የስልጠናው ተሳታፊዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መስከረም 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ባቀረቡት ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ተሳትፈዋል  የስልጠናው ተሳታፊዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መስከረም 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ባቀረቡት ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ተሳትፈዋል   (@Vatican Media)

ወጣት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሮም ተገናኝተው ስለ እምነት ግንኙነት መወያየታቸው ተነገረ

አሥራ አምስት የሚሆኑ ወጣት የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ከመስከረም 2 እስከ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ዘላለማዊ ከተማ ተብላ በምትታወቀው ሮም ውስጥ “የእምነት ግንኙነት በዲጂታል ዓለም” በሚል ጭብጥ ለአንድ ሳምንት በሚከበረው መርሃ ግብር ላይ ተገናኝተው ወንጌልን በስፋት ማሰራጨት የሚቻሉባቸው አዳዲስ መንገዶችን ለመቃኘት መወያየታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ 15 ወጣት ኮሙዩኒኬተሮች በሮም ከተማ በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽህፈት ቤት ለአምስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው “የእምነት ግንኙነት በዲጂታል ዓለም” (Faith Communication in the Digital World) የሚል ጭብጥ ያለው ሥልጠና ላይ ለመካፈል ተሰብስበው እንደነበር ተገልጿል።

ከመስከረም 2 እስከ 9 ለአንድ ሳምንት ጊዜ ያክል በተካሄደው በዚህ ስልጠና ላይ ተሳታፊዎች ልዩ የሆነ የተግባር ትምህርት እና የሲኖዶሳዊ ልምድ ልውውጥ ላይ የተካፈሉ ሲሆን፥ እነዚህ ከ11 አገሮች ማለትም ከኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ካናዳ፣ ፊሊፒንስ፣ ፍልስጤም፣ ፖላንድ፣ ክሮኤሺያ፣ ጣሊያን፣ ህንድ፣ ኡራጓይ እና ዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ወጣት ባለሙያዎች የተሳተፉበት ይህ ዝግጅት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የጀመረው እና እስከ መጋቢት 2018 ዓ.ም. ድረስ የሚቀጥለው ፕሮጀክት አካል መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮግራሙ ሳምንታዊ የዙም ስብሰባዎችን እና የቡድን ፕሮጄክቶችን አንድ ላይ ያጣመረ ሲሆን፥ ዓላማውም በዲጂታሉ ዓለም እምነትን ለማዳረስ ጠቃሚ ግብአቶችን ለማቅረብ እንደሆነ ተነግሯል።

ተሳታፊዎቹ እግረ መንገዳቸውንም በማህበራዊ ሚዲያ መስተጋብር ላይ የሃዋሪያዊ ሥራዎችን በስፋት ለማከናወን የሚቻሉባቸው መንገዶች ላይ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ልዩ ሥልጣን የተዘጋጀውን 'ኮሚዩኒዮ' እና 'ፕሮግረሲዮ' የተባሉትን የሃዋሪያዊ ሥራ መመሪያ አስመልክቶ ሥልጠና እንደወሰዱ ተገልጿል።

የዚህ ተነሳሽነት ዓላማ የመንፈሳዊ ምስረታ ጤናማ ልምምዶችን ከማጎልበት በተጨማሪ፣ አዳዲስ የወንጌል ስርጭት አይነቶችን ለማነሳሳት፣ ቤተክርስቲያኗ ተግዳሮቶች በሚገጥሟት ጊዜያት የልምድ ልውውጥን ለማበረታታት እና አዳዲስ ትውልዶች ከዲጂታል ሚዲያ ጋር የሚገናኙበትን መንገድ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹ እንደ አንድ የጉዞው አካል ለሶስት የካቶሊክ ተቋማት የግንኙነት ፕሮጀክቶችንም እንደሚያቀርቡ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

በሮም ከተማ ለአንድ ሳምንት የተካሄደው ይህ መርሃ ግብር የመስማት፣ የመንፈሳዊ ምስረታ እና የትግበራ ጊዜያትን ያካተተ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ቡድኑ የበለጸገ የእንቅስቃሴ መርሃ ግብር በመከተል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መስከረም 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ባቀረቡት ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ተገኝተው ከብፁእነታቸው ጋር ሰላምታ የመለዋወጥ እድል እንደነበራቸው፣ ብሎም የቫቲካን ረዲዮ ሙዚየምን ጨምሮ አራቱን ባሲሊካዎች፣ የቫቲካን መካነ መቃብራትን እና የቅድስት መንበር የመገናኛ ጽህፈት ቤትን መጎብኘታቸው ተገልጿል።

