ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ   ((foto © Teresa Tseng Kuang Yi))

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በጋዛ ስምምነት የተሰማቸውን 'እርካታን' ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሃፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በግብፅ ስለተፈረመው የእስራኤል-ሐማስ ስምምነት እንዲሁም ቅድስት መንበር የጳጳሳት ሹመትን አስመልክቶ ከቻይና ጋር ስላደረገችው ስምምነት እና የኖቤል የሰላም ሽልማት ለማሪያ ኮሪና ማቻዶ መሰጠቱን አስመልክተው ማብራሪያ መስጠታቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከቫቲካን የመገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በአሜሪካ አሸማጋይነት በሃማስ እና በእስራኤል መካከል በግብፅ በተደረሰው የሰላም ስምምነት የተሰማቸውን ‘አጠቃላይ እርካታ’ ገልጸው፥ ካርዲናሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ስምምነቱን አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመደ ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ “ይህ ስምምነት በእርግጥ ወደ ዘላቂ እና አስተማማኝ የሰላም ጎዳና የሚወስድ የመጀመሪያው እርምጃ ነው” ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የእስራኤል ኤምባሲ መግለጫ
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ባለፈው ሳምንት ለቫቲካን መገናኛ ብዙኃን የሰጡትን ቃለ ምልልስ በመተቸት በቅድስት መንበር የእስራኤል ኤምባሲ የሰጠውን መግለጫ በማስመልከት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ በዚህ በቫቲካን ኒውስ እና በላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ ታትሞ በወጣው ቃለ ምልልስ ላይ መግለጽ የፈለጉት መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የሃማስ ታጣቂ ቡድን በእስራኤል ላይ በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ለደረሰው ጉዳት ቅድስት መንበር ያላትን አጋርነት እና አብሮነት ለማሳየት ታስቦ እንደነበር ገልጸው፥ “ከሁሉም በላይ ቃለ ምልልሱ ለሰላም የተደረገ ጥሪ ነበር” ብለዋል።

“በሁለቱ ሁኔታዎች መካከል የሞራል እኩልነት አለ ብዬ አላምንም” ያሉት ካርዲናሉ፥ ጥቃት ሁልጊዜ መወገዝ እንዳለበት ገልጸው፥ በዚህ መግለጫ ለመግለፅ የታሰበው ዋናው ነገር ስለ ሰላም እንደሆነ፥ እንዲሁም “ይህን ግጭት ለማስቆም የእርቅ እና የሰላም መንገድ ለመጀመር ያለውን ፍላጎት ለመግለጽ ነበር” ብለዋል።

በጣም አስቸጋሪው ነገር አፈፃፀሙ እንደሆነ የጠቀሱት ካርዲናሉ፥ ምክንያቱም ደግሞ እነሱ እንደሚሉት አንዳንድ አስቸጋሪ ጉዳዮች በዝርዝሩ ውስጥ በመካተታቸው እንደሆነ ጠቅሰው፥ ስለዚህም መተግበር ያለባቸው ብዙ ነጥቦች መኖራቸውን እና ምናልባትም በሁለቱ ወገኖች መካከል ፍጹም የሆነ ስምምነት አለመኖሩ ነው ብለዋል።

ይህም በመሆኑ ዋናው የሚያስፈልገው ነገር “በጎ ፈቃድ” እንደሆነ ገልጸው፥ ውጤቱም ቢያንስ በሰላም መጠናቀቁን በማድነቅ “በዚህ አቅጣጫ እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ከቻይና ጋር በሚደረገው ውይይት የታዩ መሻሻሎች
የቅድስት መንበር ዋና ጸሃፊው ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት አጭር ውይይት እ.አ.አ. በ 2017 ዓ.ም. ቫቲካን ከቻይና ጋር የብፁዓን ጳጳሳትን ሹመት አስመልክቶ ስላደረገችው ስምምነት በማንሳት የተወያዩ ሲሆን፥ የሙከራ ስምምነቱ ወደፊትም ተግባራዊ መሆኑን እንደሚቀጥል ጠቁመው፥ ይሄንን ስምምነት በአወንታዊነቱ እንደሚያዩት እና ይህም ቅድስት መንበር እና ቻይና በጳጳሳት ሹመት መሰረታዊ በሆነው ጉዳይ ላይ አንዳንድ አነስተኛ ስምምነትን እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በእርግጥ አሁንም ድረስ ችግሮች ቢኖሩም ነገር ግን እነዚህን ችግሮች በከፍተኛ ትዕግስት እና መተማመን መፍትሄ ሊበጅላቸው እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን በድብቅ የሚሾሙ ቡድኖች መኖራቸውን ጠቁመው፥ ነገር ግን ስምምነቱ በትክክል ይህንን የመከፋፈል አዝማሚያ በማስወገድ የቤተክርስቲያኗን ሁለንተናዊነት ለማምጣት የሚያስችል እንደነበር ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ተመርጠው ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አንዳንድ “እርምጃዎችን” መውሰዳቸውን የጠቆሙት ካርዲናል ፓሮሊን፥ ብፁዕነታቸው በዚህ መንገድ እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ብዙ ጊዜ እንደሚናገሩት ይህ መንገድ አንድ ሰው በተመሳሳይ መልኩ “ጥሩ ካቶሊክ እና ጥሩ የቻይና ዜጋ” መሆን እንደሚችል ያሳያል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ይህ ሁሉንም ሃገራት እንደሚመለከት ጠቁመው፥ ጥሩ ካቶሊክ መሆን ለትውልድ አገሩ ታማኝ ከመሆን እና የመላው ህብረተሰቡን ደህንነት ለማሻሻል ከሚደረገው ጥረት ጋር በምንም መልኩ አይቃረንም ብለዋል።

ለማቻዶ የተሰጠ የኖቤል ሽልማት
እ.አ.አ. ከ 2009 እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ በቬንዙዌላ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ ሆነው ያገለገሉት እና ሃገሪቱን በሚገባ የሚያውቁት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የኖቤል የሰላም ሽልማትን ስላሸነፈችው ቬንዙዌላዊ አክቲቪስት ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ያላቸውን አስተያየት ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፥ ይህ ውሳኔ ሀገሪቱን በእውነት ሊረዳ ይችላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቁመው፥ “በሃገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን፣ የዲሞክራሲ ጎዳና እንዲታደስ እና በፖለቲካዊ አንጃዎች መካከል ትብብር እንዲኖር ያስችላል” በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

14 Oct 2025, 14:17