ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፤ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፤  (ANSA)

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “የሰው ልጅን ለጉዳት መዳረግ እና ማዋረድ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ገለጹ

ሃማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ ውድመት የተጀመረበት ሁለተኛ ዓመት በማስመልከት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን የመገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ብጹዕነታቸው በቃለ ምልልሳቸው፥ “በጋዛ እየሆነ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ” በማለት ገልጸው፥ በዚህ ምክንያት በበርካታ አገራት ሰላማዊ ሰልፎች መቀስቀሳቸውን አስታውሰው በማከልም “ፀረ-ሴማዊነት መጥፋት ያለበት ‘ካንሰር’ ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሃማስ ታጣቂ ሃይል በእስራኤላውያን ላይ በፈጸመው የሽብር ጥቃት ምክንያት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ከፍተኛ ውድመትን ያደረሰ ጦርነት የተጀመረበት ሁለተኛ ዓመት እና ከዚያን ጊዜ ወዲህ የሆነውን በማስመልከት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን የመገናኛ ብዙሃን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

የሃማስ ታጣቂዎች ከሌሎች ደጋፊ የሚሊሻ ቡድኖች ጋር በመተባበር በሺህ በሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላውያን፣ ስደተኞች እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሽብር ጥቃት መፈጸማቸው፣ ብዙዎችን ማገታቸው ሰብዓዊነት የጎደለው እና መከላከል የማይቻል እንደ ነበር ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል። ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቆይ የ “ሲምቻት ቶራህ” በዓል ማጠቃለያን ለማክበር ዝግጅት ላይ በነበሩት ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና አረጋውያን ላይ የሃማስ ታጣቂዎች የፈጸሙት ግድያ እና የሽብር ጥቃት አረመኔያዊ እንደሆነ ተናግረው፥ ቡድኑ ለዚህ ጥቃት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊያቀርብ እንደማይችል ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ቅድስት መንበር ጥቃቱ እንደተፈጸመ ወዲያው ታጋቾች እንዲፈቱ መጠየቋን ገልጸው፥ በጥቃቱ ለተጎዱ ቤተሰቦች ያላትን ቅርበት በመግለጽ የተፈጸመውን ጥቃት በጽኑ ማውገዟን፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሰላም እና እርቅ እንዲወርድ ቤተ ክርስቲያን መጸለዩዋን እና አሁንም በመጸለይ ላይ እንደምትገኝ ተናግረው፥ “ይህ የጥላቻ እና የአመጽ አዙሪት ወደ ማይመለስበት አዘቅት ውስጥ ማስገባትን እንዲያበቃ እንጠይቃለን” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አሁንም በሃማስ እስር ቤት የሚገኙትን እስራኤላውያን ታጋቾችን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ በሁለት ዓመታት ውስጥ የተወሰኑት መሞታቸውን እና ሌሎች ደግሞ ከረጅም ጊዜ ድርድር በኋላ መለቀቃቸውን ተናግረው፥ ዋሻ ውስጥ ታስረው በረሃብ የሚሰቃዩ ሰዎች ምስልን ባዩ ጊዜ ማዘናቸውን ገልጸው፥ እነዚህን ታጋቾች መርሳት የማይቻል እና የማይገባ መሆኑን አስረድተዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሕይወታቸው የመጨረሻ አንድ ዓመት ተኩል ላይ ከ21 ያላነሱ ታጋቾች እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረባቸውን እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የእርሳቸው ተተኪ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ አሥራ አራተኛ እነዚህን አቤቱታዎች ማቅረብ መቀጠላቸውን አስረድተዋል። በስቃይ ላይ የሚገኙትን በሙሉ በየዕለቱ በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው እና ከሁሉም ጋር ያላቸውን ቅርበት ገልጸው፥ እነዚህ ታጋቾች ከሚወዷቸው ዘመዶቻቸው ጋር በሕይወት እንዲገናኙ የሚቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ እንዲሁም ቢያንስ የተገደሉት ሰዎች አስከሬን በሥነ-ሥርዓት እንዲቀበር ለማድረግ ሙሉ ድጋፍ ማቅረብ መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።

