እስራኤል በጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሕንጻ ላይ የፈጸመችው ጥቃት እስራኤል በጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሕንጻ ላይ የፈጸመችው ጥቃት  (MAHMOUD ISSA)

ካርዲናል ፓሮሊን፥ ጋዛ ውስጥ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ እና በዩክሬን ያለው እልቂት እንዲያበቃ አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ ሮም ውስጥ በሚገኘው “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ውስጥ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ብጹዕነታቸው በዝግጅቱ ላይ ለተገኙት አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ቅድስት መንበር ግጭቶችን ወደ ፍጻሜ የሚያደርሱ መፍትሄዎች ሊገኙ እንደሚችሉ ተስፋ በማድረግ ድምጿን ማሰማት መቀጠሏን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ በጋዛ ሰርጥ ቀውስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቅድስት መንበር ተኩስ እንዲቆም፣ ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማዳረስ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እና ገንቢ የሰላም ድርድር እንዲጀመር በማለት ስትጠይቅ መቆየቷን አስታውሰዋል። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ለቅድስት መንበር የሰላም ጥሪ ትኩረት ባለመሰጠቱ የተነሳ በየዕለቱ የጅምላ ጭፍጨፋ እንደሚካሄድ እና ምንም ዓይነት የሰላም ውይይት አለመኖሩን ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ዓርብ መስከረም 30/2017 ቀን በሮም በሚገኝ “ባምቢኖ ጄሱ” ካቶሊክ ሆስፒታል ካደረጉት ጉብኝት ጎን ለጎን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሁድ ጳጉሜ 2/2017 ዓ. ም. ቅድስናቸውን የፋ የሚያደርጓቸውን የብጹዕ ካርሎ አኩቲስ እና የብጹዕ ፒየር ጆርጆ ፍሬሳቲ ምስልን ባርከዋል።

አሳዛኝ ሁኔታው ለውይይት ይጋብዛል

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን “SIR” ለተሰኘ ሃይማኖታዊ የመረጃ ተቋም በሰጡት አስተያየት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ብዙ ጊዜ እንዳመለከቱት ሁሉ፥ ግጭት ወስጥ የሚገኙ ወገኖች ወደ ሰላም ለመድረስ የሚያደርጉትን ውይይት እንዲቀጥሉ እና ጋዛ ውስጥ ላለው አስከፊ እና አሳዛኝ ሁኔታ መፍትሄን እንዲያገኙ ጠይቀዋል። “ጥረታችን ከዚህ በፊት የምናቀርበውን ድምጽ ለመቀጠል ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ “ከእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አቶ አይዛክ ሄርዞግ ጋር ሐሙስ ነሐሴ 29/2017 ዓ. ም. ያደረግነው ወሳኝ ውይይት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድምጽ ጋር ተዳምሮ የተወሰነ ውጤት ይኖረዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉ ሰዎችን ድኅንነት መጠበቅ

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ልክ እንደ መላው ጋዛ በክልሉ ውስጥ ባሉ ወሳኝ ሁኔታዎች ላይ በማትኮር ለቀረበላቸው ሌላ ጥያቄ ሲመልሱ፥ ጋዛ ውስጥ የሚገኝ ካቶሊካዊ ቁምስና በእስራኤል እና በሐማስ ታጣቂ ቡድን መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ መስጠቱን አስታውሰው፥ ቁምስናው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ለማይችሉ በርካታ የአካል ጉዳተኞች ያለው ሥጋት ከፍተኛ እንደሆነ በመናገር፥ በቁምስናው ውስጥ ለመቆየት ለወሰኑት እና ምንም ማድረግ ለማይችሉት ሰዎች አክብሮት እንደሚሰጣቸው እና እነርሱን የመንከባበር እና የመጠበቅ ጥሪያቸው ተደማጭነት እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ለዩክሬን የሰላም ድርድር የቫቲካን በሮች ክፍት ናቸው

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በመጨረሻም፥ አውሮፓው ውስጥ በዩክሬን ያለውን ጦርነት በማስታወስ፥ የፈቃደኛ አገራት ኅብረት የዩክሬንን ደህንነት ለማረጋገጥ ቁርጠኝነታቸውን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። “በዚህ ጉዳይ ላይ የቅድስት መንበር አቋም ‘ውይይት መጀመር አለበት’” የሚል እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ራሳቸው፥ ቫቲካን የሰላም ንግግሮች የሚካሄድባት ቦታ መሆን ትችላለች” ሲሉ በተደጋጋሚ መናገራቸውን አስታውሰዋል። “ይህም እልቂትን ለማስቆም የሚቻልባቸውን መንገዶች ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ያለንን ታላቅ ፈቃደኝነት የሚገልጽ ምልክት ነው” ሲሉ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ንግግራቸውን ደምድመዋል።

06 Sep 2025, 15:17