የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መቃብር ጎበኙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ረቡዕ ጥቅምት 26/2018 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ወደ ሮም ከደረሱ በኋላ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ በሮም ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጳጳሳዊ ባዚሊካን ጎብኝተዋል።
የፍልስጤም ግዛት ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን ወደ ባዚሊካው ያጀቧቸው የቀድሞው የቅድስት አገር ተንከባካቢ ፍራንችስካዊ ካኅን አባ ኢብራሂም ፋልታስ ሲሆኑ በባዚሊካው ውስጥ ባደረጉት የአሥራ አምስት ደቂቃ ቆይታ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያላቸውን ክብር ለመግለጽ የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ
ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ይጠብቋቸው ለነበሩት ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መካነ መቃብር ለመጎብኘት የመጣሁት ለፍልስጤም እና ለፍልስጤም ሕዝብ ያደረጉትን መርሳት ባለመቻሌ እና ማንም ሰው ሳይጠይቃቸው ለፍልስጤም እውቅና መስጠታቸውን መርሳት ባለመቻሌ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ሐሙስ ጥቅምት 27/2018 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር በቫቲካን የተገናኙት በእስራኤል እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት በጋዛ ሰርጥ ተግባራዊ ከሆነ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ እንደሆነ ታውቋል።
በ2014 (እ.አ.አ) የተከናወነ የወይራ ዛፍ ተከላ
ከአሥራ አንድ ዓመታት በፊት ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ እና በወቅት የእስራኤል ፕሬዝዳንት ከነበሩት ሺሞን ፔሬስ ጋር በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ በተካሄደው ታሪካዊ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ በመሳተፍ የሰላም ምልክት የሆነውን የወይራ ዛፍ መትከላቸው እና በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቁስጥንጥኒያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ መገኘታቸው ይታወሳዋል።
ባለፉት ዓመታት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተደጋጋሚ የተገናኙት ማህሙድ አባስ፥ የሐማስ ታጣቂዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 7/2023 (እ.አ.አ) ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ እና እስራኤል በአጸፋ መላሽ በጋዛ ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ተደጋጋሚ የስልክ ግንኙነት አድርገዋል። የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅርብ ጊዜ ግንኙነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 12/2024 (እ.አ.አ) መካሄዱ ይታወሳል። ሁለቱም በጋዛ ውስጥ ያለውን ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት አስቸኳይ ፍላጎት እንዳላቸው ደግመው ደጋግመው በመናገር፥ የሁለት ሀገራት መፍትሄን በውይይት እና በዲፕሎማሲ በኩል ማሳካት እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተዋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ያደረጉት ግንኙነት
ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ 21/2025 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር በስልክ ያደረጉት ውይይት በጋዛ ግጭት እና በዌስት ባንክ በሚካሄደው ዓመፅ ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ይታወሳል።
በውይይቱ ወቅት ከቅድስት መንበር የፕሬስ ጽሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ እንደገለጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ሙሉ በሙሉ እንዲከበር ያቀረቡትን አቤቱታ በማደስ ሲቪሎችን እና ቅዱስ ቦታዎችን የመጠበቅ ግዴታን አፅንዖት ሰጥተው እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደረገውን የኃይል ጥቃት እና በግዳጅ ማፈናቀል አውግዘዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተመሳሳይ ጥሪ ሰኔ 26/2015 (እ.አ.አ) የተፈረመውን እና በጥር 2/2016 (እ.አ.አ) ተግባራዊ የሆነውን በቅድስት መንበር እና በፍልስጤም መንግሥት መካከል የተፈረመውን ጠቅላላ ስምምነት አሥረኛ ዓመት አስታውሰዋል።