ተሳታፊዎቹ ከዚህም በተጨማሪ በቅዱስ ክሌመንት ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደው መሥዋዕተ ቅዳሴ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፥ በነበራቸው ቆይታ የቅድስት መንበር የመገናኛ ጽህፈት ቤት ፀሐፊ ከሆኑት ሞንሲኞር ሉሲዮ አድሪያን እና ከጽህፈት ቤቱ ዋና ሃላፊ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በቅድስት መንበር የነገረ መለኮት መምሪያ ዳይሬክተር በሆኑት ናታሻ ጎቬካር የሚመራ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እና የቅዱስ ጥበብን እንደ ልዩ የመገለጫ መንገድ በመጠቀም የተዘጋጀ የአስተንትኖ ክፍለ ጊዜዎች ላይ ቆይታ እንደነበራቸው ተገልጿል።

ቁልፍ በሆኑ ጥያቄዎች በመመራት ተሳታፊዎቹ ለአንድ ሰዓት ያህል የግል የፀሎት መርሃ ግብር የነበራቸው ሲሆን፥ በመቀጠልም ግንዛቤያቸውን ለቡድኑ ማካፈላቸው ተነግሯል።

ወጣት ኮሚኒኬተሮቹ ከኢዮቤልዩ የመጽናኛ ሳምንት ጋር የተገጣጠመውን ይሄንን የስልጠና ጊዜ በመጠቀም በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የተመራውን የጸሎት መርሃ ግብር ላይ ተካፍለዋል።

በእየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የምትከተል ቤተክርስቲያ የመገናኛ ብዙሃን ስራ አስኪያጅ የሆነችው ሚራል አቲክ ጉዞው በተሳሳተ ወቅት የተደረገ መስሏት በመጀመሪያው ቀናት ትንሽ ምቾት እንዳልተሰማት የገለጸች ቢሆንም፥ ሆኖም ግን ሳምንቱ በጣም አስደሳች እንደነበር ገልፃ፥ ‘በዚህ ተሞክሮ ዛሬ የምንወስዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች ትንሽ ቢመስሉም በረጅም ጊዜ ውስጥ ፍሬ ሊያፈሩ እንደሚችሉ ተስፋ ሰጥቶኛል’ ብላለች።

ሚራል የግለሰባዊ ቁርጠኝነትን አስፈላጊነት ስትገልጽ “ለመስማትና ለመማር ክፍት በሆነ ልብ፥ ለእሷ ኮሚኒኬተር መሆን እንደ ሥራ ብቻ የሚታይ ሳይሆን፣ ልዩ ሙያና በአገሯ ውስጥ የአኗኗር ዘይቤ እንደሆነ ገልፃላች።

በካናዳ ከቫንኮቨር ሃገረ ስብከት የመጣችው ራቸል ዎንግ በበኩሏ፣ መከፋፈል ጸንቶ በሚታይባት ዓለም የወንድማማችነት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፥ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ለአንድ አፍታ ባቀረበችው ጸሎት በመነሳሳት በመጨረሻ ሁላችንም መጽናናት ስላለብን፣ ምንም እንኳን የግል ሸክሞች ቢኖሩም ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ወንድማማችነት መመሥረት እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።

ራችል በሰጠችው ምስክርነት፣ ሰዎችን በእጅጉ የሚከፋፍሉትን የምሬት እና የጥላቻ ስሜቶችን በፍቅር መንገድ መፍታት ያለውን አጣዳፊነት አፅንዖት ሰጥታ ገልፃለች።

ይህ ተነሳሽነት በቤተክርስቲያኒቱ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተልዕኮ ውስጥ፣ በቅድስት መንበር የግንኙነት ጽህፈት ቤት የተሰራ ተጨባጭ እርምጃን እንደሚወክል የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ቴክኖሎጂን እንደ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ለስብከተ ወንጌል እና ኅብረትን ለመገንባት እንደ ለም መሬት ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።

23 Sep 2025, 13:37