ቅድስት መንበር ከቪየትናም ጋር ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት መሻሻሉን አስታወቀች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
12ኛው የቅድስት መንበር እና የቬትናም የጋራ ቡድን ስብሰባ በቫቲካን ውስጥ መስከረም 2/2018 ዓ. ም. የተካሄደ ሲሆን፥ ስብሰባውን በጋራ የመሩት፥ ክብርት ለቲ ቱ ሃንግ፥ የቪየትናም መንግሥት የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር እና የልዑካን ቡድኑ መሪ እና ሞንሲኞር ሚሮስላው ዋቾውስኪ፥ በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የመንግሥታት ግንኙነት ክፍል ምክትል ጸሐፊ እና የልዑካን ቡድኑ መሪ ናቸው።
ሁለቱ ወገኖች በቬየትናም እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን ግንኙነት እና በቪየትናም ውስጥ ስለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት ሰፊ የሐሳብ ልውውጥ አድርገዋል። ሁለቱም ወገኖች በቪየትናም የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በወንጌል በመመራት፥ ምዕመናኖቿም ጥሩ ዜጎች በመሆን ለቪየትናም ሁለንተናዊ ዕድገት ያደረገችውን እና እያደረገች የምትገኘውን አወንታዊ አስተዋጽዖ አስታውሰዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት ወር 2024 ዓ. ም. በሃ ኖይ ከተካሄደው አሥራ አንደኛው የቪየትናም እና የቅድስት መንበር የጋራ ቡድን ስብሰባ ጀምሮ በተደረጉት የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህም በመደበኛ ተሳትፎ እና በምክክር፣ በተለያዩ ደረጃዎች የተካሄዱ የልዑካን ልውውጦችን በተለይም በሃ ኖይ ነዋሪ የሆኑ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማሬክ ዛሌቭስኪ ከፍተኛ ደረጃ ውክልናን የሚያካትት መሆኑ ታውቋል።
ሁለቱ ወገኖች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ የጋራ የሥራ ቡድን መደበኛ ስብሰባዎችን ለመቀጠል ተስማምተዋል። መስከረም 2/2018 ዓ. ም. የተካሄደው 12ኛ የጋራ ቡድን ስብሰባ በወዳጅነት፣ በመተማመን እና በመከባበር መንፈስ እንደ ነበር ተመልክቷል።
የቬየትናም ልኡካን ቡድን ቫቲካንን በጎበኘበት ወቅት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን፥ የልኡካን ቡድኑ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊንን እና በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ጋር ተገናኝቶ ተነጋግሯዋል።