ቫቲካን “ፍጥረት እና የመኖሪያ አካባቢ ለዓለም ሰላም” በሚል ርዕሥ ሴሚናር እንደሚዘጋጅ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በጳጳሳዊ የሥነ-መለኮት አካዳሚ (PATH) የከፍተኛ ጥናቶች ምክር ቤት አዘጋጅነት ከመስከረም 1-2/2018 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየውን ሴሚናር የሚከፍቱት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ሲሆኑ፥ አራት መሪ ሃሳቦች ባሉት ሴሚናር ላይ ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ የቤተ ክርስቲያን፣ የቢዝነስ፣ የማኅበራዊ እና የባህል ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ታውቋል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው መርሐ ግብሩ፥ ቤተ ክርስቲያን ሁሉም ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በጋራ ጥቅም እና በሰላም አብሮ የመኖር መንገድ በሰላም ስም የሰውን ልጆች እና የፍጥረትን ደህንነት ለማስጠበቅ እና ለማረጋገጥ የምትከተላቸውን መንገዶች ለይተው እንዲያውቁ የምታሳስብበት እንደሚሆን ታውቋል።
ሴሚናሩ በርካታ ቁልፍ ምንጮችን መሠረት በማድረግ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለ10ኛው የዓለም የፍጥረት እንክብካቤ ጸሎት ቀን ይፋ ካደረጉት መልዕክት፣ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ስለ ፍጥረታት ካቀረበው የምስጋና ዝማሬ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ይፋ ካደረጉት “Redemptor Hominis” ወይም “የሰው ልጅ አዳኝ” ከሚለው ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በሰብዓዊ ሥነ-ምኅዳር ላይ ካደረጉት አስተንትኖ፣ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚል ርዕሥ ይፋ ካደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን እና “እግዚአብሔርን አመስግኑ” ከሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ተነሳሽነትን ማግኘቱ ታውቋል። የሴሚናሩ ተናጋሪዎች ዛሬ የሰውን ልጅ እያጋጠሙ ባሉት ተግዳሮቶች እና አዲስ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ራዕይ አስቸኳይ ትብብር አስፈላጊነት ላይ እንደሚያተኩሩ ታውቋል።
የጥናት ክፍለ ጊዜው የሚጠናቀቀው በጳጳሳዊ የሥነ-መለኮት አካዳሚ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንቶኒዮ ስታግሊያኖ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በሚመሩት መስዋዕተ ቅዱሴ እንደሚሆን ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከሴሚናሩ ታዳሚዎች ጋር በቫቲካን ውስጥ ቅዳሜ መስከረም 3/2018 ዓ. ም. ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ እንደሚገናኙ የተገልጸ ሲሆን፥ ተጨማሪ መረጃን www.theologia.va ከተሰኘ የአካዳሚው ድር-ገጽ ማግኘት እንደሚቻል ተነግሯል።
“ፍጥረት እና የመኖሪያ አካባቢ ለዓለም ሰላም” በሚል ርዕሥ ለቀረበው ዓለም አቀፍ ሴሚናር በርካታ ድርጅቶች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል፥ Arpinge, Polideck, Guglietta Global, His Way at Work እና NTT DATA የተባሉት ይገኙበታል። በተጨማሪም ታዋቂ የንግድ አጋሮች፣ በጳጳሳዊ አካዳሚ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 2023 ዓ. ም. በፀደቀው “Theologiam Promovendam” ወይም “ሥነ-መለኮትን ማስተዋወቅ” በሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ ደንብ ላይ በተቀመጡት መመሪያዎች መሠረት ተነሳሽነቱን በጣሊያን እና በዓለም ዙሪያ ከሚያስተዋውቅ የሥነ-መለኮት ክፍል ድጋፍ መደረጉ ታውቋል።