የሕጻናት ጥበቃ ኮሚሽን፥ “ቤተ ክርስቲያን አስተማማኝ ቦታ እንድትሆን” በሚል ጭብጥ ጉባኤ አካሄደ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቨርኒ በማከልም፥ “ኮሚሽኑ ጥቃት የደረሰባቸውን በመቀበል፣ በማዳመጥ፣ እውነትን በማውጣት ድጋሚ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመከላከል፥ “ቤተ ክርስቲያን የሕጻናቱ ደህንነት ይበልጥ የሚጠበቅበት ቦታ እንድትሆን ለማድረግ የሚሠራ ነው” ሲሉ በኮሚሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈፈቻ ላይ ተናግረዋል።
በፖላንድ-ክራኮቪያ ጉባኤው የሚካሄድበት የመለኮታዊ ምሕረት ቤተ መቅደስ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ “ዓመጽ በበዛበት እና እርግጠኛ ባልሆነ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲስፋፋ” በማለት የጸለዩበት ቦታ እንደሆነ ታውቋል።
ኮሚሽኑ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ዓ. ም. ከተመሠረተበት ጊዜ ወዲህ ጠቅላላ ጉባኤውን ከሮም ውጭ ሲያካሂድ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ተነግሯል።
ኮሚሽኑ ከአራት ዓመታት በፊት ከፖላንድ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጋር በመተባበር የመካከለኛው እና ምሥራቅ አውሮፓ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት የሕፃናት እና የአቅመ ደካሞች ድህንነት ለመጠበቅ የሚረዳ ዓለም አቀፍ ጉባኤን በፖላንድ ዋርሶ ከተማ ላይ ማዘጋጀቱ ይታወሳል።
በፖላንድ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2021 ዓ. ም. የተጀመረው ሲኖዶሳዊ የጥበቃ መንገድ ለመቀጠል የሚረዳ ጉባኤ ለማካሄድ ፖላንድ በድጋሚ መመረጧ የሚታወስ ሲሆን፥ ጉባኤው የተካሄደው የቅድስት ፋውስቲና ኮቫልስካ መካነ መቃብር በሚገኝበት የስጂኒኪ ብሔራዊ ቤተ መቅደስ ሲሆን ቦታው፥ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነጋዲያን ከዓለም ዙሪያ የሚመጡበት እንደሆነ ይታወቃል።
የሕጻናትን እና አቅመ ደካሞችን ድህንነት መጠበቅ
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቨርኒ በጉባኤው የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ማብቂያ ባደረጉት ንግግር፥ “በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተጠቆመውን መንገድ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ፈለግ ተከትለን፥ የቤተ ክርስቲያንን እና የሰው ልጆች ጭንቅን ለመሐሪው ኢየሱስ ክርስቶስ አደራ ለመስጠት መጥተናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቨርኒ፥ ኮሚሽኑ ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደርሰውን በደል ለመዋጋት ያበረከተውን አገልግሎት ለማበረታታት ኮሚሽኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ያቋቋሙት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እገዛ እና ተተኪያቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በማድረግ ላይ የሚገኙትን ድጋፍ አስታውሰዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቨርኒ፥ “የኮሚሽኑ ተልዕኮ የሕፃናትን እና የአቅመ ደካሞችን ደህንነት በመጠበቅ በድርጊቱ እና ከእነሱ ጋር በሚሆንበት መንገድ ወንጌልን ማወጅ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ ይህ ቁርጠኝነት የአገራቱን ቤተ ክርስቲያናት ማዳመጥን፣ አብሮ መጓዝ፣ ማበረታታት እና መደገፍ እንደሚያካትት አስረድተዋል።
የየአገራቱን ቤተ ክርስቲያናት መደገፍ
በዓለም ዙሪያ ስልጠናን እና ግብዓቶችን የሚያቀርብ “Memorare Initiative” የተሰኘ ተቋም ሲሆን፥ ኮሚሽኑ ክራኮቪያ ጉባኤው የሚካሄድበት ቦታ አድርጎ በመምረጥ ይህም ለአካባቢው ምዕመናን ማኅበረሰብ ያለውን ቅርበት ለማሳየት መሆኑ ተገልጿል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቨርኒ፥ “በሲኖዶሳዊ የጥበቃ ሂደት ላይ በኅብረት ለመጓዝ ያለንን ፍላጎት የሚገልጽ ተጨባጭ ማሳያ ነው” ብለው፥ “ተጎጂዎችን መቀበል፣ ማዳመጥ፣ እውነትን መስማት እና ድጋሚ ጥቃትን መከላከል፥ ቤተ ክርስቲያን አስተማማኝ ቤት ማድረግ የሁላችን ከፍተኛ ጥረት ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ እነዚህን ግቦች ተግባራዊ የሚያደርገው በየአገራቱ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ሁለንተናዊ የጥበቃ መመሪያዎችን ቀስ በቀስ ተግባራዊ በማድረግ ሲሆን፥ ለተፈጻሚነቱ የጥበቃ ፖሊሲዎች እንዲተገብሩ፣ ለቅሬታዎች ምላሽ እንዲሰጡ፣ ለተጎጂዎች፣ ለቤተሰቦች እና ለማኅበረሰቦች ስልጠናን የሚሰጥ የ “Memorare Initiative” ወይም “ሜሞራሬ” ተነሳሽነት ድጋፍ እንደሚስፈልግ ተገልጿል።
“እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ጉባኤው ላይ ቀርበው ከተገመገሙ በኋላ በኮሚሽኑ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ ይሆናሉ" ያሉት ሊቀ ጳጳስ ቬርኒ፥ “በቅርቡ ሁለተኛው ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚቀርብ ስገልጽ ደስታ ይሰማኛል” ብለው፥ የኮሚሽኑ አባላት መስከረም 2/2018 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር መገናኘታቸውን እና በዕለቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የድኅንነት ጥበቃ ፖሊሲዎችን እና ሂደቶችን የያዘ ሪፖርት በማቅረብ የመጀመሪያው ሪፖርት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 29/2024 ዓ. ም. መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጸሎት
ሊቀ ጳጳስ ቬርኒ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ “ዓመጽ በበዛበት እና እርግጠኛ ባልሆነ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲስፋፋ” በማለት የተናገሯቸውን ቃላት በማስተጋባት፥ “የዘላለም አምላክ በደግነትህ ወደ እኛ ተመልክተህ ምህረትህን በውስጣችን እንድታበዛልን፣ በአስቸጋሪ ጊዜያት ተስፋ ሳንቆርጥ በጽኑ እምነት ራሳችንን ለቅዱስ ፈቃድህ እንድናስገዛ እርዳን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ወደፊት የሚጠብቅ ሥራ
በፖላንድ-ክራኮቪያ ከመስከረም 20-23/2018 ዓ. ም. በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ከቅድስት መንበር የመጡ የሕጻናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን አባላትን ጨምሮ ከገዳማዊ ማኅበራት እና ከምዕመናን ወገን የተወጣጡ ባለሙያዎች እንዲሁም አንዳንድ የጥቃቱ ሰለባዎችም መገኘቸው ታውቋል።
እስከ ዓርብ መስከረም 23/2018 ዓ. ም. ድረስ በሚቆየው ጉባኤ መካከል በርካታ የጋራ እና የቡድን ውይይቶች እንደሚካሄዱ የተገለጸ ሲሆን፥ ኮሚሽኑ ከፖላንድ ጳጳሳት ጉባኤ ጋር እንደሚገናኝ እና በጉባኤው መጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥም ይጠበቃል።