የሲኖዶሳዊነት ጉዞ የጥናት ቡድኖች ጊዜያዊ ሪፖርቶቻቸውን ይፋ አደረጉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሪፖርቶቹ ውስጥ የዲጂታል ተልዕኮ፣ የሴቶች ሚና በቤተ ክርስቲያን፣ የክርስቲያኖች አንድነት፣ ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት፣ የአምልኮ ሥርዓት፣ የቅድስት መንበር እንደራሴዎች አገልግሎት እና የጳጳሳት ምርጫን የሚመለከቱ ርዕሦች ይገኙበታል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትእዛዝ የተቋቋሙት እና ከሃያ ወራት በላይ ያስቆጠሩት እነዚህ አሥር የጥናት ቡድኖች ከቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና ከብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላላ ጽሕፈት ቤት ጋር የበለጠ ትብብር እንዲፈጥሩ የተጠየቁ እና ጊዜያዊ ሪፖርታቸውን “Interim Reports” ኅዳር 8/2018 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉ መሆናቸው ታውቋል።
የሁለት አዳዲስ የጥናት ቡድኖች መዋቀር
ሪፖርቶቹ የያዟቸው የተለያዩ ርዕሦች፥ የዲጂታል ተልዕኮ አገልግሎት፣ የሴቶች ተሳትፎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፤ በምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት እና በላቲን ሥርዓት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት፣ የክርስቲያኖች አንድነት፣ የቅድስት መንበር እንደራሴዎች ሚና፣ የብጹዓን ጳጳሳት ምርጫ፣ በተሻለ ሁኔታ እየታዩ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጉዳዮች እና በጦርነት ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሚሉት ይገኙባቸዋል።
ከሪፖርቶቹ ጎን ለጎን የሕገ-ቀኖና ኮሚሽን የሚያበረክታቸው አስተዋጽዖዎች እና የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም (SECAM) የገለጸው “ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት እና የአምልኮ ሥርዓት በሲኖዶሳዊነት ዕይታ” የሚሉት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡ ርዕሦች ናቸው። የመጨረሻዎቹ ሁለት ቡድኖች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንዲካተቱ የሚፈልጓቸው ሲሆኑ ሥራችውን የጀመሩ በሐምሌ ወር ውስጥ እንደ ነበር ታውቋል። የአምልኮ ሥርዓት በሲኖዶሳዊነት ዕይታ በሚለው ጥናቱን የሚያካሂደው ቡድን በቅርቡ የተመሠረተ ሲሆን ሌላኛው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ደንቦችን፣ የቤተ ክርስቲያን ምክር ቤቶች እና ልዩ ምክር ቤቶች ጉዳዮችን የሚመለከት እንደሆነ ታውቋል።
የመጨረሻ ሪፖርቶችን የማስረከቢያ የጊዜ ገደብ ማራዘም
ሁሉም የጥናት ቡድኖች አስተያየታቸውን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንዲያቀርቡ የተጠየቁት እስከ ሰኔ ወር 2017 ዓ. ም. መጨረሻ ድረስ እንደ ነበር ይታወሳል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕልፈት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ምርጫ እና ለሥራው ተጨማሪ ጊዜ የመስጠት አስፈላጊነት የጊዜ ገደቡን እንዲራዘም አድርጎታል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመጨረሻዎቹ ሪፖርቶች በተቻለ መጠን እስከ ታኅሳስ 22/2018 ዓ. ም. ድረስ እንዲቀርቡ መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች አንዳንድ ቡድኖች ሥራቸውን ለማጠናቀቅ መቃረባቸውን እና ሌሎች ደግሞ እስከሚቀጥሉት ወራት ድረስ የሚቀጥሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለው ግንኙነት
በምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት እና በላቲን ሥርዓት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት በማስመልከት የተዘጋጀ የመጀመሪያ ሪፖርት የጥናት ቡድን አባላት በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተመረጡ መሆናቸው ታውቋል። 25 ጥያቄዎችን፣ ሃሳቦችን እና አስተያየቶችን የያዘው መጠይቁ በመካከለኛው ምሥራቅ ካቶሊካዊ ፓትርያርኮች ምክር ቤት የተቀረፀ እና የጋራ ጥቅም ባላቸው ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የተወያየ የጥናት ቡድን አንድ የዝግጅት ሥራን የተመለከተ ሲሆን፥ ይህም ተዋረድ በሌለው በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን የዳያስፖራ ምዕመናን ላይ ብቻ ያተኮረ እንደሆነ ተመልክቷል። ቡድኑ ሊያዘጋጅ ካሰባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ሕገ ቀኖና ደንቦችን ማሻሻል ይገኝበታል።
የድሆች እና የምድር ጩኸት ማድመጥ
ከአምስት አኅጉራት የተውጣጡ አራት ገዳማውያት እና ሦስት ወንድ ምዕመናን የጥናት ቡድን ሁለት አባላት የድሆችን እና የምድርን ጩኸት በሚያዳምጥ ጭብጥ ላይ ሠርተዋል። ቡድኑ በርካታ የአውታረ መረብ ላይ ስብሰባዎችን እና የአገራት አብያተ ክርስቲያናትን በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በማነጋገር በርካታ ስብሰባዎችን ያካሄደ ሲሆን፥ እስካሁን በተዘጋጀው ሪፖርት የብጹዓን ጳጳሳትን፣ የነገረ መለኮት ሊቃውንትን እና የሐዋርያዊ ሠራተኞች አስተያየቶችን አሰባስቧል።
ቡድኑ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረትን በማማከር ከገዳማውያት ተቋማት ከ200 በላይ ሃሳቦችን መሰብሰቡ እና የአካል ጉዳተኞች በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከሚሳተፉበት የአውስትራሊያ ጳጳሳት ጉባኤ የአካል ጉዳተኞች ጽሕፈት ቤት ጋርም ተወያይቷል።
የመጨረሻው ሪፖርት በአሁኑ ጊዜ እየተዘጋጀ ሲሆን ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ የግብረ መልስ ዑደት ውስጥ እያንዳንዱ የቡድኑ አባል በትውልድ አህጉሩ ማኅበረሰቦች ድሆች ወይም የተገለሉ ሰዎች ጋር ለመሳተፍ ያለውን ቁርጠኛነት ገልጿል።
በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ያለው ተልዕኮ
ሲኖዶሱ ሲኖዶሳዊነትን በማስመልከት ላቀረበው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የጥናት ቡድን ሦስት ቤተ ክርስቲያን በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ያላትን ተልዕኮ በማስመልከት ያቀረበችውን ጥያቄ በመዳሰስ የተለያዩ አስተያየቶችን በትኩረት ማዳመጡ ታውቋል። ቡድኑ በተጨማሪም በቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት 84 የጳጳሳት ጉባኤዎች የመገናኛ ቢሮዎችን አማክሯል።
“ቤተ ክርስቲያን ታዳምጣለች” የሚለው ተነሳሽነት ተጀምሮ ከ67 አገሮች የመጡ 1,618 ዲጂታል ሚስዮናውያን ወጣቶች እና ከማኅበረሰቡ ተገልለው የሚኖሩ የዲጂታል የመገናኛ መሣሪያዎች የአጋርነት ተሞክሮዎችን ተመልክቷል። አባላቱ በዲጂታል አውዶች ውስጥ የሥነ-ምግባር እና የጾታዊ ጥቃት ጥበቃ ጉዳዮችን ያጎሉ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ጋር የተደረገ ውይይት አስፈላጊነትንም ተመልክቷል።
የጥናት ሂደቱን ለማሻሻል የተቋቋሙ ሦስት ጭብጦች ያሏቸው የሥራ ቡድኖች፥ ምሁራን፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት ባለሙያዎች፣ የዲጂታል አገልግሎት ዜደ ፈጣሪዎች እና ከ35 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችን ከሁሉም የዓለም ክፍል በማሰባሰብ በመጨረሻው ሪፖርት ላይ እየሠራ ይገኛል። ይህም በካቶሊክ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ኢዮቤልዩ ወቅት ከተገኙት ውጤቶች ጋር ተሻሽሎ ይቀርባል።
የክኅነት ምሥረታን መከለስ
ረጅሙ ጉዞ በጥናት ቡድን አራት ሪፖርት ላይ የተዘረዘረ ሲሆን፥ ይህም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 ዓ. ም. ለቀረበው የክህነት ተቋም መሠረታዊ መርህ የተሰጠ መሆኑ ታውቋል። አመለካከቱ የክኅነት ምሥረታ ሲኖዳላዊ ክለሳ ሲሆን ሆኖም አሁንም እየተቀበለው ያለ የቅርብ ጊዜ ሠነድ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሳዊነት እና ሚስዮናዊ ገጽታዎች ጋር የተያያዙ ጉልህ ሥራዎችን አስተዋውቋል። በአሁኑ ጊዜ ብሔራዊ የክኅነት ምሥረታ ሠነድ እየተዘጋጀ ሲሆን አንዳንዶቹ በቤተ ክኅነት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተረጋግጠው ሌሎች ደግሞ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
