ቅድስት መንበር በአየር ንብረት ቀውስ ውስጥ ለሰው ልጅ ገጽታ ትኩረት መስጠቷ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP30) የክልል እና የመንግሥታት መሪዎች ስንሰባቸውን ከጀመሩ ከአሥር ቀናት በኋላ የአየር ንብረት ሚኒስትሮች ሰኞ ኅዳር 8/2018 ዓ. ም. ወደ ቤሌም ሲደርሱ ሁለተኛ የፖለቲካ ምዕራፍ ውይይቱን ጀምሯል።
የቅድስት መንበር የልዑካን ቡድን መሪ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃምባቲስታ ዲኳትሮ ማክሰኞ ኅዳር 9/2018 ዓ. ም. መድረኩን ወስደው ቫቲካን ቅድሚያ የምትሰጥባቸውን ጉዳዮች በድጋሚ በማንሳት ንግግር አድርገዋል።
በብራዚል የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃምባቲስታ ዲኳትሮ ንግግራቸውን የጀመሩት ጥቅምት 28/2018 ዓ. ም. በመሪዎቹ ጉባኤ ወቅት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ለተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ COP30 ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ እንደሆነ ታውቋል።
“የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ በምድራችን ውስጥ የሁሉንም ሰው ሕይወት አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መናገራቸው ሲታወስ፥ በመሆኑም ዓለም አቀፍ ትብብር እና የተባበረ ባለብዙ ወገን ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ይህም የሕይወትን ቅድስና እና እግዚአብሔር ለእያንዳንዱን ሰው የሰጠውን ክብር እና የጋራ ጥቅምን ማዕከል እንደሚያደርግ መናገራቸው ይታወሳል።
ባለብዙ ወገንተኝነት እና ፍትሃዊ ሽግግር
በመቀጠል የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድን አራት ቁልፍ ጉዳዮችን ለጉባኤው የዘረዘሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃምባቲስታ፥ ይህም “ወደፊት የሚመለከት ተያያዥነት ያለው ባለብዙ ወገንተኝነት ነው” በማለት ጀምረዋል።
“የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር የለውም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃምባቲስታ፥ የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን በማስረዳት፥ ሥነ ምግባር ከአካባቢያዊ ፍላጎቶች በላይ መሸፈን በሚያስችል የሰዎችን ክብር ማክበር የሚችል ባለብዙ ወገን ስልት ብቻ ነው’ በማለት በዱባይ ከተካሄደው ሃያ ስምንተኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP28) ቀደም ብሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው ላይ የተናገሩትን አስታውሰዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. በተካሄደው በዚሁ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የፈረሙት ሀገራት የቅሪተ አካል ነዳጆችን ቀስ በቀስ ለማስወገድ የተስማሙበት እና ይህም በቅድስት መንበር የተደገፈ የኃይል ሽግግር ሲሆን፥ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው መዘዝ በዋናነት ድሆችን እና እጅግ ደካማ የሆኑትን እንደሚጎዳ በማስታወስ በፍትሃዊነት የተከናወነ እንደ ነበር ይታወሳል።
በግንባር ቀደምትነት ላይ የሚገኙ ሴቶች እና ልጃገረዶች
“በአየር ንብረት ቀውስ የሰው ልጅ ገጽታ” ላይ አፅንዖት የሰጡት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃምባቲስታ፥ የተባበሩት መንግሥታት በፆታዊ የእንክብካቤ እርምጃ እቅድ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን በተለይም በዓለም ደቡባዊ ክፍል የሚገኙት በአየር ንብረት ለውጥ ባልተመጣጠነ ሁኔታ የሚጎዱ መሆናቸውን እንደሚገነዘብ እና ይህንንም በመዋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ቅድስት መንበር ተስፋ እንደምታደርግ ተናግረዋል።
“አንድ ላይ የጋራ ቋንቋ እና ስምምነትን መፈለግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አፅንዖት የሰጡት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃምባቲስታ፥ “የራስ ወዳድነት ፍላጎቶችን ወደ ጎን በመተው ለአንድነት እና ለወደፊት ትውልዶች ያለውን ሃላፊነት ማስታወስ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
የትምህርት ሚና
በመጨረሻም “የአየር ንብረት ተግዳሮት ስፋትን በተመለከተ፥ ኢኮኖሚያዊ እና የአሠራር ሃይሎች መኖራቸው አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን በቂ አይደሉም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃምባቲስታ፥ “የፓሪስ ስምምነት ግቦችን ለማሳካት የፖለቲካ እና የቴክኒክ መፍትሄዎች አዳዲስ ዘላቂ የኑሮ መንገዶችን እና የፍጥረትን እንክብካቤ የሚያቀርብ የትምህርት ሂደትን ካላካተቱ በስተቀር ማሳካት አንችልም” ሲሉ ተናግረዋል።
“ግቦች መሳካታቸው፣ ተግዳሮቶች መፈታታቸው፣ የትግበራ ዘዴዎች መጠናከራቸው፣ ኪሳራ እና ጉዳት መወገዳቸው ዕድገትን ለማረጋገጥ የትምህርት ሚናን ማሳደግ ወሳኝ ነው” ሲሉ ያስረዱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃምባቲስታ፥ በቤሌም በተካሄደው ሁለተኛ ዙር የውሳኔ ሃሳቦች ወቅት ከትምህርት ጋር የተያያዙ ነገሮችን በብሔራዊ ደረጃ ከተወሰኑ አስተዋፅዖዎች (NDCs) ጋር ከብዙ አገሮች የተውጣጡ አበረታች ምልክቶችን በደስታ ተቀብለዋል።
የቅድስት መንበር የልዑካን ቡድን መሪ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃምባቲስታ ዲኳትሮ በማጠቃለያቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “እውነተኛ ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥ ሊካሄድ የሚችለው ወደ ልብ በመመለስ ብቻ ነው” በማለት አጥብቀው ማሳሰባቸውን በመጥቀስ ንግግራቸውን ደምድመዋል።