ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ መሳተፋቸው ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት 796,500 ሰዎች የአምልኮ ሥርዓቶችን መከታተላቸው፣ 900,000 የሚሆኑት ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚሰበሰቡ ምዕመናን ጋር በሚያቀርቡት ሳምንታዊ የመልአከ እግዚያብሔር ጸሎት መርሃ ግብር ላይ መገኘታቸው ተገልጿል።

በጥቅምት ወር በሁለቱም የአምልኮ በዓላት ወደ 200,000 የሚጠጉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን የተገኙ ሲሆን፥ በሳምንታዊ የኢዩቤልዩ እና ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ደግሞ ወደ 295,000 የሚደርሱ ምዕመናን መሳተፋቸው ተገልጿል።

 

 

 

02 Jan 2026, 15:53