“ዛሬ በጋዛ ያለው ሁኔታ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው የበለጠ አሳሳቢ እና አሳዛኝ እየሆነ በመምጣት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ አውዳሚ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ወደ ማመዛዘን ስሜትን ለመመለስ፣ የጥላቻ እና የቂም በቀልን ጭፍን አመክንዮ በመቀበል ሁከትን እንደ መፍትሄ መቀበል የለብንም” ብለዋል። ጥቃት የሚደርስባቸው ሰዎች እራሳቸውን የመከላከል መብት እንዳላቸው የተናገሩት ብጹዕነታቻው፥ ነገር ግን ሕጋዊ መከላከል ቢሆንም የተመጣጠነ መርህን ማክበር እንዳለበት ገልጸው፥ “እንደ አለመታደል ሆኖ የተቀሰቀሰው ጦርነት አስከፊ እና ኢ-ሰብዓዊ መዘዞችን አስከትሏል” ብለዋል። በፍልስጤም በየዕለቱ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በደርዘን የሚቆጠር እና አንዳንዴም በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደሆኑ አስረድተዋል።

የበርካታ ሕጻናት ስህተት በጋዛ መወለዳቸው እስኪመስል ድረስ ብዙ ልጆች በጦርነቱ መገደላቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ይህም እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። ለዚህ ሁሉ እልቂት ዝንጉ የመሆን አደጋ መኖሩን የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ “ሰዎች ቁራሽ እንጀራ ለማግኘት ሲሞክሩ የተገደሉ፣ በቤታቸው ፍርስራሽ ሥር የተቀበሩ፣ በሆስፒታሎች፣ ከድንኳን በተሠሩ ካምፖች ውስጥ እያሉ በቦምብ የተገደሉ፣ የተፈናቀሉ እና ከዚያች ጠባብ እና የተጨናነቀች አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሄዱ የተገደዱ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው፥ የሰውን ልጅ ይህን ለመሰለ የጋራ ጉዳት መዳረጉ እና መዋረዱ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በብዙ የዓለም ክፍሎች እየተስፋፉ የመጡ የፀረ-ሴማዊነት ክስተቶችን በማስመልከት ሲናገሩ፥ የሚያሳዝን እና እኩል ያልሆኑ መዘዞች መሆናቸውን ገልጸው፥ “ዛሬ የምንኖረው የሐሰት ዜናዎች እና የተጋነኑ ትረካዎች ባሉበት ዓለም ውስጥ ነው” ብለዋል። እነዚህን የተዛቡ መረጃዎችን የሚቀበሉ ሰዎች በጋዛ ውስጥ ለሚፈጠረው ነገር በሙሉ የአይሁድ ሕዝብ ሃላፊነት እንዲወስድ የሚጠይቁ እንደሚያደርጋቸዋል ተናግረው፥ ነገር ግን ያ እውነት እንዳልሆነ አስረድተዋል። በአሁኑ ጊዜ ያለው የእስራኤል መንግሥት በጋዛ እና በተቀረው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ እየተሠራ ያለውን በመቃወም ብዙ ጠንካራ የተቃውሞ ድምጾች ከአይሁዶች ዓለም መነሳታቸውን ገልጸው፥ “ብዙውን ጊዜ የእነዚህ ዓመፀኛ የሕገ ወጥ ሠፋሪዎች መስፋፋት የፍልስጤም መንግሥት እንዳይመሠረት ለማድረግ መፈለጋቸውን መርሳት የለብንም” ብለው፥ “የታጋቾች ቤተሰቦች የአደባባይ ምስክርነት ተመልክተናል” ብለዋል። ፀረ-ሴማዊነት መዋጋት እና መጥፋት ያለበት አደገኛ እንቅስቃሴ መሆኑን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ “በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች፣ እንድንገነዘብ የሚረዱን አስተማሪዎች እና ከሁሉም በላይ ከልብ እንድንገነዘብ የሚረዱን አስተማሪዎች ያስፈልጉናል” ብለዋል።