እንደዚሁም የጥናት ቡድን አራት ሪፖርት በአሁኑ የለውጥ ዘመን ውስጥ ተከታታይ ፍላጎቶች መኖራቸውን የሚያጎላ እና ይህም ችላ ሊባል የማይችል መሆኑ ታውቋል። ከእነዚህም መካከል “በእግዚአብሔር ሕዝብ ሕያው ተሞክሮ ውስጥ የበለጠ ሥር የሰደደ ምሥረታ አስፈላጊነት” የሚል ይገኝበታል። የጋራ ምሥረታ ጊዜያት ምዕመናንን፣ ገዳማውያትን እና ገዳማውያንን፣ የተቀቡ አገልጋዮችን እና የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎችን የሚያካትት እንዲሁም የተሾሙ አገልጋዮችን በማቋቋም ረገድ የሴቶችን እና የቤተሰቦችን የበለጠ ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደሆነ ታውቋል።
ይህ ሁሉ መሠረታዊ የመጀመሪያ ሠነድ በማዘጋጀት ዕድል ላይ እንድናስብ የሚያደርገን እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከጥቅምት 2024 ጀምሮ በሲኖዶሱ ውስጥ ተሳታፊዎች ያደረጓቸውን አስፈላጊ ማበረታቻዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ማኅበራዊ አውታረ መረቦችን፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ተግዳሮቶችን እና የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤቶች አወቃቀርን ያካትታል።
በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ
ከሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አመላካች ሃሳቦች ጋር በሚስማማ መልኩ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ከጥናት ቡድን አምስት ጋር የሚዛመድ፥ “በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና አመራር የሴቶች ተሳትፎ” በሚለው ልዩ ርዕሥ ላይ የመጨረሻውን ሪፖርት በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። የእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤቱ በርካታ አስተያየቶችን አሰባስቦ የገመገመ ሲሆን፥ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ እና አመራር ውስጥ ጉልህ በሆነ መልኩ የተሳተፉ የበርካታ ሴቶች አስተዋፅዖን ጋብዟል።
በተለይም የመጨረሻው ሪፖርት በሴቶች ሚና ላይ የተነሱ ዋና ዋና ግኝቶችን እና መስተጋብሮችን እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን አመራር ወይም በቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች ምስክርነቶችን በማካተት በቤተ ክርስቲያን ከሴቶችን ሚና ጋር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አስተዋጽኦ አካትቷል።
የሪፖርቱ የመጀመሪያ ረቂቅ ከጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አማካሪዎች ጋር በሐምሌ ወር 2025 ዓ. ም. (እ.አ.አ) ውይይት የተደረገበት ሲሆን፥ አስተዋጽኦቸው በሁለተኛው ክፍል ጥቅም ላይ እንደሚውል ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ሴት ዲያቆናት የጥናት ቡድን ሁለት የኮሚሽን ሥራን እንደገና ያበረታቱበትን ጉዳይን በተመለከተ “ጊዜያዊ ሪፖርቱ ከዚህ ርዕሥ ጋር የተያያዙ ሁሉም የሲኖዶሳዊነት አስተዋጽዖዎች ኮሚሽኑ እንዲመለከተው ተልኳል” ሲል ያስረዳል።
የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ የሥራውን የመጨረሻ ውጤት ያለምንም መዘግየት እንደሚያቀርብ ይጠብቃል።
በጳጳሳት፣ በመነኮሳት እና በመንፈሳዊ ማኅበራት መካከል ያለው ግንኙነት
የጥናት ቡድን 6 ሥራ በሦስት ጭብጥ ንዑስ ቡድኖች የተከፈለ ሲሆን፥ እነዚህም በጳጳሳት እና በመነኮሳት መካከል ያለውን ግንኙነት፣ በጳጳሳት ጉባኤዎች እና በገዳማውያት እና ገዳማውያን የበላይ አለቆች መካከል ያለውን ትብብር እና በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት እና በአገራት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግንኙነት ይተነተናሉ።
