ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ ሬይና፥ “የኢዮቤልዩ ውርስ እርስ በርስ መቀራረብ ነው” ሲሉ ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር በሚዘጋበት በዛሬው ዕለት፥ እግዚአብሔር ለእኛ ስላሳየን የፍቅር ምልክቶች በሙሉ የምስጋና መዝሙርን እናቀርብለታለን” ብለው፥ “በልባችን ውስጥ ያለው የምሕረት እና የሰላም ምኞት ለሁሉም ሕዝቦች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ የባዚሊካው ቅዱስ በር የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት በተፈጸመበት ዕለት ቅዳሜ ታኅሳስ 18/2018 ዓ. ም. ጠዋት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን ተናግረው፥ የባዚሊካውን በር ከመዝጋታቸው በፊት በስግደት ጸሎት ላቀረቡ በኋላ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ምዕመናንም እጃቸውን በበሩ ላይ በመጫን ጸሎታቸውን አድርሰዋል።
እግዚአብሔርን ወደ ሮም ጎዳናዎች ማምጣት
በሮም የሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር የተከፈተው የቅዱስ ቤተሰብ በዓል በተከበረበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 29/2024 ዓ. ም. ሲሆን፥ የተዘጋውም የኢየሱስ ክርስቶስ የቅርብ ጓደኛ በሆነው ደቀ መዝሙር፣ ሐዋርያ እና ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ በዓል ላይ መሆኑን የቅዱስ በር መዝጊያን ተከትሎ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተናግረው፥ “ቅዱስ ዮሐንስ ኢየሱስን የሚከትል፣ ድምፁን የሚሰማ እና ጆሮውንም በደረቱ ላይ በማሳረፍ የሚያዳምጥ ነበር” ብለዋል።
የሮም ከተማ ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቲየሪን እና የከተማው የመንግሥት ተወካይ ላምቤርቶ ጃኒኒን ጨምሮ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ምዕመናን የቅዱስ ዮሐንስን ምሳሌ ተከትለው የእግዚአብሔር የምሕረት አገልጋዮች እንዲሆኑ ጋብዘው፥ ይህም እግዚአብሔር ብዙዎች ተስፋ ባጡባት ከተማ ውስጥ እርካታን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል” ሲሉ ካርዲናሉ ተናግረዋል።
ብጹዕነታቸው በቃለ-ምዕዳናቸው እንደገለጹት፥ በተጣለባቸው ሸክም፣ በሚደርስባቸው ሥቃይ እና በኢ-ፍትሃዊነት ምክንያት የሚጮሁ ሰዎችን ማድመት የማይችል ሰው የክርስትና እምነቱን በተጨባጭ እኖረዋለሁ ብሎ መናገር የማይችል መሆኑን አስረድተው፥ የአንድነት አለመኖር፤ ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች ትኩረትን አለመስጠት፤ የወንድማማችነት ስሜት አለምኖር፣ በቤተ ክኅነትም ብቻችን እንድንሆን የሚያደርግ፣ ቤተሰብ የሚፈርስበት፣ ግንኙነቶች የሚቋረጡበት፣ ትውልዶች የሚጋጩበት እና የፖለቲካ ተልዕኮን የማይከተል እና ፍትህ ማጣት፣ ይህ ሁሉ ሰው ራሱን የሚችልበት እኩል ዕድል እንዲኖር፣ ህልሞች እንዲሳኩ፣ ክብሩ እንዲጠበቅ፣ በሥራ ዘርፍ ፍትሃዊ ደሞዝ እንዲከፈል እና መኖሪያ ቤት እንዲያገኝ ለሚደረጉ ጥረቶች እንቅፋቶችን ማስወገድ ነው” ብለዋል።
ከተማዋን ለመለወጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ማሳደግ
ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ በመቀጠልም፥ በማየት እና በማሰብ መከልከል የብዙዎች ልብ በሚያዝንበት፣ ፍርድ በሚዛባበት፣ መረጃ ከእውነት ፍለጋ ጋር ያለውን ግንኙነት በጠፋበት እና ባሕልም ተዓማኒ አስተማሪዎች በሌሉበት ወቅት ላይ ይገኛል ብለው፥ ጠንካራው አስተሳሰብ በሚያሸንፍበት ዓለም ውስጥ ሰላም አለመኖሩን አፅንዖት ሰጥቷል። ይህ ሁሉ የትንቢት እጥረት እግዚአብሔርን ዝም እንዲል ያደርገዋል ሲሉ ተናግረው፥ ምእመናን ከእግዚ አብሔር ጋር እንዲገናኝ እና የሮም ከተማም በሁሉም ማኅበራዊ እና የመኖር ህልውና ደረጃዎች ልትለወጥ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
ሁሉን ሰው እንደ ወንድም እና እህት አድርጎ መቁጠር