“በአውሮፓ እምብርት በአይሁዶች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት መርሳት የለብንም” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ ይህ ክፋት ዳግም እንዳይከሰት ኃይላችንን ማስተባበር ይገባል” ብለዋል። እንደዚሁም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እና የሕግ ጥሰቶች በፍፁም ትክክል እንዳልሆኑ ማረጋገጥ እንደሚገባ የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ “ማንኛውም አይሁዳዊ አይሁዳዊ በመሆኑ ብቻ ጥቃት ሊደርስበት ወይም ሊገለል እንደማይገባ ሁሉ እንዲሁም የትኛውም ፍልስጤማዊ ፍልስጤማዊ በመሆኑ ብቻ ጥቃት ሊደርስበት ወይም ሊገለል አይገባም” ብለዋል። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ “አሸባሪ ሊሆኑ የሚችሉት ፍልስጤማውያን ናቸው” የሚባለውን በማስታወስ፥ ጠማማ የሆነ የጥላቻ ሰንሰለት ወደየትም ሳይሆን ጥላቻን በመቀስቀስ ወደ ክፋት ብቻ እንደሚመራ ተናግረው፥ “የሕይወት አስተማሪ ሆኖ ከሚቀር ከቅርብ ጊዜ ታሪክ እንኳን መማር አለመቻልን ማየት ያማል” ሲሉ አስረድተዋል።

