ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለዩክሬን ሰላም የሁሉም ሰው አስተዋጽዖ ያስፈልጋል ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ማክሰኞ ጥቅምት 18 በሮም በሚገኘው ባምቢኖ ገሱ የሕፃናት ሆስፒታል በተደረገው ዝግጅት ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ ሃገራት እየተካሄዱ የሚገኙትን ግጭቶችን ለማስቆም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ከእነዚህም ግጭቶች መካከል በዩክሬን እየተካሄደ ላለው ጦርነት ‘ጥቂት እርምጃዎችን በመውሰድ ሰላምን ለማስፈን የሁሉም ሰው አስተዋፅኦ በእውነት እንደሚያስፈልግ’ ገልጸው፥ "የተሻለ ጉልህ ሚና" እንዲጫወቱ ጥሪ ከቀረበላቸው ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ አውሮፓ፣ እንዲሁም ቻይና እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሁኑ ወቅት እየጎበኟቸው ከሚገኙት የምስራቅ ሃገራት ድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የቅድስት መንበር የሕፃናት ሕክምና ሆስፒታል የሆነው ‘ባምቢኖ ገሱ’ የምርምር፣ የህክምና እና የጤና አጠባበቅ ሳይንሳዊ ተቋም (IRCCS) ሆኖ እውቅና ያገኘበት 40ኛ ዓመት በተከበረበት ዝግጅት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
ግጭቶችን ለማስወገድ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስመልክተው እንደተናገሩት አስተዋይነት እና ጥንቃቄ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበው፥ በሁለቱ ሃገራት መካከል ዕርቅ እንዲወርድ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ለተጠየቁት ጥያቄ “በአስቸኳይ መልስ ለመስጠት ቀላል ባይሆንም” ነገር ግን ተስፋ ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ በይፋ ባይሆንም አንዳንድ ድርድሮች እየተካሄዱ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
እነዚህ ውይይቶች ፍሬ እንዲያፈሩ ያላቸውን ተስፋ በድጋሚ የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሃፊው፥ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰፊ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፥ ይሄንንም ለማድረግ የዩናይትድ ስቴትስ ተሳትፎ በእርግጠኝነት አስፈላጊ እንደሆነ እና አውሮፓም ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ሚና እንደምትጫወት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዚሁ ጉዳይ ለመወያየት በአሁኑ ጊዜ በቻይና እና በሩቅ ምሥራቅ ሃገራት ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኝ አስታውሰው፥ ቻይናም የበኩሏን አስተዋፅዖ እንደምትወጣ የገለጹ ሲሆን፥ ወደ ሰላም ጥቂት እርምጃዎችን ለመራመድ የሁሉም ሰው አስተዋፅዖ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ኦርባን ጋር የተደረገው ስብሰባ
ሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ጋር በቅድስት መንበር ስለነበራቸው ቆይታ የተጠየቁት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረው ስብሰባ “መልካም አጋጣሚ” እንደሆነ ገልጸው፥ “ሁለቱም ወገን የየራሳቸውን አመለካከት መግለጽ እንደቻሉ” የጠቆሙ ሲሆን፥ አቋማቸው ይራራቅ እንደሆነ ለተጠየቁት ጥያቄ፣ “ሁለቱን አካላት ይበልጥ ለማቀራረብ ጥረት እየተደረገ” እንደሆነ አብራርተዋል።
ለሰብአዊ ሥራዎች ያለው ቁርጠኝነት
የቅድስት መንበር ዋና ጸሃፊ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የባምቢኖ ገሱ ሆስፒታል ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ለጣሊያን የጤና ተቋማት የመልካም ግንኙነት ተምሳሌት እንደሆነ ገልጸው፥ ሆስፒታሉ በካቶሊክ እና በብሔራዊ የጤና ተቋማት መካከል ያለውን ህልውና እና ሚና ለማጉላት ይህ አስፈላጊ ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከፍልስጤም ብቻ ሳይሆን በግጭት የተጎዱ ሌሎች ህፃናትን ተቀብሎ የሚያስተናገደውን የሆስፒታሉን የሰብአዊ አገልግሎት ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ ባምቢኖ ጌሱ ታላቅ የሰብአዊነት ሥራ እየሰራ እንደሆነ ገልጸው፥ ለሰላም የዝግጁነት እርምጃ ሊሆን እንደሚችል በማመን የጦርነቱ ሰለባዎችን በመንከባከብ እና በእስረኞች ልውውጥ ወቅትም የራሱን ድርሻ በመወጣት ባሳየው ከፍተኛ የሰብአዊ ጥረቶች ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት አሳይተናል ብለዋል።