ጳጳሳት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ከዓለማችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ወንድ እና ሴት ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና ቀጥታ ልምዶች ላይ ተመሥርተው አመለካከታቸውን ተለዋውጠዋል።
ከውይይቶች፣ ከቃለ መጠይቆች እና ከጽሑፍ ጥያቄዎች በኋላ ንዑስ ቡድኑ የማጠቃለያ ሪፖርት ካዘጋጀ በኋላ የመጨረሻውን ሪፖርት ማዘጋጀት የጀመረ ሲሆን፥ በዚህ የመጨረሻ ደረጃ የገዳማውያን እና ገዳማውያት አለቆች አንድነት (UISG እና USG) እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ሪፖርቶች ይደመጣሉ።
ጳጳስ እና ሐዋርያዊ አገልግሎቱ
እጩ ጳጳስን ለመምረጥ የሚያግዙ መስፈርቶች በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙ ጳጳሳትን እና ምእመናንን በማሳተፍ፣ የጳጳሳት የመጀመሪያ እና ቀጣይነት ያለው ስልጠና፣ የሐዋርያዊ አባት የዳኝነት ተግባር፣ በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ወደ ሮም የሚደረግ የጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች አካሄድ እና ተግባር፥ እነዚህ በቅርብ ወራት ውስጥ ወደ 200 የሚጠጉ ግለሰቦችን ያዳመጠ የጥናት ቡድን 7 ሥራ መመሪያዎች ናቸው። ቡድኑ ሁለተኛው የሲኖዶስ ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ በየወሩ ሲገናኝ ቆይቷል።
የእጩ ጳጳስ ምርጫን በተመለከተ ቡድኑ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኩል በወቅቱ የብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ከነበሩት ካርዲናል ሮበርት ፍራንሲስ ፕሬቮስት ያገኘውን ሚስጥራዊ መመሪያዎችን ለሚመረምር በሐዋርያዊ ስልጣን ሥር በሚገኙ ግዛቶች የጳጳስ ሹመት ሂደትን ለሚመለከት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት እና ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ልኳል።
በቫቲካን በተካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት ቡድኑ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን ያቀረቡ 80 የሚያህሉ አባላትን አማክሯል። ቡድኑ በአንድ ወቅት በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ የሥራ አስፈፃሚዎችን በመምረጥ ረገድ በሲቪል ማኅበረሰብ ውስጥ ከሚተገበሩት ሂደቶች ጠቃሚ ግንዛቤዎችን በማግኘት ሪፖርት እንዲያቀርብ ተጋብዟል።
የብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤቶች ፕሬዚዳንቶች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካዮችን በቃለ መጠይቅ አስተያየታቸውን ጠይቀዋል። ወንድ እና ሴት ምዕመናን በጽሑፍ ምክራቸውን ለግሰዋል። ወደ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተላኩ 25 የሚያህሉ በፈቃደኝነት የተበረከቱ አስተያየቶች ተመርምረዋል።
ከዚህ ሰፊ ምክክር በኋላ ቡድኑ በተወሰኑ አመለካከቶች ላይ ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን፥ ለምሳሌ፣ ሕዝበ እግዚአብሔርን በማቋቋም ረገድ የበለጠ ጥረት እንዲደረግ እና በአገሮች ውስጥ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጳጳሳት ይበልጥ እንዲሳተፉ ጠይቋል።
የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴዎች ሚና
የጥናት ቡድን 8 የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ተወካዮች አገልግሎት በሚስዮናዊ እና በሲኖዳላዊ ዕይታ እንዴት ሊገለጥ እንደሚችል ምርምር የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቶታል። በዚህ ኃላፊነት በሮም በሚገኘው የሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ወይም በአውታረ-መረብ አማካይነት በርካታ ስብሰባዎችን አካሂዷል።