ጦርነቱ እንዳይቆም የሚከለክሉ ብዙ ፍላጎቶች መኖራቸውን የጠቀሱት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ የእስራኤል ጦር የሐማስ ታጣቂዎችን ለማጥፋት ያካሄደው ጦርነት ሕንጻዎችን እና የመኖሪያ ቤቶችን ወደ ፍርስራሽነት ሲቀይር ቀድሞውንም ለስቃይ በተዳረገው የጋዛ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ የተናቀ ይመስላል” ብለው፥ ዛሬ ጋዛ ምን እንደሚመስል ለመረዳት የአየር ላይ ምስሎችን መመልከት በቂ እንደሆነ ተናግረው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚያሳዝን ሁኔታ አቅም እንደሌለው እና እውነተኛ ተፅእኖ መፍጠር የሚችሉ አገራትም እየደረሰ ያለውን እልቂት ለማስቆም እስካሁን እርምጃ አለመውሰዳቸው ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሐምሌ 13/2017 ዓ. ም. የተናገሯቸውን ግልጽ ቃላት መድገም እንደሚችሉ ተናግረው፥ ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፥ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰብዓዊ ሕግጋትን እንዲያስከብሩ እና ሲቪሎችን ከአደጋ የመጠበቅ ግዴታውን እንዲያከብር፣ እንዲሁም የጋራ ቅጣትን የኃይል አጠቃቀም እና ሕዝቡ በግዳጅ እንዳይፈናቀል የመከልከል ሃላፊነትን እንዲያከብር ጥሪዬን አቀርባለሁ” ማለታቸውን አስታውሰው እነዚህ ቃላት አሁንም ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በእርግጥ አሁን እያደረገ ካለው እጅግ የላቀ ነገር ማድረግ እንደሚችል የጠቆሙት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአንድ በኩል እየሆነ ያለው ነገር ተቀባይነት የለውም እያለ በሌላ በኩል እንዲከሰት መፍቀዱን ቀጥሏል” ብለው፥ ስለዚህ ማኅበረሰብ ሕጋዊነት ራሳችንን በቁም ነገር መጠየቅ አለብን ብለዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተፈጸመ ላለው ግድያ የጦር መሣሪያን ማቅረብ መቀጠሉ የገለጹት ብጹዕነታቸው፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እየሆነ ያለውን ነገር ማስቆም ባይችልም ነገር ግን ይህንን አሳዛኝ ክስተት ለማስቆም ብዙ ማበርከት የሚችሉ እና ማበርከት ያለባቸው ዓለም አቀፍ ተዋናዮች መኖራቸውን ተናግረው፥ “የተባበሩት መንግሥታት በዓለም ላይ እየተካሄዱ ያሉትን በርካታ ጦርነቶችን በማስቆም ረገድ የበለጠ ውጤታማ የሚሆንበትን መንገድ በማሳየት ልናግዘው ይገባል” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ጦርነቱ እንዲቆም በማለት ያወጡትን  እቅድ በማስመልከት እንደተናገሩት፥ የፍልስጤም ሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን በሚወስነው መንገድ እና ይህን እልቂት ለማስቆም የሚረዳ ማንኛውም እቅድ፥ ታጋቾችን መልቀቅ፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በየቀኑ የሚደርስ ግድያን የሚያስቆም እና ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ እና የሚደገፍ መሆን አለበት ብለው፥ አያይዘውም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ፓርቲዎቹ እቅዱን እንደሚቀበሉ እና ወደ እውነተኛ የሰላም ሂደት የሚወስድ ድርድር እንደሚጀመር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ በእስራኤል ውስጥ ሲቪሉ ማኅበረሰብ የእስራኤልን የጦርነት ፖሊሲ በመቃወም እና ሰላምን በመደገፍ የወሰደውን አቋም በማስመልከት ሲናገሩ፥ ምንም እንኳን ለእነዚህ ተነሳሽነቶች አንዳንድ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ጥቂት ጽንፈኞች በሚፈጽሙት ጥቃት ሳቢያ የተሳሳተ መረጃ ሊሰጥባቸው ቢችልም፥ የእስራኤል ሲቪል ማኅበረሰብ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ መገኘቱ እና የበርካታ ወጣቶች ቁርጠኝነት በጣም አስደናቂ እንደሆነ ገልጸው፥ “በግዴለሽነት የተመለከቱት እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው” ብለው፥ ይህ የእኛ እና የዓለም የሰላም ፍላጎት እና የወደፊት ዕጣ የሚወሰነው በእነርሱ ላይ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ይህ ሁሉ ሲያጋጥም ቤተ ክርስቲያን ከሁሉ በላይ መጸለይ እንዳለባት፣ “ጥረቱ በዓመፀኞች እጅ ወድቆ መጫወቻ እንዳይሆን በሚል ስጋት ወደ ጎዳና መውጣት የለበትም” የሚለውን በተመለከተ ሲናገሩ፥  “እኔ የተጠመቅሁ፣ አማኝ እና ካህን እንደመሆኔ በእግዚአብሔር ፊት የማያቋርጥ ጸሎት ማድረግ፣ እርሱ እንዲረዳን፣ የሚሆነውን ክፉ ነገር በሙሉ ለማስቆም ጣልቃ እንዲገባ መጠየቅ እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ጥረት መደገፍ አስፈላጊ እና መሠረታዊ ነው” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ምዕመናን በሙሉ ከጥቅምት 1 ጀምሮ ለሰላም የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያደሱ በድጋሚ ማሳሰባቸውን  አስታውሰው፥ የክርስትና እምነት ከእግዚአብሔር ኃይል ጋር ካልተዋሄደ እምነት ሊሆን እንደማችል ገልጸው፥ “እንደ እኛ ስጋል ለብሶ ሰው የሆነው አምላክ በዙሪያችን ወይም ከእኛ ርቆ በሚሆነው ነገር ላይ ግድየለሾች መሆን እንደማንችል አሳይቶናል” ብለዋል። ጸሎት መቼም ቢሆን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነገር ግን ተጨባጭ ተግባር፣ የሕሊና መነቃቃት፣ የሰላም ተነሳሽነት፣ ግንዛቤን መጨበጥ እንደሚያስፈል አሳስበዋል። “በዝምታ ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ለኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ በርካታ ወጣቶች አሉ” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ እነዚህ በሙሉ ለጸሎት መጠራታቸውን ገልጸው፥ “የክርስቲያንነት ድርሻችን ራሳችንን በቤተ መቅደስ ውስጥ በጸሎት መዝጋት ብቻ ሳይሆን፥ ጸሎታችን ከተግባር እና ከምስክርነት ጋር ተጨባጭ ወደ ሆኑ ምርጫዎች የሚመራን መሆን አለበት” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሰላም ጥሪ ማቅረብ እንደማይሰለቹ እና ቅድስት መንበርም የራሷን ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ቅድስት መንበርን አንዳንድ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ እንደሚረዷት የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ የሰላም ጥሪ፣ ውይይት፣ መጋበዝ፣ እና ድርድር የሚሉትን ቃላት መጠቀም እንደምትቀጥል ተናግረው፥ እነዚህ በሙሉ ማለቂያ ለሌለው ጦርነት፣ ለጥላቻ እና ለጥፋት የዲፕሎማሲ አማራጮ በመሆናቸው ከፍ አድርገን ድምጻችንን ማሰማት፣ ጊዜው ከማለፉ በፊት ጦርነትን ማቆም እና እርምጃን መውሰድ አለብን” ብለዋል።

