ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ በዓለም ካሉ ትላልቅ የስደተኞች መጠለያ ካፖችች መካከል አንዱን ጎበኙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ ከጥቅምት 22-25/2018 ዓ. ም. ባንግላዲሽን ጎብኝተው ከሊቀ ጳጳስ አቡነ ኬቨን ራንዳል እና በአገሪቱ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የፍትህ እና የሰላም ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከአባ ሊቶን ሁበርት ጎሜዝ ጋር ሆነው ወደ ኮክስ ባዛር - ኡኪያ ሮሂንጊያ የስደተኞች ካምፕ ተጉዘዋል።
ከትላልቅ የስደተኛ ካምፖች መካከል አንዱ የሆነው
ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ በሊቀ ጳጳስ አቡነ ላውሬንስ ሱብራታ ሃውላደር እና በመላው የ “ካሪታስ”-ባንግላዲሽ ቡድን አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፥ የልዑካን ቡድኑ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ” ሴቶችን፣ ልጆችን፣ ቤተሰቦችን እና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በማገልገል ላይ የሚታወቅ ጠንካራ ድርጅት በመሆኑ አገልግሎቱን የሚያበረክትበትን የኮክስ-ባዛር የስደተኞች መጠለያን ጎብኝቷል።
‘ካሪታስ-ባንግላዲሽ’ ከጤና፣ ከሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና ከመደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ዕድሎችን በመስጠት፥ የሥነ-ምኅዳር ለውጥ እና የልብስ ስፌት ሙያ ስልጠናዎችን ጨምሮ የተለያዩ እገዛዎችን ያደርጋል።
ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ በጉብኝታቸው ወቅት ከአንዳንድ ልጆች እና መምህራን እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር ተገናኝተው የጋራ ጊዜን በማሳለፍ አውደ ጥናቶችን በመጎብኘት በሃይማኖታዊ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
የኮክስ-ባዛር የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች መካከል አንዱ ሲሆን፥ በውስጡ ከ1,100,000 በላይ ሰዎችን እንደሚይዝ እና አብዛኛዎቹ ከማያንማር የመጡ የሮሂንጊያ ስደተኞች መሆናቸው ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ባንግላዲሽ የሮሂንጊያ ስደተኞችን የምትቀበል ሲሆን፥ ከ2017 (እ.አ.አ) ጀምሮ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ወደ አንድ ሚሊዮን መደረሱ እና ከእነዚህም ውስጥ 50% የሚሆኑት ለአካለ መጠን ያልደረሱ መሆናቸው ታውቋል።
የብጹዕነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች
ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ ከኮክስ-ባዛር ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ ወደ ዋና ከተማ ዳካ በመጓዝ ከባንግላዲሽ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤና ዘንድሮ ሃምሳኛ የአገልግሎት ዓመቱን ከሚያከብር የፍትህ እና የሰላም ጳጳሳዊ ኮሚሽን አባላት ጋር ተገናኝተው ከበዓሉ ቀናት በአንዱ ላይ ተሳትፈዋል።
በባንግላዲሽ ሞራንዳንጉርን፣ ሞዶንፑርን እና ናራያንጋንጅን የጎበኙት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ ለስደተኛ ክርስቲያን ቤተሰቦች ሐዋርያዊ እንክብካቤን እና ሥልጠናዎችን በሚሰጥ በፒተር ባባን ክሬዲት ዩኒየን ማዕከል ቆይታ ካደረጉ በኋላ እዚያው ከ600 ምዕመናን ጋር የስደተኞች ኢዮቤልዩ መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል።
ብጹዕነታቸው በሁሉም ነፍሳት ቀን በአገሪቱ ውስጥ ትልቁ በሆነው በቅዱስ መቁጠሪያ ቤተ ክርስቲያን 5,000 ከሚሆኑ ምዕመናን ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን ካሳረጉ በኋላ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የመካነ መቃብር ሥፍራ ዑደት አድርገዋል።