የፈንጂ ጦር መሣሪያዎች ተቃውሞ ስምምነት የፈንጂ ጦር መሣሪያዎች ተቃውሞ ስምምነት   (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር፥ “የሰብዓዊነት ሕግን ማክበር የሰው ልጆች ኃላፊነት ነው” ስትል ገለጸች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ፥ በፈንጂ የጦር መሣሪያዎች ተቃውሞ ስምምነት የፈረሙት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ ሰብዓዊ ስምምነቶቹ ለአሁኑ እና ለመጪው ትውልድ የሞራል ቁርጠኝነት መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ በንግግራቸው፥ ፈንጂ የጦር መሣሪያዎች ስምምነት በማስመልከት መስከረም 6/2018 ዓ. ም. በተካሄደው 13ኛው የመንግሥታት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግጋትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ደንቦችን ማክበር ደካማነት አይደለም” ብለው፥ ለስምምነቱ ባሳየችው ቁርጠኝነት ፊሊፒንስን አመስግነው መንግሥታቱን በቅርቡ የተቀላቀለች የደቡብ ፓሲፊክ አገር ቫኑዋቱን በደስታ ተቀብለዋል።

“የሰብዓዊነት ስምምነቶች ሕጋዊ ግዴታዎች ብቻ ሳይሆኑ ለአሁኑም ሆነ ለመጪው ትውልድ የሞራል ቁርጠኝነትን ያካተቱ ናቸው” በማለት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ ወር 1939 ዓ. ም. ያቀረቡትን የሰላም ጥሪን በመጥቀስ፥ “በእርግጥ ፍትህ የሚመራው በምክንያት እንጂ በጦር መሣሪያ ኃይል አይደለም” ሲሉ አሳስበዋል።

ሁሉም መንግሥታት የስምምነት አባል እንዲሆኑ የቀረበ ጥሪ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ፥ በስምምነቱ ገና ያልተካተቱ አገሮች ስምምነቱን የሚያከብሩት መሆናቸውን በመልዕክትም ሆነ በመንፈስ በአስቸኳይ እንዲገልጹ የቅድስት መንበር ልዑካን ጥሪ ማድረጉን ተናግረው፥ ስምምነቱ የጸደቀበት አንዱ ምክንያት ሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት ለመጠበቅ፣ ተጎጂዎችን ለመርዳት እና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል እንደሆነ አስረድተዋል።

“ፈንጂ ጥይቶች በተጎጂዎች እና በመሬት ላይ የሚያስከትሉት አስከፊ መዘዞች፣ መመረታቸው፣ መከማቸታቸው፣ መዘዋወራቸው አልፎ ተርፎም በግጭቶች ወቅት ጥቅም ላይ መዋላቸው ቅድስት መንበርን  እጅግ አሳዝኗታል” ሲሉም ተናግረው፥ ለጦርነት ጭካኔያዊ ተግባር የተዳረጉ በርካታ ንጹሐን ተጎጂዎችን እያሳደዱ ይገኛሉ” ብለዋል።

የጦር መሣሪያ ትጥቅ ሳይፈታ ዘላቂ ሰላም ሊኖር አይችልም

“የበርካታ አገራት ቤተሰብ እንደ መሆናችን፥ ተጎጂዎችን መርዳት በዓለም አቀፍ ትብብር እና አንድነት  ላይ የተመሠረተ የጋራ ኃላፊነት ነው” መሆኑን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመደበው ወታደራዊ ወጪ ከ2.7 ትሪሊየን ዶላር በላይ መሆኑ እጅግ በጣም አሳሳቢ እና አልፎ ተርፎም ቅሌት መሆኑን አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ አስረድተው፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሚያዝያ ወር 2025 ዓ. ም. ለመላው ዓለም እና ለሮም ነዋሪዎች ያስተላለፉትን መልዕክት አስታውሰው፥ “ወታደራዊ ወጪው በተለይ በግጭቶች የተጎዱትን ወይም ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለመደገፍ፣ የተራቡትን ለመመገብ እና ሰላምን ለማስፈን ከሚደረገው ውስን ሃብት ጋር ሲወዳደር እጅግ የሚበልጥ መሆኑ በግልጽ ይታያል” ብለው፥  “ያለ እውነተኛ ትጥቅ ማስፈታት ዘላቂ ሰላም ሊኖር አይችልም” ብለዋል።

በአገሮች መካከል መተማመንን ማጎልበት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ እያንዳንዱ ሀገር ሉዓላዊነቱን እና ደህንነቱን ለማስጠበቅ ያለው ቁርጠኝነት ሕጋዊ ቢሆንም፥ ይህ ግን ወደ የጦር መሣሪያ ትጥቅ ውድድር መዞር እንደሌለበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ወታደራዊ አቅምን ማጠናከር በአገሮች መካከል መተማመን እንዲፈጠር እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርግ እንደሆነ በማስተንተን ባቀረቡት አስተያየታቸው፥ “ራስን የመከላከል መብት ፍፁም አይደለም፤ የግጭት መንስኤዎችን ወይም ስጋቶችን መቀነስ፣ በተቻለ መጠን ማስወገድ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ አቅሞችን ለሕጋዊ ደህንነት አስፈላጊ በሆኑት ላይ የመገደብ ግዴታ አለ" ብለዋል።

የጦር መሣሪያ ውድድርን መቃወም

ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ በተጨማሪም፥ የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም የበለጠ እንዲቀጣጠል፣ በሌሎች ዘንድ ዛቻ እና ፍራቻ እንዲፈጠር የሚያደርግ እና ሁሉንም ለጭንቀት በመዳረግ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚያደርግ ከመጠን ያለፈ የጦር መሣሪያ ክምችትን አውግዘዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ፥ሰላምን የማስፈን እና ትጥቅን የማስፈታት ሥራ እንዲጠናከር፣ የሰው ልጅ ክብር ቀዳሚነት እና ተፈጥሯዊ እሴት እንዲቀጥል ጥሪ በማቅረብ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅርቡ የተናገሩትን በማስታወስ፥ “ከሁሉ የሚበልጥ ሕልማችን ሰላም እንጂ ግጭት ባለመሆኑ ይህን ሰላም የምንገነባው አብረን በመሥራት ነው” ብለዋል።

 

 

18 Sep 2025, 13:53