ቅድስት መንበር በጠፈር ላይ የተመሰረተ የጦር መሳሪያ ‘ጥልቅ እና ከባድ’ ስጋትን እንደሚፈጥር ገለጸች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ 80ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቺያ በህዋ ላይ የጦር መሳሪያዎችን ማከማቸት ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት “እውነተኛ እና ከባድ” ስጋትን እንደሚፈጥር አሳስበዋል።
የህዋ ስፋት እና ተጎጂነት
ሊቀ ጳጳስ ካቺያ ሃምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ‘አፖሎ-11’ ጨረቃ ላይ ያረፈችበት 56ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከጠፈር ተመራማሪው ቡዝ አልድሪን ጋር በቪዲዮ ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ‘የህዋ ስፋት የፍጥረትን ታላቅነት ምስጢር፥ ደግሞም ደካማነቱን ያሳያል’ ማለታቸውን አስታውሰዋል።
የህዋ ውጫዊው አካል በትብብር እና በሳይንሳዊ ግኝቶች ረገድ ‘ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ እድሎችን’ እንደሚሰጥ የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ሆኖም ግን ይህንን ዕድል አደጋ ላይ የሚጥሉ አሳሳቢ አዝማሚያዎች መኖራቸውን አስጠንቅቀዋል።
እ.አ.አ. ከ 1985 ዓ.ም. ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓመታዊ የጦር መሳሪያ ቅነሳ ጉባኤ ላይ ጉዳዩ እየታየ ቢሆንም፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማንኛውም ዓይነት የጦር መሳሪያዎች በጠፈር ላይ እንዳኖር የሚከለክለው ምክረ ሃሳብ ላይ እስካሁን ስምምነት ላይ እንዳልተደረሰ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ካቺያ፥ ፀረ-ሳተላይት ስርዓቶች እና በዝቅተኛ የምድር ምህዋር ውስጥ ያለው የቆሻሻ ክምችት የዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነትን እንዲሁም የጠፈር እንቅስቃሴዎችን የረዥም ጊዜ ዘላቂነት እንደሚጎዳ ጠቁመዋል።
ከግል እና ከሃገራት ፍላጎቶች ጠፈርን መጠበቅ
የቅድስት መንበር ውጫዊው የጠፈር ክፍል ‘ለሁሉም የሰው ልጆች ጥቅም’ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ደጋግማ ስትገልጽ እንደነበር ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህ ራዕይ ቀደም ሲል በውጫዊ የህዋ ስምምነት ውስጥ መካተቱን ገልጸው፥ በስምምነቱ እነዚህ አካባቢዎች ለትውልድ የሚጠበቁ "የጋራ ጥቅም" እንደሆኑ በመገንዘብ ከሃገራት ወይም ከግል አካላት ልዩ ጥቅም መጠበቅ እንዳለባቸው መካተቱን አስረድተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ካቺያ እነዚህ ጉዳዮች “ያለፉት ግጭቶች ወደ መድገም” ወይም ጠፈርን ‘ሁሉንም ሰው አደጋ ላይ ወደሚጥል የውድድር ሜዳ’ መቀየር እንደማይገባቸው አስጠንቅቀው፥ ከዚህ ይልቅ ሃገራት የመተባበር እና ብዝሃነትን የመቀበል፥ እንዲሁም “በህዋ ውስጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የጋራ ተጠቃሚነትን የማበረታታት ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው መክረዋል።
የተስፋ፣ የእድገት እና የጋራ ኃላፊነት ጎራ
የቅድስት መንበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ ተወካይ ሊቀ ጳጳስ ካቺያ በመጨረሻም “ምድራዊ ፉክክርን ወደ ‘ጠፈራዊ’ ፉክክር ከማስፋት” ይልቅ “አብሮነትን ለማጠናከር” ጥቅም ላይ እንደሚውል ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፥ ዋና ዓላማው ውጫዊው ጠፈር የተስፋ፣ የእድገት እና የመጪዎቹ ትውልዶች የጋራ ኃላፊነት መያዙን ማረጋገጥ ነው በማለት ንግግራቸውን አጠቃለዋል።