የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ  (@Vatican Media)

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የቬነዙዌላ ምዕመናን የፍትህ መሠረቶችን እንዲገነቡ አሳሰቡ

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ የመጀመሪያዎቹ ሁለት የቬነዙዌላ ቅዱሳን፥ ሆሴ ግሬጎሪዮ ሄርናንዴዝ ሲስኔሮስ እና ማርያ ካርመን ሬንዲልስ ማርቲኔዝን በማስታወስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ የሆሴ ግሬጎሪዮ ሄርናንዴዝ ሲስኔሮስ እና የማርያ ካርመን ሬንዲልስ ማርቲኔዝ የቅድስና አዋጅ ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ሰኞ ጥቅምት 10/2018 ዓ. ም. የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴን አቅርበዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሑድ ጥቅምት 9/2018 ዓ. ም. በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ሰባት አዳዲስ ቅዱሳንን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ቬነዙዌላ ውስጥ ለአምስት ዓመታት ሐዋርያዊ አገልጋይ ሆነው መሥራታቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ የቬነዙዌላ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደስታን በመካፈል የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴን አቅርበዋል። “በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ልባችን በደስታ ተሞልቷል” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ የቬነዙዌላ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት ቅዱሳንን አግኝታለች” ብለው፥ “እነዚህ ቅዱሳን የሁላችን ቅዱሳን ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከቬንዙዌላ የመጡት የሲሞን ቦሊቫር መዘምራን ዝማሬያቸውን ያሰሙ ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቬንዙዌላ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ባለ ሥልጣናት እና በዓሉ ላይ ለመገኘት ወደ ሮም የመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን ተገኝተዋል።

ፈውስን የሚሰጥ ዕርዳታ

በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ከትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 58፡6-11 ተወስዶ በተነበበው ላይ በማስተንተን ቃለ ምዕዳናቸውን ያሰሙት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ሁለቱም ቅዱሳን ለተራቡት እንጀራን እንዲሰጡ፣ ቤት የሌላቸውን እንዲያስጠልሉ፣ የታረዙትን እንዲያለብሱ እና የሚሰቃዩትን እንዲንከባከቡ ለቀረበላቸው ጥሪ ምላሽ የሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቅዱስ ሆሴ ግሬጎሪዮ ሄርናንዴዝ ወደ ጎዳናዎች በመሄድ ለታመሙት መድኃኒት በማደል ፈውስ እና መጽናናትን ይሰጣቸው እንደ ነበር አስታወሰዋል። ብዙዎች “በእርሱ መገኘት ብቻ ተፈውሰናል” ይሉ እንደ ነበር ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረዋል። አክለውም ቅድስት ማርያ ካርመን የቬነዙዌላ ሴቶች ጥንካሬን በመላበስ፣ በሥራ፣ በማደራጀት እና እምነትን ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ እንደምትታወቅ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን 1ኛ ዮሐ. 3:14-18 ተወስዶ የተነበበውን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ “ወንድሞቻችንን በመውደድ ብቻ ከሞት ወደ ሕይወት እንሸጋገራለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል” ብለው፥ “ይህም ሁለቱ ቅዱሳን በብርታት የኖሩት ሕይወት እና ዛሬ ምዕመናን እንዲከተሉት የተጠየቁት መልዕክት ነው” ብለዋል።

ለቬነዙዌላ ሕዝብ የቀረበ ጥሪ

ቬነዙዌላ ከሞት ወደ ሕይወት የምትሸጋገረው የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥ ብቻ ነው” ያሉት   ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ግፊቶችን በማፍረስ፣ የተጨቆኑትን ነጻ በማውጣት እና ሰላምን በመገንባት በፍትህ፣ በእውነት፣ በነጻነት እና በፍቅር እንደ ሆነ ተናግረዋል። ሀገሪቱ የእርስ በርስ መግባቢያ መንገዶችን እንድታመቻች፣ አንድ ለሚያደርጋት ነገር ቅድሚያን እንድትሰጥ እና ለችግሮችዋ የጋራ መፍትሄን እንድትፈልግ አሳስበዋል።

ወደ ቅዱሳን ዘንድ የቀረበ ጸሎት

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያ፥ የቅድስና አዋጁ ይህን መንገድ ለመጀመር ትክክለኛ ወቅት በመሆኑ በከንቱ ማለፍ እንደሌለበት በማሳሰብ፥  ይህን መንገድ በተስፋ እና በቁርጠኝነት ለመጓዝ እንዲያግዙ በማለት የአዲሶቹ ቅዱሳን የቅዱስ ሆሴ ግሬጎሪዮ እና የቅድስት ካርመን አማላጅነት ተማጽነዋል።

 

21 Oct 2025, 16:40