ፈልግ

የዓለም አቀፍ የወጣቶች አማካሪ ህብረት (IYAB) ወጣት አባላት የዓለም አቀፍ የወጣቶች አማካሪ ህብረት (IYAB) ወጣት አባላት 

ዓለም አቀፍ የወጣቶች አማካሪ ህብረት በቫቲካን ሊሰበሰብ እንደሆነ ተነገረ

ዓለም አቀፍ የወጣቶች አማካሪ ህብረት ወይም ‘ኢንተርናሽናል ዩዝ አድቫይዘሪ ቦዲ’ የተባለው የወጣቶች ህብረት ከጥቅምት 18 እስከ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በቅድስት መንበር የምዕመናን፣ የቤተሰብ እና የህይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተገናኝቶ በቤተክርስቲያን ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎን በሚዳስሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሊወያይ እንደሆነ ተገልጿል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ይህ በሮም ውስጥ በቅድስት መንበር የምዕመናን፣ የቤተሰብ እና የህይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች አማካሪ አካል (IYAB) የውይይት መድረክ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ የሚጠበቅ ሲሆን፥ የአማካሪ ህብረቱ የተቋቋመበት ዓላማ በተለያዩ የቤተክርስቲያኒቱ ተልዕኮ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የወጣቶችን አስተያየት ወደ ቅድስት መንበር ለማምጣት እንደሆነ ተገልጿል።

የውይይት ርዕሶች
ይህ ስብሰባ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ ከተካሄደው የመጀመሪያው ስብሰባ ቀጣይ ሲሆን፥ በወቅቱ የተሾሙትን የሁለተኛው የወጣቶች ቡድን አባላትን አንድ ላይ የሚያሰባስብ እንደሆነም ተነግሯል።

ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚህ ስብሰባ ከሚነሱት ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ እ.አ.አ. በ 2027 ዓ.ም. በሴኡል ለሚደረገው የዓለም ወጣቶች ቀን መደረግ ስላለባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ጀምሮ በቤተሰብ አውድ ውስጥ በወጣቶች የወንጌል አገልግሎት ላይ ማሰላሰል፣ የወጣቶች አገልግሎት እና የቤተሰብ አገልግሎት የሚገናኙበትን መንገዶች መፈለግ እና የድህረ ሲኖዶሱ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ የሆነው ‘የክርስቶስ ሕያውነት’ በዛሬው ማኅበራዊ አውድ ውስጥ ያለው ጠቀሜታ በሚሉት ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የስብሰባው ተሳታፊዎች የቦርጎ ላውዳቶ ሲ' መንደርን እንደሚጎበኙም ጭምር ተገልጿል።

‘ተሳትፎ፣ ሲኖዶሳዊነት እና ተልዕኮ’ የዚህ የውይይት መድረክ ዋና መሰረታዊ ነገሮች እንደሆኑ አዘጋጆቹ የገለጹ ሲሆን፥ በዚህ የውይይት መድረክ ለጽህፈት ቤቱ ተጨባጭ የአሠራር መስመሮችን የሚያቀርብ እውነተኛ አውደ ጥናት ለመፍጠር የሚያስችሉ እቅዶችን ለማዘጋጀት ሀሳቦችን እና ተግባራዊ ልምዶችን የሚያካፍሉ ቡድኖች እንደሚኖሩም ተገልጿል።

የማህበሩ እንቅስቃሴዎች
ማህበሩ እ.አ.አ. ከ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የሲኖዶሱ የወጣቶች ጉዳይ የመጨረሻ ሰነድ ያቀረበውን ግልጽ ጥያቄ ተከትሎ ከተለያዩ የዓለም ክልሎች እና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች፣ ማህበራት እና ማህበረሰቦች የተውጣጡ 20 ወጣቶች ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ተባባሪዎች በሮማን ኩሪያ አማካይነት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እያደረጉ እንደሆነ ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ከወጣቶች አገልግሎት ጋር የተያያዙ እና ሌሎች አጠቃላይ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሲኖዶሳዊ ዘይቤ እንደሚጠቀሙ የተገለጸ ሲሆን፥ ማህበሩ የወጣቶችን ድምጽ እንደመወከሉ መጠን ለቅድስት መንበር የምዕመናን፣ ቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንዲሁም ምክሩን ለሚጠይቁ ሌሎች ተቋማት በወጣቶች ስም በተለይም ለችግር የተጋለጡን፣ ድሆችን፣ በዳርቻ አከባቢ ተገለው የሚኖሩትን ወይም የትምህርት እና የሥራ እድሎችን የማግኘት ችግር ያለባቸውን ሁሉ በመወከል የምክር አገልግሎት እና ንቁ ድጋፍ እንደሚያቀርብ ተገልጿል።

28 Oct 2025, 13:17