በቅድስት መንበር እና በፍልስጤም መንግሥት መካከል በተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት ቅድስት መንበር ለፍልስጤም ግዛት ከአሥር ዓመታት በፊት በይፋ እውቅናን መስጠቷን የተነገሩት  ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ የዓለማቀፋዊ ስምምነቱ መግቢያ የፍልስጤም ጉዳይ በሁሉም መልኩ ፍትሃዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ሰላማዊ መፍትሄን በዓለም አቀፍ ሕግ እና በሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔዎች መሠረት የሚደግፍ መሆኑን አስረድተዋል። በተመሳሳይም ዌስት ባንክን፣ ምሥራቅ እየሩሳሌምን እና ጋዛን የሚያካትት ነፃ፣ ሉዓላዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተግባራዊ የሆነ የፍልስጤም መንግሥትን የሚደግፍ መሆኑን አክለው አስረተደዋል። ስምምነቱ በተቃራኒ ሳይሆን የፍልስጤም ግዛት ከሌሎች ጎረቤት አገራት ጋር በሰላም እና በፀጥታ አብሮ የመኖር አቅም እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል። በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ አገሮች ለፍልስጤም ግዛት እውቅናን መስጠታቸው እንዳስደሰታቸው ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ተናግረዋል። ነገር ግን የእስራኤል መግለጫዎች እና ውሳኔዎች በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ መሆናቸውን በጭንቀት እንደሚመለከቱ ተናግረው፥ “ይህም እውነተኛ የፍልስጤም ግዛት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መወለዱን ለማደናቀፍ ያለመ ነው” ብለዋል። የፍልስጤምን መንግሥት የመፍጠር መፍትሔ ካለፉት ሁለት ዓመታት ክስተቶች አንፃር ዛሬ የበለጠ ትክክለኛ የሚመስል መሆኑን ገልጸው፥ ቅድስት መንበር ከጅምሩ የደገፈችው “በሁለት ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ሁለት ሕዝቦች” የሚል እንደሆነ እና የሁለቱም ሕዝቦች እና ግዛቶች ዕጣ ፈንታ የተሳሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በጋዛ ክርስቲያኖች ላይም ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ እነዚህ ክርስቲያኖች በጦርነት ወቅትም ቢሆን በቤታቸው ለመቆየት የቆረጡ፣ ለሰላም እና በጦርነት ለተጎዱት በየዕለቱ የሚጸልዩት ሰዎች መሆናቸው አስረድተው፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁኔታው አስጊ እየሆነ የመጣ ቢሆንም፥ በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ እና ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት ከሆነው “ካሪታስ” ጋር በሁሉም መንገድ ለመቀራረብ እንደሚሞክሩ ገልጸዋል። ዕርዳታን ለማድረስ እና በጽኑ ለቆሰሉ ሰዎች እንክብካቤን የሚያደርጉ መንግሥታትን እና ተቋማት አመስግነዋል። ቁጥራቸው እየቀነሰ በሄደ ቁጥር በመካከለኛው ምሠራቅ ያሉ ክርስቲያኖች ሚና አሁንም ድረስ መሠረታዊ እንደሆነ አስረድተው፥ “በስቃይ ላይ ያለውን የፍልስጤም ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ሙሉ በሙሉ እንካፈላለን፣ አብረናቸውም የምንሰቃይ መሆናችንን አበክረን መግለፅ እፈልጋለን” ሲሉ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን የመገናኛ ብዙሃን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።

 

 

07 Oct 2025, 17:05