በሰው ሠራሽ አስተውሎት ‘AI’ እና በሕክምናው ዓለም ላይ የተካሄደ  ዓለም አቀፍ ጉባኤ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ‘AI’ እና በሕክምናው ዓለም ላይ የተካሄደ ዓለም አቀፍ ጉባኤ  

የሕክምና ባለሙያዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በጤና አጠባበቅ ላይ ውይይት አካሄዱ

“ሰው ሠራሽ አስተውሎት ‘AI’ እና የሕክምናው ዓለም፥ ሰብዓዊ ክብርን ያጋጠመ ፈተና” በሚል ርዕሥ በሮም የሕክምና ባለሙያዎች፣ ፈላስፋዎች እና የሃይማኖት ሊቃውንትን በያዝነው ሳምንት ውስጥ በቫቲካን ጉባኤ አካሂደዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጉባኤው ተሳታፊዎች፥ “ቴክኖሎጂን በሰው ልጅ በመተካት የሰውን ልጅ ቁሳዊ በሚያደርግ ፈተና ውስጥ መውደቅ የለብንብ ሲሉ” ተናግረዋል።

ይህ ርዕሥ ባለፉት ጥቂት ቀናት የሕክምና ባለሙያዎች “ሰው ሠራሽ አስተውሎት ‘AI’ እና በሕክምናው ዓለም ሰብዓዊ ክብርን ያጋጠመ ፈተና” በሚል በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከተነሱት ርዕሦች መካከል አንዱ ብቻ እንደ ነበር ታውቋል።

ከኅዳር 1-3/2018 ዓ. ም. የተካሄደውን ጉባኤ በጋራ ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ የካቶሊክ የሕክምና ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIAMC) እና በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ (PAV) መሆናቸው ታውቋል።

የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ አቡነ ሬንዞ ፔጎራሮ፣ የአካዳሚው አባል ፕሮፌሰር ቴሬዝ ሊሳውት እና የዓለም የሕክምና ማኅበር ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ኦትማር ክሎይበርን ጨምሮ አንዳንድ ተሳታፊዎች ከቅድስት መንበር የመግለጫ ክፍል ጋር ተነጋግረዋል።


ሃይማኖት እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ዕድገት

አቡነ ሬንዞ ፔጎራሮ የጉባኤውን ዓለም አቀፋዊነት በማስመልከት እንደተናገሩት፥ “ከሕንድ፣ ከላቲን አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከዩናይትድ ስቴትስ የተሰጡ አስተዋፅዖዎች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እና ተግዳሮቶችን እንድንረዳ ረድተውናል” ብለዋል።

አቡነ ሬንዞ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ሲናገሩ፥ “ጤናን እና ሕመምን ወደ ቁጥራዊ መረጃ የመቀየር አደጋ” እንዳለ አስጠንቅቀው፥ “ታካሚው ከፍርሃት እና ስሜቶች የተዋቀረ ውስብስብ የሕይወት ተሞክሮ ያለው ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“ሕክምናን የግል የማድረግ ችሎታ የማይተካ የጤና አጠባበቅ ክህሎት ነው” ያሉት አቡነ ሬንዞ፥ ቤተ ክርስቲያኗ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በሥነ-ምግባር አጠቃቀም ረገድ ስላላት ሚና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። “‘ቻትጂፒቲ’ ያሉ መሣሪያዎችን ወዲያውኑ ‘ጥሩ’ ወይም ‘መጥፎ’ ብሎ ማለት ሳይሆን እንዴት እንደሚሠሩ፥ ግልጽ፣ አድልዎ የሌለባቸው እና ነጻ መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል” ብለዋል።

ከታካሚው ጋር ያለውን የሰው ልጅ መስተጋብር ከመቀነስ መቆጠብ

የዓለም የሕክምና ማኅበር ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ኦትማር ክሎይበር፥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት “AI” በፍጥነት ወደ ሕክምናው ዓለም እየገባ መሆኑን በማስታወስ፥ ምርመራዎችን እና ሕክምናዎችን በማፋጠን፣ የበለጠ ትክክለኛ በማድረግ እና አንዳንድ ጊዜ የበለጠ የግል በማድረግ የሚሰጠውን ጥቅም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ የሚያስከትሉትን አደጋዎች በመግለጽ እንዳስጠነቀቁት፥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት “AI” ታካሚው ከሕክምና ባለሞያው ጋር ያለውን ግንኙነት ሊቀንስ እና የሕክምና ወጪዎችን መሸፈን ለማይችሉ ሰዎች ዝቅተኛ ዋጋ ያለውን እንክብካቤ የሚሰጥ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል፣ ቴክኖሎጂ የሰዎችን የሥራ ዕድልን በመቀማት ውጥረትን ሊጨምር እና አዳዲስ ማኅበራዊ አለመመጣጠን ሊያስከትል ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

ክሎይበር አክለውም፥ ዜጎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት “AI” መውሰድ ያለበትን አቅጣጫ በመወሰን ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ተናግረው፥ “እንደዚህ ያሉ ውይይቶች፣ ራዕዮች፣ አስተያየቶች፣ እምነት እና ተስፋ በሕክምናው ዓለም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ‘AI’ ለመጠቀም ለማቀድ እና ለመምራት ወሳኝ ጠቀሜታ አላቸው” ብለዋል።

ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ መሪዎች የሥነ-ምግባር ጥያቄዎችን ማቅረብ

የጳጳሳዊ አካዳሚው አባል ፕሮፌሰር ቴሬዝ ሊሳውት በንግግራቸው፥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት “AI” በሕይወት ሳይንስ እና በጤና አጠባበቅ ዕድገቶች (ባዮኤቲክስ) የሚነሱ የሥነ-ምግባር፣ የማኅበራዊ እና በሕግ ጉዳዮች ሁለገብ ዘርፍ ለሚሠሩ ካቶሊካዊ ምሁራን አዲስ እንደሆነ አስረድተዋል።

በባሕላዊ መልኩ የሕይወት ሳይንስ እና የጤና አጠባበቅ ዕድገቶች (ባዮኤቲክስ) ለልማት ምላሽ እንደሚሰጡ አስረድተው፥ ለሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ (PAV) ሥራ እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ እነዚህን ጉዳዮች በውይይት መካከል በማስገባት በሦስት የውይይት ቀናት ውስጥ የቀረቡ አዎንታዊ ገጽታዎችን መገምገም መቻላቸውን አስረድተዋል።

በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ውስጥ ያሉ አዎንታዊ ዕድገቶች ጉጉት እና አድናቆት መፍጠራቸውን አስተውለዋል።

ይህ አካሄድ በሕክምናው ዓለም አድናቆት ማግኘቱን ገልጸው፥ ሕንድ እና ካታሎኒያ ከመሳሰሉ አካባቢዎች የቀረቡ ሪፖርቶች ቴክኖሎጂዎች የጤና አጠባበቅን እንደሚያበረታቱ ማሳየታቸውን እና ይህም በመስኩ ላይ ለሚሠሩ ሰዎች ብዙ ተስፋ እንደሚሰጥ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ቴሬዝ ሊሳውት በመጨረሻም፥ ቴክኖሎጂን በሰው ልጅ በመተካት እና የሰው ልጅን ቁሳዊ አገልጋይ በማድረግ ዝንባሌ መካከል ላለው ውጥረት አፅንዖትን ሰጥተው፥ እነዚህን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ማወቅ እና በርዕሡ ላይ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

13 Nov 2025, 12:40