ፈልግ

እውቁ ተዋናይ አርኖልድ ሽዋዜኔገር እውቁ ተዋናይ አርኖልድ ሽዋዜኔገር  

እውቁ ተዋናይ ሽዋዜኔገር ‘የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለአካባቢ ጥበቃ ለሚደረገው ንቅናቄ ወሳኝ ኃይል ነች' ማለቱ ተነገረ

በካስቴል ጋንዶልፎ ‘ለአየር ንብረት ፍትሕ ተስፋን ማዳበር’ በሚል ጭብጥ ከሚካሄደው ጉባኤ ቀደም ብሎ እውቁ የፊልም ተዋናይ አርኖልድ ሽዋዜኔገር ከቫቲካን ዜና ጋር በነበረው ቆይታ የጋራ ቤታችንን ለመፈወስ የሚያስችል የጋራ አቅም ስላላቸው 1.4 ቢሊዮን ካቶሊኮችን መድረስ የምትችለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳላት ተናግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከ1,000 በላይ የሚሆኑ የሀይማኖት መሪዎች፣ የአየር ንብረት ባለሙያዎች እና የፖለቲካ መሪዎች በካስቴል ጋንዶልፎ ከመስከረም 21 እስከ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ “ለአየር ንብረት ፍትህ ተስፋን ማዳበር” በሚል ጭብጥ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ እንደሚሰበሰቡ የተገለጸ ሲሆን፥ በዝግጅቱ ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለተፈጥሮ እንክብካቤ የምትሰጠውን ጥብቅና አንድ ደረጃ ከፍ ስላደረገው የነፍስኄር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክት የሆነው ‘ላውዳቶ ሲ’ 10ኛ ዓመት ይታወሳል ተብሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በጉባኤ መክፈቻው ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ከሚጠበቀው ከዚህ ጉባኤ አስቀድሞ የካሊፎርኒያ የቀድሞ አስተዳዳሪ እና የተርሚኔተር ፊልም ዋና ተዋናይ የሆነው አርኖልድ ሽዋዜኔገር የአካባቢን ጉዳዮችን በማስመልከት መንግሥትን እና ህዝባዊ እንቅስቃሴን አንድ ለማድረግ ስላደረገው ጥረት አስመልክቶ ከቫቲካን ዜና ጋር ውይይት አድርጓል።

ማክሰኞ ዕለት በቅድስት መንበር የጋዜጣዊ መግለጫ ጽህፈት ቤት ከተሰጠው አጠቃላይ መግለጫ ቀደም ብሎ “እግዚአብሔር ይሄንን ጉዳይ ለሌሎች ማስተላለፍ የምችልበትን ጸጋውን ሰጥቶኛል” ያለው ተዋናዩ፥ የተሻለ ዓለም እንዲኖር የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል የገባ ሲሆን፥ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 200,000 ደብሮች ውስጥ የሚገኙት 400,000 ካህናት በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ ካላቸው ለውጥ ለማምጣት “ታላቅ ኃይል” አላቸው ብሏል።

'እውነተኛ የተግባር ጀግኖች'
ሽዋዜኔገር ቫቲካን በዓለም ላይ ከካርበን ልቀት ነፃ የሆነች የመጀመሪያዋ ሀገር ለመሆን ያላትን ቁርጠኝነት አመስግኖ፥ ከንግግር ባሻገር ነገሮችን በተግባር የሚያሳዩ “እውነተኛ የተግባር ጀግኖች ናቸው” በማለት አወድሷል።

በዚህ የተፈጥሮ ጥበቃ እንቅስቃሴ ውስጥ መንግስት በጣም አስፈላጊ አካል መሆኑን የጠቀሰው ተዋናዩ፥ ነገር ግን መንግስት ብቻውን ሊሰራው እንደማይችል እና ሁሉም ባለድርሻ አካል ተሳትፎ እንዲያደርግ በማሳሰብ፥ “የአካባቢ ጥበቃ ሕጎች ኢኮኖሚውን ስለሚጎዱ ሊተገበሩ አይችሉም” ብለው ከሚተቹ ሰዎች አሻግረው እንዲመለከቱ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ካሊፎርኒያ ምንም እንኳን ጥብቅ የሆነ የአካባቢ ህጎች ቢኖሯትም እያደገ ያለ ኢኮኖሚ እንዳላት ያስታወሰው ተዋናዩ፥ ይህች የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት እንደ አንድ ሀገር ብትታይ ከዓለም አራተኛዋ ትልቁ የኢኮኖሚ ባለቤት ትሆናለች በማለት ገልጿል።

