ካርዲናል ሮላንዳስ ማሪካስ፥ “የእግዚአብሔር ልብ ዘወትር ክፍት ሆኖ ይቆያል” ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማሪካስ ሐሙስ ታኅሳስ 16/2018 ዓ. ም. በተፈጸመው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት በርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን ባደረጉት ንግግር፥ ምእመናን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ዘወትር ዝግጁዎች፣ ባልንጀራን ለመቀበል እና ይቅርታ ለማድረግ ዝግጁዎች እንዲሆኑ አደራ ብለው፥“ይህን ቅዱስ በር ስንዘጋ የማይጠፋ የአዲስ ሕይወት ምንጭ የሆነው እና ከሞተ የተነሣው የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ በእርሱ ተስፋ ለሚያደርጉ በሙሉ ዘወትር ክፍት እንደሆነ እናምናለን” ብለዋል።
ጥንታዊ እና ቅዱስ የሆነ ሥነ-ሥርዓት
በጽሞና ወደ ባዚልካው ቅዱስ በር በሚወስደው ደረጃ ላይ የወጡት ብጹዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማሪካስ፥ተንበርክከው ጸሎት ካደረሱ በኋላ የባዚሊካውን ዋና በር በይፋ ዘግተዋል። ሥነ-ሥርዓቱ የተከናወነው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ዘንድሮ ለአንድ ዓመት ሲከበር የቆየው የኢዮቤልዩ ዓመት ፍጻሜን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ታውቋል። ባዚሊካው ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ጉዝጓዝ እንደ ቅርስነት በክብር ተጠብቆ የሚገኝበት እንደሆነ ይታወቃል።
ራስን ለሌሎች ክፍት ማድረግ
“የእግዚአብሔር መለኮታዊ ጸጋ ዘወትር ክፍት ነው” ያሉት የባዚሊካ መሪ ብጹዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማሪካስ፥ የቅዱስ በር መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ቤተ ክርስቲያኒቱ ያወጀችው ልዩ የኢዮቤልዩ ጊዜ ማጠቃለያን የሚገልጽ እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ፥ “የእግዚአብሔር መሐሪ ልብ ዘወትር ክፍት ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ብጹዕነታቸው በማከልም ዘንድሮ የተከበረ የኢዮቤልዩ ዓመት የባዚሊካው መዘምራን የመሠረተበት 480ኛ ዓመት የሚከበርበት መሆኑን በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል።
“ዛሬ የባዚሊካው ቅዱስ በር ሲዘጋ ተመልክተናል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማሪካስ፥ “ነገር ግን አስፈላጊው የልባችን በር ነው” ሲሉ ገልጸው፥ የልባችን በር የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ዘወትር ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ፥ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለመቀበል ሰፊ እና ይቅር ለማለት እና ይቅርታ ለመጠየቅ ኃይል እንደሚያገኝ አስረድተዋል። በቅዱስ በር በኩል ማለፍ ስጦታ እንደ ነበር የገለጹት ብጹዕነታቸው፥ “ከዛሬ ጀምሮ ለሌሎች ክፍት መሆን የወደፊት ተልዕኳችን የተከበረ ተግባር እና የአመስጋኝነት መታሰቢያ እና ደፋር ተልዕኮ ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
በአንድ የኢዮቤልዩ ዓመት ሁለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት
ብጹዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማሪካስ፥ ሊጠናቀቅ የተቃረበውን የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት በማስልከት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳናቸው፥ የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተጀምሮ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መቀጠሉን አስታውሰዋል።
ሌላኛው እና ብቸኛው እንደ ጎርጎርሳውያኑ በ1700 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት 12ኛ ተከፍቶ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ክሌመንት 11ኛ የተጠናቀቀው እንደ ነበር አስታውሰው፥ “ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን የሐዋርያዊ አመራር ጊዜ የሚያልፍ ቢሆንም ነገር ግን እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን ፈጽሞ የማይተዋት መሆኑን እንገነዘባለን” ብለዋል።
