ፈልግ

ቅድስት መንበር የ2024 (እ.አ.አ) የፋይናንስ ዓመት ቅድስት መንበር የ2024 (እ.አ.አ) የፋይናንስ ዓመት  

ቅድስት መንበር የ2024 (እ.አ.አ) የፋይናንስ ዓመት በ1.6 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ መዝጋቷ ተገለጸ

በቅድስት መንበር የኢኮኖሚ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ወደፊት ሊረጋገጥ የሚችል የፋይናንስ ዕድገት መታየቱን የሚያሳይ የ2024 ዓ. ም. (እ.አ.አ) የፋይናንስ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የኢኮኖሚ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የ1.6 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ የሚያሳይ የ2024 ዓ. ም. (እ.አ.አ) የፋይናንስ መግለጫ አውጥቷል።

የዘንድሮ ውጤት ያለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ51.2 ሚሊዮን ዩሮ ቅናሽ ጋር ሲነጻጸር ጉልህ የሆነ ዕድገት የታየበት እንደሆነ ታውቋል።

ረቡዕ ኅዳር 17/2018 ዓ. ም. የታተመው ዓመታዊ ሪፖርቱ ግልጽ መሻሻል መታየቱን የሚያሳይ እና ወደ ሙሉ የፋይናንስ ዘላቂነት ለመድረስ ረጅም ጊዜን የሚጠይቅ ቢሆንም ግልጽ እና አዎንታዊ አቅጣጫ መያዙን አስተውሏል።

በፋይናንስ ዘርፍ የታየው ጠቅላላ መሻሻል የተመሠረተው 50% ገደማ በታየው ቅናሽ ከ83 ሚሊዮን ወደ 44 ሚሊዮን ዩሮ በመውረድ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

ይህ ሊሆን የቻለው በዋነኝነት ከልገሳዎች እና ከሆስፒታል አስተዳደር የሚገኙ ገቢዎች 79 ሚሊዮን ዩሮ ጭማሪ በማሳየቱ እና ወጪዎችን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ጥረቶች ሲሆን ይህም የዋጋ ግሽበትን እና የሠራተኞችን ወጪ በከፊል የሚሸፍን እንደሆነ ታውቋል።

በፋይናንስ አስተዳደር ውስጥ ያለው አፈጻጸም አዎንታዊ የነበረ ሲሆን፥ ይህም እስከ 46 ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ አዎንታዊ ገቢን ያስገኘ እና እንደ ጎርጎሮሳውያንኑ በ2023 ዓ. ም. ከታየው ከፍ በማለት የአሠራር ጉድለትን በመሸፈን ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

ይህ አፈፃፀም በዋናነት በኢንቨስትመንት ኮሚቴ እገዛ የተገኘውን የካፒታል ትርፍ በማስገኘቱ እንደ ሆነ ታውቋል።

የፋይናንስ ትንተና


ቅድስት መንበር የሆስፒታል አገልግሎት ገቢዎችን ሳይጨምር ዓመቱን በ18.7 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ መዝጋቷ ታውቋል።

ይህንን አሃዝ በመተርጎም ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት የሰጠው በቅድስት መንበር የኢኮኖሚ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት፥ ይህ መሻሻል በዋናነት በልገሳዎች መጨመር እና ከረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንቶች ሽያጭ ጋር የተያያዘው የኢንቨስትመንቶች የአንድ ጊዜ የሂሳብ ተፅእኖ ምክንያት ሲሆን፥ ታየ የተባለው ዕድገት በሚቀጥሉት ዓመታት መረጋገጥ እንዳለበት ተገልጿል።

ሐዋርያዊ ተልዕኮ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፈንዶች

በመጨረሻም የወጪ ዕቃዎችን በመተንተን በሐዋርያዊ ተልዕኮ እና በተጨባጭ የኢኮኖሚ አተገባበር መካከል ያለውን ወጥነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ተገልጿል።

የተለያዩ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ተግባራት የሐዋርያዊ ተልዕኮ ገጽታዎችን እንደሚያንጸባርቁ ተገልጿል።

እነዚህ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ወይም ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያገለግሉ ሲሆን፥ ለየአገራቱ ቤተ ክርስቲያናት ከሚሰጡት ድጋፎች ጀምሮ ለእምነት አንድነት ተነሳሽነቶች የሚያደርጉት ድጋፍ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክቶች ጀምሮ እስከ የሰው ልጅ ዕድገት እና ሰላም፣ ከሥርዓተ አምልኮ እስከ የቫቲካን ቅርሳ ቅርስ እንክብካቤ እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንደራሴ ጽሕፈት ቤቶች የሚያደርጓቸውን ድጋፎች ያካትታል።

ሪፖርቱ በተጨማሪም ለሐዋርያዊ ተልዕኮ እና ለጳጳሳዊ ፈንዶች (ሆስፒታሎችን ሳይጨምር) የተመደበውን 393.29 ሚሊዮን ዩሮ የተከፋፈሉባቸውን ዘርጎች በዝርዝር ይገልጻል።

ከእነዚህ ፈንዶች ውስጥ አብዛኛዎቹ (83%) ቅድሚያ በሚሰጣቸው አምስት ዘርፎች ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ታውቋል።

ከጠቅላላው 146.40 ሚሊዮን ዩሮ ውስጥ 37% የሚወክለው በችግር ውስጥ የሚገኙ አገራት ቤተ ክርስቲያናትን ለመደገፍ የተመደበ እና የተወሰኑት ደግሞ የወንጌል ሥርጭት አገልግሎቶችን ለመርዳት የተመደቡ መሆናቸው ታውቋል።

ሌሎች ዋና ተጠቃሽ የወጪ ዘርፎች፥ ለአምልኮ ሥርዓቶች እና ለወንጌል ምስክርነት (14%)፣ ለመልዕክት ልውውጥ (12%)፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤቶች (10%) እና ለበጎ አድራጎት አገልግሎቶች (10%) የሚደረጉ ወጭዎች መሆናቸው ታውቋል።

የተቀረው 17% ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት አደረጃጀት፣ ለታሪካዊ ሃብቶች እንክብካቤ እና ለትምህርት ተቋማት ልዩ ልዩ ተግባራትን የሚመደቡ ወጭዎችን የሚሸፍን መሆኑ ታውቋል።

 

27 Nov 2025, 17:01