“ይህም በልባቸው ውስጥ ከባድ ሸክሞችን የተሸከሙትን፣ በጎዳናዎቻችን ላይ ትተው የነበሩትን እና በቅዱስ በር ላይ የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚፈልጉትን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ምዕመናንን ያነሳሳ ተስፋ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ይህ ኢዮቤልዩ ዓመት ለእያንዳንዱ ምዕመን የሚሰጠው ትምህርት እንደሆነ አጥብቀው ተናግረው፥“የእግዚአብሔር አስደናቂ ቅርብነት ምስጢር የተገለጠበት ቅዱስ በር አሁን የሚዘጋ ቢሆንም፣ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ በኩል በማለፍ ምሕረትን ለመስጠት ማንኳኳቱን አያቁርጥም” ብለው፥ “ከሁሉም በላይ ጠላቶች የምንላቸውን ጨምሮ ሁሉንም እንደ ወንድምና እህት በማወቅ ባለን ችሎታ በዘመን መጨረሻ ላይ በፍቅር እንፈረድበታለን” ሲሉ ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ ተናግረዋል።
የሮም ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነትን የምታሳድግ ናት
“አሁን የሮም ሀገረ ስብከት አዲስ ዘመን በሚጀምርበት ወቅት የእግዚአብሔርን መገኘት የሚገልጽ፣ እርስ በርስ በመቀራረብ የእርሱ ቅርበት የሚመሰከርበት ቦታ እንዲሆን ጸሎቶቻችን እና ጥረቶቻችን አንድ ላይ እንሰብስብ” ሲሉ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዘንድሮ በመስከረም ወር ለሮም ሀገረ ስብከት ያስተላለፉትን መልዕክት የጠቀሱት ብጹዕነታቸው፥ ቤተ ክርስቲያን እና የሮም ከተማ በዚህ መንገድ ብቻ ወንጌልን ወደ ሕይወት ማምጣት የሚችሉ የሲኖዶሳዊነት ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ካርዲናል ባልዳዛሬ በኢዮቤልዩ በዓል የተባበሩትን በሙሉ አመስግነዋል
የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ ሬይና የመጨረሻ ቡራኬያቸውን ከመስጠታቸው በፊት፥ በኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት ለተሳተፉት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ያደረጉትን ድጋፍ በማስታወስ እንዲሁም በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቢተ ዋና ኃላፊ ለሆኑት እና የኢዮቤልዩ አስተባባሪ ለሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ሰላምታቸውን አቅርበዋል።
በዚህ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ውስጥ የሁሉን ሰው ደኅንነት ለመጠበቅ ለሠሩት የሲቪል እና የጦር ኃይል ባለሥልጣናት እና የቸርነታቸውን የገለጹትን እና በእንግዳ ተቀባይነት ያገለገሉ በርካታ የሀገረ ስብከቱን ምዕመናን አመስግነዋል።
የቤተ ክርስቲያንቅዱስ በር
በኢዮቤልዩ ታሪክ ውስጥ በቀኝ በኩል የሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባሲልካ ቅዱስ በር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1423 ዓ. ም. በተከበረው ቅዱስ ዓመት የተከፈተው የመጀመሪያው እንደ ነበር ይታወሳል።የበሩ መሻገር የኢዮቤልዩ ጉዞ ዋና ምልክት እንደሆነ እና ይህም የጸጋውን ስጦታ ለመቀበል በኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ በር ማለፍን የሚያመላክት መሆኑን ያስረዱት፥ አሁን ቅዱስ አጽማቸው በዋናው መሠዊያ ፊት ለፊት ባለው የኑዛዜ ክፍል ውስጥ የሚገኘው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማርቲን አምስተኛ እንደ ነበሩ ይታወሳል።
ሌሎች የቅዱስ በር የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቶች
የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር ከጳጳሳት ባሲሊካዎች መካከል በሁለተኛነት የተዘጋ ሲሆን፥ ብጹዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማሪካስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ቅዱስ በር በቀዳሚነት ሐሙስ ታኅሳስ 16/2018 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በጸሎት ሥነ-ሥርዓት መዝጋታቸው ታውቋል።
ቀጥሎም እሁድ ታህሳስ 19/2018 ዓ. ም. የቅድስት ቤተሰብ በዓል በተከበረበት ዕለት ብጹዕ ካርዲናል ጄምስ ሚካኤል ሃርቪ የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ቅዱስ በር በጸሎት ሥነ-ሥርዓት በሦስተኛ ደረጃ መዝጋታቸው ታውቋል።
በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ ታኅሳስ 28/2018 ዓ. ም. ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በብርሃነ ጥምቀቱ መታሰቢያ ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በርን የዘጉት መሆናቸውን የሥነ-ሥርዓቱ መርሃ ግብር አስታውቋል።