ሰላም ማምጣት ይቻላል
ብጹዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማሪካስ በመቀጠልም “የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ሩቅ እንዳልሆነ፣ ሰላምን ማምጣት የሚቻል እንደሆነ፣ ምሕረትም ከኃጢአት የሚበልጥ መሆኑን ለመላው ዓለም እንደገና የሰበከችበት ጊዜ ነበር” ብለዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ፈለግ በመከተል፥ ተስፋ በቅዠት ወይም በሞኝነት የተሞላ ሳይሆን ይልቁንም አዳዲስ መንገዶችን የሚከፍት ተጨባጭ ኃይል፣ በፍቅር የሚደረግ ውሳኔ፣ በቃሉ እና በሥጋው መሳተፍ፣ ሌሊት እንኳን ሊያጠፋው የማይችል ብርሃን ነው” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።
ተስፋ ከመልካም አቀባበል ይወለዳል
በመሆኑም የኢዮቤልዩ ዓመት በፍጻሜው ወቅት የሚያውቁት ክስተት ሳይሆን ነገር ግን ቃሉን በጽሞና ካላዳመጡ ተስፋ ለወልድ ትኩረት እንድንሰጥ የቀረበ ግብዣ እንደ ነበር አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ማሪካስ አክለውም፥ ተስፋ የእግዚአብሔርን ቃል በደስታ ከመቀበር የሚወለድ መሆኑን ሁሉን ሰው ያስተማረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ሆነች፥ እግዚአብሔርን ወደ ሕይወት መቀበል፣ ሌሎች ሰዎችን እና መጻዒ ጊዜን ያለፍርሃት በደስታ መቀበል እግዚአብሔር ወደ ልባችን እንዲገባ የምናደርግበት፣ ምሕረትን እና እርቅን የምናደርግበት እና ወንድማማችነትን ማሳደግ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅዱስ ዓመትን ወደ ተጨባጭ ተግባር መተርጎም
ብጹዕ ካርዲናል ማሪካስ በመጨረሻም፣ የሮም ነዋሪዎች ጠባቂ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል እንዲሁም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የሌሎች በርካታ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ምድራዊ ቅሪቶች የሚገኝበት ጳጳሳዊ ባዚሊካ ምእመናን የኢዮቤልዩን ዓመትን አዲስ ጸሎት የሚያቀርቡበት፣ ለድሆች ተጨባጭ ትኩረት የሚሰጡበት፣ በቤተሰብ ውስጥ እርቅ፣ በሥራ ዘርፍ ቁርጠኝነት እና በማኅበረሰብ መካከል እርቅ የሚደረግበት እንዲያደርጉት አሳስበዋል። “ወንጌልን በእጆቿ የያዘች ቤተ ክርስቲያን በመሆን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በልባችን ውስጥ ለመያዝ ድፍረት ሊኖረን የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ድሆችን በጸሎት ማስታወስለ
በምእመናን ጸሎት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ወንጌልን ለአሕዛብ በማወጅ ተልዕኮዋ ታማኝ እንድትሆን፤ በቅዱስ በር በኩል ያለፉት ምዕመናን በተስፋ ታድሰው የጌታን ፍቅር እንዲመሰክሩ፤ እውነትን ለሚፈልጉ፣ ጨለማን፣ ጥርጣሬን እና ድካምን የሚያሸንፍ ብርሃንን፣ ቃልን እና ጥንካሬን በእግዚአብሔር እንዲያገኙ ጸሎት ቀርቧል። በባዚሊካው ለተገኙት ምዕመናንም በቀረበው ጸሎት ላይ ለድሆች አዲስ ትኩረት ለመስጠት ያለው ፍላጎት እንዲነሳሳ ጸሎቶች ቀርበዋል።
የሌሎች ባዚሊካዎች ቅዱስ በሮች መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት
በኢዮበልዩ የተስፋ ዓመት ማጠቃለያ ላይ የተዘጋው የመጀመሪያው በር በሮም የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር እንደ ነበር ታውቋል። ቀጥሎም ቅዳሜ ታኅሳስ 18/2018 ዓ. ም. ጠዋት የቅዱስ ዮሐንስ ላተራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር የመዝጋት ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል። በቀጣዩ ቀን ማለትም የቅዱስ ቤተሰብ ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት እሑድ ታኅሳስ 19/2018 ዓ. ም. የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር የሚዘጋ ሲሆን፥ ሁለቱን ሥነ-ሥርዓቶች የሚመሩት ብጹዕ ካርዲናል ባልዳሳሬ ሬይና እና ብጹዕ ካርዲናል ጄምስ ሚካኤል ሃርቪ እንደሚሆን ተገልጿል።
በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ማክሰኞ ታኅሳስ 28/2018 ዓ. ም. ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በብርሃነ ጥምቀቱ መታሰቢያ ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በርን እንደዘጉት የሥነ-ሥርዓቱ መርሃ ግብር አስታውቋል።