በመጀመሪያ በጥቅምት ወር 2024 (እ.አ.አ) በተካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ከተገኙት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዚዳንቶች ጋር ልዩ ስብሰባ ተካሂዷል። በስብሰባው ከተገኙት 61 አባላት መካከል 45ቱ የተሳተፉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከቡድኑ አባላት ጋር የግል ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ከዚያም ከዓለም ዙሪያ ከተላኩ 87 ተሳታፊዎች ጋር በሲኖዶሳዊነት ላይ ለመወያየት የአውታረ-መረብ ሴሚናር ተካሂዷል።
በካርዲናል ማርዮ ግሬች እና በሕንድ የቀድሞ የቦምቤይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የተፈረመ ደብዳቤ ለተለያዩ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዚዳንቶች የተላከ ሲሆን፥ ይህም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ እንደራሴዎች አገልግሎት ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ጋብዟል። በሌላ ተጨማር መልዕክት የቅድስት መንበር ዲፕሎማቶች የራሳቸውን ሃሳብ እና አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀዋል። በሁለቱም መንገዶች የተሰጡ ምላሾች አዎንታዊ እና ትልቅ ዋጋ ያላቸው እንደ ነበሩ ተመልክቷል።
ስለዚህ የአሁኑ ምዕራፍ ከጥናት ቡድኑ አባላት ጋር በመሆን የይዘት ማብራሪያ እና ትንተና የሚሰጥበት የማጋራት ደረጃ ነው። የተሳታፊዎችን ጂኦግራፊያዊ ርቀቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ የተወሰነ ጊዜን የሚወስድ ቢሆንም ነገር ግን የመጨረሻው ሪፖርት በመጭው ታኅሳስ 22/2018 ዓ. ም. እንደሚቀርብ ተጠይቋል።
የትኩረት አቅጣጫዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፥ ለቅድስት መንበር የድፕሎማሲ አካዳሚ እጩዎች የሚደረግ የምረጫ ሂደት እና ስልጠና፣ በአገልግሎት የመጀመሪያ ዓመታት ለዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት አባላት የሚደረግ ዕርዳታ፣ በቅድስት መንበር እንደራሴዎች መካከል የሚደረጉ የክልል ስብሰባዎች እና በጡረታቸው ጊዜ እንክብካቤ ማድረግን ይመለከታል።
አወዛጋቢ የሆኑ የዶክትሪን፣ የሐዋርያዊ እና የሥነ ምግባር ጉዳዮች
"የአስተሳሰብ ለውጥ እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ታማኝነት ላይ የተግባር ልምዶች መታደስ" የሚለው የጥናት ቡድን 9 በአወዛጋቢ የዶክትሪን፣ የሐዋርያዊ እና የሥነ ምግባር ጉዳዮች ላይ የተጀመረ የመነሻ ነጥብ ነበር።
እንዲሁም እንደ “ግብረ ሰዶማዊነት፣ ግጭት እና ዓመፅ የሌለበት የወንጌል ልምምድ እና በጦርነት ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት” የሚሉት አወዛጋቢ እና ይፋ እየወጡ የሚገኙ ጉዳዮችን አንስቷል።
ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው ዓላማው “ለሁሉም ጉዳዮች ተፈጻሚ የሚሆኑ መፍትሄዎችን መስጠት ሳይሆን የማጣቀሻ መስፈርቶችን ማቅረብ” መሆኑን ይገልጻል። አድማሱ "የሐዋርያዊነት መርህ ማለትም የሌላውን ተገዢነት ሳይገነዘቡ እና ሳያስተዋውቁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ማወጅ በማይቻልበት አመክንዮ እንዲሁም ለተባባሪው የእንግዳ ተቀባይነት እና የኃላፊነት አመለካከት የሚል አመክንዮ ነው።
የክርስቲያኖች የኅብረት ጉዞ
ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያን አንድነት ሁለት እርስ በርስ የተያያዙ ጭብጦች ናቸው። ከዚህ መርህ ጀምሮ የጥናት ቡድን 10 ሦስት ጉዳዮችን በማጣቀስ የኅብረት ጉዞ ፍሬዎችን ዳስሷል። ሲኖዶሳዊነት እና የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ቀዳሚነት፤ ቅዱስ ቁርባንን መሠረት ያደረገ እንግዳ ተቀባይነት፣ ለጥንዶች እና ቤተሰቦች ልዩ ትኩረት መስጠት፤ ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች እና በክርስቲያናዊ ተነሳሽነት የሚደረጉ የተሃድሶ ንቅናቄዎች መከሰት የሚሉ ናቸው።
