ልማት የሰዎችን እይታ ሲያጣ ወደ ቀውስ እንደሚያመራ ቅድስት መንበር አስታወቀች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቫቲካን የአገራት ጉዳዮች መምሪያ ምክትል ጸሐፊ ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዛሬ ዓለምን እያጋጠማት ያለውን የልማት ቀውስ ለማሸነፍ እና የበለጠ ወንድማማችነት እና ዘላቂ የወደፊት ሕይወት ለመገንባት በሚያስችል ዕድል በጋራ እንዲሠራ አበረታተዋል። ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ ጥሪያቸውን ያቀረቡት ማክሰኞ ጥቅምት 11/2018 ዓ. ም. በጄኔቫ በተካሄደው 16ኛ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት (UNCTAD) የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ሲሆን፥ “የወደፊት ዕጣ ፈንታን መቅረጽ፣ ለፍትሃዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማት የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን መነሳሳት” በሚለው የጉባኤው ጭብጥ ላይ በማተኮር እንደሆነ ታውቋል።
“ልማት የሰው ልጅን እይታ ሲያጣ ወደ ቀውስ ያመራል” ያሉት ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዚህ ወቅት ያለፍትሃዊነት እና ያለ ተሳትፎ ዕድገት፣ ያለ እውነተኛ ብልጽግና ሃብትን የማካበት ቀውስ እያጋጠመው እንደሆነ ገልጸዋል።
“ልማት ወደ አሃዞችና ጠቋሚዎች ብቻ ሊቀየር አይችልም” ያሉት ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ፥ ምክንያቱም ከሁሉም በላይ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ እና በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ክብርን መጠበቅ ስለሚገባ ነው” ብለው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን በመጥቀስ፥ “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድህነትን መዋቅራዊ መንስኤዎች ለመፍታት የበለጠ ቁርጠኝ መሆን አለበት” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ልማትን የሚያበረታቱ አንዳንድ ቁልፍ መንገዶች
በቫቲካን የውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የአገራት ጉዳዮች መምሪያ ምክትል ጸሐፊ ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ፥እውነተኛ የሆነ የተቀናጀ ልማትን ለማራመድ የጋራ ቁርጠኝነትን ለማሳደግ የሚያግዙ የተወሰኑ ቁልፍ ዘርፎች አጉልተው ሲገልጹ፥ “ሕይወትን መንከባከብ እና ለቅድስናው አክብሮት ማሳየት የእውነተኛ ልማት ማዕከል ናቸው” ብለዋል።
“ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ፥ የሃይማኖት ነፃነት ነው” ሲሉ የተናገሩት ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ፥ የሃይማኖት አክራሪነት የሃይማኖት ነፃነትን ሊነካ እንደሚችል አፅንዖት ሰጥተው፥ ነገር ግን በአገሮች ውስጥ የሚታይ የሃይማኖት ግድየለሽነት ወይም ሆን ብሎ የሚሰራጭ አምላክ የለሽ ርዕዮተ ዓለም የሰው ልጅ ዕድገትን ሊያደናቅፍ እንደሚችል ገልጸዋል።
የፋይናንስ ዘዴ እና የዕዳ ቅነሳ
ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ በመቀጠል፥ የልማት ቀውሱ ወደ ፊት ለማስኬድ የታሰቡትን መዋቅሮች እንደሚነካ ገልጸው፥ ይህም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ መሠረቶችን ጨምሮ አሁን ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚደረገው ጥረት እንደሚያደናቅፍ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የዕዳ ቀውሱ ታዳጊ አገሮችን በድህነት ውስጥ በማስገባት ዘላቂ ልማትን እንደሚያደናቅፍ ተናግረዋል። የዋና ፀሐፊው፥ የወለድ ክፍያዎች የሕዝብ ወጪን እያሳደጉ በመሆናቸው ተቀባይነት እንደሌላቸው በመግለጽ፥ በመጀመሪያ ለዕድገት የታሰቡ ብድሮች በብዙ አጋጣሚዎች የወደፊት ትውልዶች ተስፋን የሚያሟጥጡ ሆነዋል” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።
ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ፥ “አካባቢን ከሚያበላሹ የንግድ አለመመጣጠን እንዲሁም በተወሰኑ አገሮች ለረጅም ጊዜ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከመጠን በላይ ከመጠቀም የሚመነጭ የሥነ-ምህዳር ዕዳ ነው” ሲሉም ጠቅሰው፥ በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት አበዳሪ መንግሥታት ዕዳቸውን ለመክፈል የማይችሉ አገራት ዕዳን ይቅር እንዲሉ ቅድስት መንበር ጥሪ ማቅረቧን አስታውሰዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት “IA” ን በሚመለከት
ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ፥ የልማት ቀውስን የሚመለከት ሌላው ቁልፍ ዘርፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ፈጣን ዕድገት እንደሆነ ገልጸው፥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘላቂ ልማትን የማራመድ አቅም ቢኖረውም በኃላፊነት፣ በማስተዋል፣ በሥነ-ምግባር አስተዳደር እና በሰው ልጅ ላይ ያተኮሩ የቁጥጥር ማዕቀፎችን ይፈልጋል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ የሥራ ልምዱ የሆነው “አውቶማቲዝም” እና ማስመሰል የሰውን ክብር እንዲተካ መፍቀድ አይቻልም” ሲሉ አክለዋል።
በዓለም ዙሪያ ተስፋን ማለምለም
ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ በንግግራቸው፣ “የሞራል ድፍረት እና የተለየ አቅጣጫ የመውሰድ ውሳኔ” በመባል በሚታወቀው የኮንፈረንሱ ጭብጥ ላይ አፅንዖት ሰጥተው፥ እሱም ወቅታዊውን የብዙ ወገን ሥርዓት ቀውስ ለመጋፈጥ አስፈላጊ የሆነው የተስፋ ምላሽ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮንፈረንሱ ጭብጥ ላይ የተገለጹት፥ “ወደፊት”፣ “ለውጥ” እና “ልማት” የሚሉት ቃላት ለቅድስት መንበር በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት የተሻለ ዓለም እንዲገነቡ፣ ዓለም አቀፍ አለመመጣጠንን እንዲፈቱ እና ለእውነተኛ የሰው ልጅ ዕድገት መጣጣራቸውን እንዲቀጥሉበት የሚያበረታቱ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።
“ይህ ማለት የሰውን ልጅ የሚያስቀድም፥ እግዚአብሔር የሰጠውን ክብር የሚያከብር እና ኤኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሥነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ የደህንነት ገጽታዎችን በማዋሃድ የጋራ ጥቅምን የሚያራምድ ልማት ማለት ነው” ብለዋል።
በቫቲካን የውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የአገራት ጉዳዮች መምሪያ ምክትል ጸሐፊ ሞንሲኞር ዳንኤል ፓቾ፥ በዚህ ረገድ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት የሚኒስትሮች ጉባኤ (UNCTAD) ተግባር በሦስት መሠረታዊ አምዶች በኩል የተስፋ ምልክት ሆኖ በመቆም አንድነት እና ኃላፊነት የወደፊት ዕድልን ወደ መልካምነት ሊለውጥ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ፥ እያንዳንዱን ሰው በተለይም ድሃውን ማኅበረሰብ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ በሆነ እውነተኛ ሰብዓዊ ልማት ውስጥ እንደሚያሳተፍ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።