“እኔ ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ትልቅ እምነት አለኝ” ያለው ሽዋዜኔገር፥ ግልጽ የሆነ ራዕይ እና ግብ ካለ ይህን ማድረግ እንደሚቻል ገልፆ፥ ነገር ግን ለተስፋ ብቻ ከተሰራ ይህ ጥሩ ስልት እንዳልሆነ እና በጣም አስፈላጊው ጉዳይ ጠንካራ እቅድ ማውጣት እንደሆነ አመላክቷል።

'ለአየር ንብረት ፍትሕ ተስፋን መፍጠር'
በቅድስት መንበር የጋዜጣዊ መግለጫ ጽህፈት ቤት ውስጥ መግለጫ ከሰጡት መካከል ሽዋዜኔገርን ጨምሮ የቱቫሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር የሆኑት ማይና ታሊያ፣ በብራዚል የፖርቶ አሌግሬ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሃይሜ ስፔንገር፣ የላውዳቶ ሲ' ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎርና ጎልድ እንዲሁም የቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ፀሐፊ ሲስተር አሌሳንድራ ስሜሪሊ ይገኙበታል።

በካስቴል ጋንዶልፎ በሚካሄደው የሶስት ቀናት ጉባኤ ተሳታፊዎቹ ከሚያደርጉት ጥልቅ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ውይይቶች ጎን ለጎን የአየር ንብረት ተሟጋቾች ቁልፍ የሆኑ ንግግሮችን እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ማክሰኞ ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ሲስተር ስሜሪሊ በዓለም ዙሪያ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት፣ ደብሮች እና የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ህዝቡ ዘላቂ ሕይወት መምራት የሚችልበትን መንገድ ለማስተማር የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት አወድሰዋል።

“ለአየር ንብረት ፍትሕ ተስፋን ማዳበር” በሚል ጭብጥ የተዘጋጀው ጉባኤ የሚካሄድበት በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘው የላውዳቶ ሲ መንደር ቤተክርስቲያኗ እምነትን፣ ሥነ-ምህዳርን እና ባህልን እርስ በርስ ለማስተሳሰር ያላትን ተልዕኮ የሚያሳይ ተጨባጭ ምልክት እንደሆነ ተገልጿል።

“የላውዳቶ ሲ' አሥረኛው ዓመት ማስታወሻ ክብረ በዓል መድረሻ ግብ ሳይሆን አዲስ ጅምር ነው” ያሉት ሲስተር ስሜሪሊ፥ ያሉት ተግዳሮቶች እጅግ በጣም ብዙ እንደሆኑ ብናውቅም፥ ይህ ግን አዲስ ቁርጠኝነት እዲኖረን ያደርጋል ብለዋል።

የ 'ላውዳቶ ሲ 10' ጉባኤ
የላውዳቶ ሲ' ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሎርና ጎልድ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ለአየር ንብረት ፍትህ ተስፋን ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል ረቡዕ ዕለት በሚጀመረው ከፍተኛ ደረጃ ጉባኤ ላይ ወደ 1,000 የሚጠጉ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፥ ይህ ጉባኤ ህዳር ወር ላይ በብራዚል ከሚካሄደው የ COP30 የአየር ንብረት ጉባኤ ቀደም ብሎ ከአንድ ወር በፊት እንደተካሄ ገልጸው፥ የፖለቲካ መሪዎች ለመጪው ትውልድ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ በቂ እድገት እያሳዩ አይደለም ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን፣ ነገር ግን ‘በሄድንበት ሁሉ ተስፋ እንድናደርግ እና እንድንዘምር’ ያሳስቡናል ያሉት ጸሃፊዋ፥ በጣም ፈታኝ ጊዜ ውስጥ እንኳን ተስፋ እንደሚያሸንፍ እና ነገሮች ሊለወጡ እንደሚችሉ ማመን እንደሚገባ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. በ 2015 ዓ.ም. ባስተላለፉት በዚህ ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው ላይ ያለውን ራዕይ እና ተልዕኮ ለመፈጸም ሁሉም አካላት ፍላጎታቸውን በግልጽ እንዲያስቀምጡ ለመጋበዝ ‘ላውዳቶ ሲ 10” የተሰኘ ጉባኤ እንደሚካሄድ የላውዳቶ ሲ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጎልድ አስታውቀዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፍ አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን እንዳበረታታ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ አሁን የብፁዕነታቸውን ትሩፋት ለማስቀጠል ብሎም የእርሳቸውን አመራር እና ቁርጠኝነት ወደ ሥራቸው ለማምጣት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸው፥ “በሚቀጥሉት ዓመታት እርሳቸው በሰጡን አቅጣጫ መሰረት በሁሉም ቦታ ተስፋን በደስታ እና በቆራጥነት መንፈስ ለማሳደግ ተግተን እንሰራለን” ብለዋል።

01 Oct 2025, 14:19