ሥነ-መለኮታዊ እና ሐዋርያዊ ማዕቀፎች ከዳበሩ በኋላ ከክርስቲያን አንድነት ማበረታቻ መምሪያ ጋር ምክክር እየተደረገ ነው። እንደ ታይዜ፣ ቼሚን ኑፍ እና የፎኮላሪ እንቅስቃሴ ከመሳሰሉ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እና ከተለያዩ አህጉራት ከተውጣጡ የሃይማኖት ሊቃውንት ጋር መወያየትን ያካትታል።
ዋና ግቡ ለአካባቢ አብያተ ክርስቲያናት ተግባራዊ አቅጣጫዎችን ማዘጋጀት ሲሆን፥ ይህም ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ቅርፅ እና ወደ ሙሉ ተጨባጭ አንድነት የሚደረገውን የክርስቲያኖች የአንድነት ጉዞ ዕድገት አስተዋጽኦን ማድረግ ነው።
የአምልኮ ሥርዓት በሲኖዶሳዊነት እይታ
እንደተጠቀሰው ሌላው የጥናት ቡድን ተግባር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተሾመው እና ስለ አምልኮ ሥርዓት የሚናገር ሲሆን፥ ሥራውን ለመጀመሪያ ጊዜ እያቀረበ ይገኛል።
ከሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የመለኮታዊ አምልኮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የሚመራው ቡድን በቅዱስ ቁርባን አከባበር እና በቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሳዊነት ሚስዮናዊ ሕይወት መካከል ያለውን ግንኙነት ከመመልከት ጀምሮ ሥልጣኑን ያከናውናል።
ትኩረት ከሚሰጥባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል በተለይም ለሴቶች ሚና እውቅና መስጠት፣ የመድልዎ ዓይነቶችን መታገል የሚቀጥሉበት፣ ሴቶች በመዳን ታሪክ ውስጥ ያላቸውን ሚና በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ውስጥ ማጉላትን ጨምሮ እንዴት ማስተዋወቅ እንደሚቻል የሚገልጽ ይገኝበታል።
የሕገ ቀኖና ኮሚሽን
ከአሥሩ የጥናት ቡድኖች ጊዜያዊ ሪፖርቶች በተጨማሪ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 በተካሄደው የሲኖዶሱ የመጀመሪያ ስብሰባ ወቅት የተቋቋመው የሕገ-ቀኖና ኮሚሽንም ይገኛል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኮሚሽኑ ስምንት ጊዜ ተገናኝቶ የምእመናን ወይም የሴቶችን ጭብጦች፣ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች/ልዩ ምክር ቤቶች እና የተሳትፎ አካላትን አነጋግሮ በአሁኑ ሕግ ላይ የተደረገውን የማሻሻያ ሃሳብ ገምግሟል።
ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት
ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት የሚለውን በተመለከተ የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም (SECAM) የባለሙያዎች ቡድንን አቋቁሟል። ከደሴቶች እና ከክልሎች የተውጣጡ አሥራ ሁለት ባለሙያዎች፣ የሕገ-ቀኖና፣ የማኅበረሰቦች ባሕል እና ዕድገት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እና የሐዋርያዊ እንክብካቤ ባለሙያዎች፣ ከብዙ ጋብቻ ጋር በተያያዘ ሥነ-መለኮታዊ እና ሐዋርያዊ ማስተዋልን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል እና ወደ እምነት የሚመጡ ከአንድ ሚስት በላይ ያላቸውን ሰዎች እንዴት መደገፍ እንደሚቻል በማሰላሰል ላይ ይገኛሉ።
ተቀባይነትን ያገኘው ዘዴ በሦስት ደረጃዎች የተዘጋጀ ሲሆን፥ እነርሱም ማዳመጥ፣ ማድነቅ እና መሳተፍ” የሚሉት ናቸው። ዋና ዋና ጥያቄዎች፥ “በወንጌል መሠረት ከአንድ ሚስት በላይ ላላቸው ሰዎች ምን ዓይነት ሐዋርያዊ ምክር መስጠት ተገቢ ነው? ክርስቲያኖች ነጠላ ጋብቻን እንዲቀበሉ ለማድረግ ምን ዓይነት ሐዋርያዊ ድጋፎች መስጠት ይገባል?” የሚሉ ናቸው።
ቡድኑ በተጨማሪም አበረታች ምላሾችን እና ሊታዩ የሚገቡ የተወሰኑ ጉዳዮችን የያዘ እና የእምነት አስተምህሮ መምሪያን የሚጋራ የመጀመሪያ ሠነድ አዘጋጅቷል።
ጽሑፉ ተጨማሪ ክለሳ እየተደረገበት ሲሆን፥ በዚህ የተነሳ ወደ ብሔራዊ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሳይላክ ቆይቷል። ሆኖም ባለፈው ክረምት በኪጋሊ (ሩዋንዳ) በተካሄደው የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም (SECAM) ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ቀርቦ በጳጳሳት እና በሥነ-መለኮት ሊቃውንት ውይይት ተደርጎበታል።
የጥናት ቡድኖች ጊዜያዊ ሪፖርቶችን ሙሉ ጽሑፍ በሲኖዶስ ድረ ገጽ website ላይ ያንብቡ።