ፈልግ

ለአረጋውያን የሚሰጥ እንክብካቤ እና የጤና አገልግሎት ዕርዳታ ለአረጋውያን የሚሰጥ እንክብካቤ እና የጤና አገልግሎት ዕርዳታ   (©Pixel-Shot - stock.adobe.com)

በአእምሮ ጤና ላይ የሚወያይ የተስፋ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጉባኤ በሮም እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገለጸ

ከመላው ዓለም የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሞክሮአቸውን የሚለዋወጡበት የሦስት ቀናት ዓለም አቀፍ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የተስፋ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጉባኤ በሮም እየተካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል። ከጥቅምት 26-28/2018 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደው ጉባኤ ዋና ዓላማ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ የአእምሮ ጤና አገልግሎትን ለማጠናከር እንደሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ይህ ‘የተስፋ ሐዋርያዊ አገልግሎት’ ጉባኤ፥ ከመላው ዓለም የተወጣጡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን፣ ባለሙያዎችን እና የሐዋርያዊ አገልግሎት ሠራተኞችን በማሰባሰብ ልምዳቸውን የሚለዋወጡበትን፣ በኅብረት የሚያሰላስሉበትን እና የሚጸልዩበትን መድረክ አዘጋጅቷል።

የሦስት ቀናት ጉባኤን በኅብረት ያዘጋጁት፥ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የአእምሮ ጤና አገልግሎት ማህበር እና በቫቲካን የሥነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ሲሆኑ፥ በሥነ-ልቦና፣ በማኅበራዊ እና በመንፈሳዊ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙት ግለሰቦች እና ማኅበረሰቦች የፈውስ አገልግሎት በሚሰጡት ባለሞያዎች መካከል መደማመጥን እና ትብብርን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።

ጉባኤው ከጦርነት፣ ከመፈናቀል እና ከማኅበራዊ ክፍፍል በተለየ ቤተ ክርስቲያን በእውቀት ላይ በተመሠረተ እምነት፣ ማኅበረሰብ እና ሐዋርያዊ እንክብካቤ ፈውስን እና ጽናትን ለማምጣት የሚያስችል ግንዛቤን ለመፍጠር እንደሆነ፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቱ ርህራሄ እና ዝግጁነት ሊኖረው እንደሚገባ፣ በመቀራረብ፣ በጠንካራ እውቀት እና በማስተዋል ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥቷል።

በቅዱስ ጴጥሮስ ‘ባዚሊካ’ አቅራቢያ ረቡዕ ጥቅምት 26/2018 ዓ. ም. በቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የተከፈተው ጉባኤ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የራስን ሕይወት ማጥፋትን መከላከል” በሚል ርዕሥ ለዚህ ወር ካዘጋጁት ወርሃዊ የጸሎት ሃሳብ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ታውቋል።

በጉባኤ ላይ ራስን ማጥፋትን ለመከላከል የሚደረጉ ሐዋርያዊ ጥረቶች ዙሪያ የሚቀርቡ አስተያየቶችን እና ምስክርነቶችን ለመጋራት የሚያግዝ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፥ ዓላማው ግንዛቤን እና የጋራ ጸሎትን ማሳደግ እንዲሁም ሕዝባዊ ተሳትፎን በኅብረት እና በምልጃ ለማቅረብ እንደሆነ ታውቋል።

ጉባኤው ካኅናትን፣ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን፣ በሐዋርያዊ አገለግሎት ሥራ ላይ የሚሳታፉ ምዕመናንን፣ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎችን እና ልምድ ያላቸውን ግለሰቦችን ጨምሮ በግምት 50 የሚሆኑ ሰዎችን እንደሚያሳትፍ ታውቋል።

ጉባኤው በተጨማሪም ከሙያዊ ግንዛቤ ጋር የተዛመዱ ሥነ-መለኮታዊ አስተንትኖዎችን፣ ነጻ ውይይቶችን፣ የጋራ ትምህርትን እና እንደ ግጭት ቀጠናዎች፣ በስደተኛ ማኅበረሰቦች፣ በትምህርት ቤቶች እና በቁምስናዎች  ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ የተግባር አቀራረቦች መጋራትን እንደሚያበረታታ ታውቋል።

በመጨረሻም፥ “በሰብዓዊ ቀውስ አውዶች ውስጥ የአእምሮ ጤና እና ሐዋርያዊ እንክብካቤ” በሚል ርዕሥ፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ አዲስ ሠነድ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ጉባኤው ጭንቀትን በመቋቋም አውዶች ውስጥ ሊዳሰሱ የሚገቡ ዋና ዋና ጭብጦች፥ በዛሬው ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ጂኦፖለቲካዊ እውነታዎች ውስጥ መከራን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ማወቅ፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት ልምዶች በቁምስናዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በማኅበረሰቦች ውስጥ የእርስ በርስ ግንኙነትን እና አብሮነትን እንዴት እንደሚያበረታቱ ማሰስ፣ የአእምሮ ጤና እውቀትን ከሐዋርያዊ የአገልግሎት ሕንጸት ጋር ማዋሃድ እና የሠራተኞችን ደህንነት ማረጋገጥ፤ እና በካቶሊካዊ ሥነ-መለኮት አኳያ በመንፈሳዊነት እና በሰው ልጅ ታሪክ የአእምሮ ደህንነት ትርጉም ላይ ማሰላሰልን እንደሚያካትት ታውቋል።

ይህ የተስፋ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጉባኤ ከሙያዊ የልምድ ልውውጥ ባሻገር የቤተ ክርስቲያኗን የእንክብካቤ ተልዕኮን ለማደስ የተነደፈ መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ጉባኤ እንደሆነም ታውቋል።

ጉባኤው ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለይም በብቸኝነት እና በተስፋ መቁረጥ በሚሰቃዩ ሰዎች መካከል መተማመንን፣ ሰብዓዊ ክብርን እና ኅብረትን ማጎልበት የምትችልበትን መንገድ ከማስገንዘብ በተጨማሪ ሠራተኞቹ በአገልግሎታቸው ውስጥ ሥነ ልቦናዊ ግንዛቤን ከመንፈሳዊነት ጋር ማዋሃድ የሚችሉ ሰዎችን በማዘጋጀት አስፈላጊነት ላይ እንደሚወያይ ታውቋል።

06 Nov 2025, 12:30