ፈልግ

የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሙከራ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሙከራ  

ቅድስት መንበር፥ በኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሙከራ የተጎዱ ማኅበረሰቦችን መደገፍ እንደሚገባ አሳሰበች

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ በዓለም አቀፍ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ ተቃውሞ ቀን ንግግር አድርገዋል። ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ በኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሙከራ ምክንያት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን መደገፍ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ በኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሙከራ ምክንያት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር፥ ለጋራ ውይይት፣ የጦር መሣሪያ ትጥቅ ለማስፈታት እና ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነፃ የሆነ ዓለም ለመገንባት የተገቡ ስምምነቶችን የማክበር ሞራላዊ ግዴታ እንደገና እንዲታደስ አስቸኳይ ጥሪ አቅርበው፥ ኒውክሌር የመሣሪያ ተቃውሞን አስመልክቶ የሚሰሙ ጠንካራ ንግግሮች እንደገና ማገርሸታቸውን ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራን ለመቃወም እና ለማስተዋወቅ በኒውዮርክ ሐሙስ ነሐሴ 29/2017 ዓ. ም. በተካሄደው ከፍተኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈነዳ ሰማንያ ዓመታት ማለፋቸውን አስታውሰው፥ “ድርጊቱ ዓለምን ካልተጠበቀ አጥፊ ኃይል ጋር ያስተዋወቀ እና በሰው ልጅ ላይ ረዥም ጥላ ያጠላበት ክስተት ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ቀጣይነት ያላቸው የኑክሌር ሙከራዎች

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ እንደ ጎርግሮሳውያኑ ከ1945 ዓ. ም. ጀምሮ የተካሄዱት ከሁለት ሺህ የሚበልጡ የኒውክሌር ሙከራዎች በቀጣይነት መካሄዳቸውን በቁጭት ገልጸው፣ እነዚህ ሙከራዎች ነባር ተወላጅ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ፅንስ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አበክረው ተናግረው፥ “የብዙዎች ጤና እና ሰብዓዊ ክብር ለብዙ ጊዜ ሳይስተካከል በዝምታ መጎዳቱን ቀጥሏል” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ የተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ የተከበረ ዓለም አቀፍ ቀን እንደ አዲስ የኃላፊነት ጊዜ ሆኖ እንዲያገለግል አሳስበው፥ በተለይም አስፈላጊ እና የጋራ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የሚሰጥ ዓለም አቀፋዊ ምላሽ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ በመጓዝ በጠቅላላ የሰው ልጅ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይን ከማፍሰስ እና የጋራ ጥቅምን ከማስተዋወቅ ይልቅ ወታደራዊ ወጪን ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር የበለጠ አውዳሚ የጦር መሣሪያዎችን ማምረትን የሚገልጽ ነው” ብለዋል።

በጦር መሣሪያዎች ላይ እምነት መጣል አያስፈልግም

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጦር መሣሪያዎች ላይ እምነት የመጣልን ፈተና እንዲቋቋም አሳስበዋል።

ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነፃ የሆነ ዓለምን መገንባት ስልታዊ እና አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የሞራል ኃላፊነት ጭምር እንደሆነ አስረድተው፣ ቅድስት መንበር ለባለ ብዙ ወገን ማዕቀፎች እና ጠቅላላ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ እገዳን ጨምሮ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ክልከላ ስምምነት እንደምትደግፍ በድጋሚ ገልጸዋል።

የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራ እገዳን ለማጠናከር የቀረበ ዓለም አቀፍ ጥሪ

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ በኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሙከራ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ያህል ለተጎዱት ማኅበረሰቦች ተጨባጭ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው፥ ቅድስት መንበር በኒውክሌር የጦር መሣሪያ ፍንዳታ ላይ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ደንብ ማጠናከር እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ማመኗን ደግመው ገልጸዋል።

09 Sep 2025, 17:24