ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ  

የር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ጉብኝት በክርስቶስ መለኮታዊነት ላይ እምነትን ለማጎልበት እንደሚያግዝ ተገለጸ

በቱርክዬ የሚገኝ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እና ከቁስጥንጥንያው የክርስቲያኖች አንድነት ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ጋር ለማክበር እየጠበቀ እንደሚገኝ ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፥ ይህ የጋራ መታሰቢያ ለክርስቲያናዊ አንድነት ምስክር እንደሚሆን ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ ከተካሄደ 1,700 ዓመታት ቢያልፉም ጉባኤው እስከ ዛሬ ድረስ ጠቃሚ ሆኖ የቆየበትን ምክንያት የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ ለዚህም ሁለት ምክንያቶች እንዳሉት የመጀመሪያ፥ ጉባኤው በተካሄደበት እንደ ጎርጎሮሳያኑ በ325 ዓ. ም. የክርስትና እምነት በብዙ ክፍፍል እና መለያየት ገና ያልቆሰለ በመሆኑ እና ሁለተኛው፥ የክርስትና እምነት የተመሠረተው የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መሆኑ ክርስቲያኖችን በሙሉ የሚመለከት መታሰቢያ በመሆኑ በክርስቲያናዊ ኅብረት ሊከበር መታሰቡን ተናግረው፥ ይህን ማስታወስ እና በኅብረት እምነታችንን ማጠናከር የዚህ ክስተት ትልቅ ጥቅም እንደሆነ አስረድተዋል።


የክርስቶስ መለኮታዊነት ከክርስቲያኖች አንድነት ጋር ዛሬም ተዛማጅነት አለው

በጥንት ጊዜ በክርስቶስ መለኮታዊ ተፈጥሮ ላይ የነበሩ አለመግባባቶች አሁንም እንዳሉ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ ምንም እንኳን በክርስቲያኖች መካከል ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አንድነትን ማግኘት የሚቻለው በእምነት ብቻ መሆኑን ገልጸው፥ በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት ለእያንዳንዱ አዲስ የክርስቶስ አካል አባል በአደራ በሚሰጥ ሐዋርያዊ እምነት ውስጥ አንድነትን ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።

በእርግጥ የኒቂያው ጉባኤ እምነት የተመሠረተበት ትልቅ መሠረት እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ በኢየሱስ መለኮታዊነት ላይ እምነት የተሰጠው እንዲሁ ሳይሆን፥ ዛሬም ድረስ ጥያቄን የሚያነሳ በመሆኑ በጥልቀት መመልከቱ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ መሠረቱ እንደገና ሊጠናከር እንደሚችል ተናግረዋል።

ለዚህ ታላቅ የመታሰቢያ በዓል ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሆነ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ብዙ እንግዶች የተጋበዙ መሆናቸው ሲነገር፥ ዓላማው በተቻለ መጠን ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖር ማስቻል እንደሆነ ታውቋል።

በበዓሉ ላይ ማን እንደሚገኝ ወይም እንደማይገኝ አስቀድሞ ማረጋገጥ የሚቻል እንደሆነ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ በትክክል ማወቅ እንደማይቻል ተናግረው፥ በዚህ ረገድ የሐሰት ሪፖርቶችን ማሰራጨት እንደማይፈልጉ ገልጸው፥ የመታሰቢያ በዓሉ ዋና ዓላማ በተቻለ መጠን ብዙ ክርስቲያኖች እንዲገኙ ማድረግ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ፍላጎትም ይህ መሆኑን አፅንዖት መስጠት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

“በእርሱ ብቻ አንድ ነን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መሪ ቃል

ከጉባኤው መታሰቢያ ምን መልዕክት ማግኘት እንደሚፈልጉ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥በክርስትና እምነት ውስጥ አንድ መሆናችንን የሚያሳይ ምስክርነትን ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ ይህም “በእርሱ ብቻ አንድ ነን” ከሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ድንቅ መሪ ቃል ጋር እንደሚዛመድ አስረድተዋል።

ይህ ማለት ብዙ እና የተለያየን ብንሆንም ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነን ማለት እንደሆነ ገልጸው፥ቅዱስነታቸው ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የመረጡት መሪ ቃል ለክርስቲያኖች አንድነትም በእኩል እንደሚያገለግል አስረድተዋል።

በቫቲካን እና በክርስቲያኖች የአንድነት ጉዞ ውስጥ ያሳለፏቸውን ረጅም የሥራ ዓመታት መለስ ብለው በማየት በኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን እንዲገልጹ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥

በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ክስተት የኒቂያ ጉባኤ ከተካሄደበት ጊዜ ወዲህ ለ1,700 ዓመታት መላውን የክርስትና እምነት እንዴት እያንቀሳቀሰ እንደሚገኝ በማየታቸው እጅግ እንደተደሰቱ ገልጸው፥ በጉዳዩ ላይ በርካታ ስብሰባዎች መካሄዳቸውን በማስታወስ፥ ክርስትና በዚህ ጉባኤ ላይ እያሰላሰለ የጋራ እምነትን እያደሰ በመሆኑ እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑ ተናግረዋል።

“የርኅራኄ እና የአንድነት ሐዋርያዊ ጉብኝት”

ከቱርኪዬ በኋላ ሊባኖስን በመጎብኘት፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ምን ዓይነት ፍሬዎችን ለማየት ተስፋ እንደሚያደርጉ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥በእነዚህ አገራት ውስጥ ካሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቱርኪዬ እና በተለይም በሊባኖስ የሚያደርጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት በእርግጥ የርኅራኄ እና የአንድነት ጉብኝት እንደሚሆን እና አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የቱርኪዬ ክርስቲያኖች ማበረታቻ እንደሚሆን አስረድተዋል።   

በሊባኖስ ውስጥ ከሚገኝ ጠንካራ የማሮናይት ክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር በአስቸጋሪ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ልዩ ልዩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እንዳሉ ገልጸው፥ እነዚህን ማኅበረሰቦች ማጠናከር እና ማበረታታት የቅዱስነታቸው ዓላማ እንደሆነ፣ የክርስቲያኖች የአንድነት ውይይት፣ በሌሎች ሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት፣ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል የሚደረግ ውይይት በሊባኖስ ውስጥ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ከማሮናይት የክርስቲያን ማኅበረሰብ የተገኙ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሙስሊም እምነት የተገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 

25 Nov 2025, 15:34