አቡነ ጋላገር፥ “ሰላምን፣ ልማትን እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማበረታታት የመንግሥታቱ ድርጅት መታደስ አለበት" (ክፍል 1)
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ክብርት ፕሬዚደንት! የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሐዋርያዊ ቡራኬ እና ሰላምታ ለእርስዎ እና እዚህ ለተሰበሰቡት የመንግሥታት ተወካዮች በማድረሴ የተሰማኝን ደስታ እየገለጽኩ እንዲሁም ይህንን ጉባኤ እንዲመሩ በመመረጥዎ እንኳን ደስ አለዎት። በጉባኤው መግቢያ ላይ፥ ሚያዝያ 13/2017 ዓ. ም. በተፈጸመው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኘውን ጠቅላላ ጉባኤ ላመሰግን እወዳለሁ።
ሁላችሁም እንደምታውቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በተመረጡበት ወቅት ለመላው ዓለም የተናገሯቸው የመጀመሪያ ቃላት ‘ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን’ የሚል እንዲሁም በጦርነት እና በግጭት በተጎዳው ዓለም ውስጥ ያስተላለፉት የመጀመሪያ መልዕክት የጦርነት ትጥቅን የሚያስፈታ፣ ትሁት እና ጽኑ ሰላም እንዲገኝ የሚል ነበር።
ክብርት ፕሬዚደንት! ‘ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ ለሰማንያ ዓመታት እና ከዚያም በላይ ለሰላም፣ ለልማት እና ለሰብዓዊ መብቶች’ የሚለው እና ለዘንድሮው ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠው መሪ ሃሳብ የመተባበርን አስፈላጊነት ያስረዳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1945 ዓ. ም. የተመሠረተበትን 80ኛ ዓመት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድሮ ማክበሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። ‘ከጊዜ ወደ ጊዜ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ዓለም አቀፍ ሰላምን፣ ልማትን እና ሰብዓዊ መብቶችን ማጎልበት’ የሚሉ የድርጅቱ እጅግ አስፈላጊ እሴቶችን እንደገና ለማረጋገጥ መልካም አጋጣሚ ነው።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1948 ዓ. ም. ይፋ በሆነው ዓለም አቀፍ መግለጫ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋራ እርምጃ ግጭቶችን ለመከላከል እና ለማስቆም፣ ድህነትን ለመዋጋት እና ሰብዓዊ መብቶችን ማሳደግ ወሳኝ ነው።
ሰዎችን ማግለል ወደማይገመት አለመረጋጋት የሚመራ መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። በተቃራኒው አንድነት ኃላፊነት የሚሰማውን ጽናት እና የጋራ ዕድገትን ያጎለብታል። ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቱ እየተባባሰ በሄደበት፣ የአየር ንብረት ቀውስ እየተባባሰ በመጣበት፣ የእኩልነት መጓደል እየሰፋ እና ድህነት እየጨመረ በሄደበት በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ አንድነትን ማደሱ አስፈላጊ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ራሱን ከተለወጠው ዓለም ጋር በማላመድ፥ አንድ ሀገር ብቻውን ሊቋቋመው ከማይችለው እንደ የአካባቢ መራቆት እና የቴክኖሎጂ ሁከት ከመሳሰሉ አደጋዎች አንጻር ውጤታማነቱን ማስጠበቅ አለበት።
የዓለም ሀገራት ተወካዮች እንደመሆናችን መጠን በወንድማማችነት፣ በመተሳሰብ እና በመከባበር እንድንኖር በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረን በሰውነታችን አንድ ሆነናል። ቅድስት መንበር ከግጭት ይልቅ ሰላም የሰፈነበት፣ ፍትህ ድህነትን የሚያሸንፍበት፣ የሕግ የበላይነት ጉልበትን የሚበልጥበት እና እውነት የሰውን ልጅ የዕድገት መንገድ የሚያበራበት መሆኑን በሚያስረዳ ጊዜ በማይሽረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በመመራት ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ ሆኖ ለመቆየት አስባለች።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ በሚገኙ ተግዳሮቶች መካከል በሚታገል ዓለም ውስጥ የሰላም፣ የፍትህ እና የእውነት መሠረቶችን እንደገና መገንባት ያስፈልጋል። የበለጠ የወደፊት ፍትሃዊ ሕይወትን ለመፍጠር ከታሪክ ትምህርት እየወሰዱ እነዚህን ምሰሶዎች መመርመር እና መገንባት አስፈላጊ ነው።
ክብርት ፕሬዚደንት! ሰላም ሁለንተናዊ እና በሥርዓት የተቀመጠ እና በእሴት ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መሠረታዊ ነው። ሰላም ጦርነት ወይም ግጭት አለመኖር ብቻ አይደለም። በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን የኃይል ሚዛን ለመጠበቅ ብቻ ሲባል ጥቅሙ መዘንጋት የለበትም። ይልቁንም ሰላም በመከባበር ላይ የተመሠረተ እና በሰው ልጅ ትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ነው። በፍትህ እና በበጎ አድራጎት ላይ የተመሠረተ ሥርዓትን መመሥረት አስፈላጊ ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሰላምን እንደ ንቁ እና ጥረትን የሚጠይቅ ስጦታ ሲሉ ገልጸውታል። ባሕላችን ወይም ሃይማኖታችን ምንም ይሁን ምን እያንዳንዳችንን ያሳትፈናል፣ ይሞግተናል። ከሁሉ በፊት በራሳችን ላይ እንድንሠራ ይጠይቀናል። ሰላም በልብ ውስጥ የሚገነባ እና ከልብ ውስጥ የሚመነጭ በመሆኑ ትዕቢትን እና በቀልን በማስወገድ ቃላቶቻችንን በጥንቃቄ መምረጥ ያስፈልጋል። የጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ቃላትም ቢሆኑ ሊያቆስሉ አልፎ ተርፎም ሊገድሉ ይችላሉ።
ሰላማዊ እና የበለጸገ ማህበረሰብን መገንባት የሚቻለው ዕለት በዕለት በቁርጠኝነት በመነሳት እግዚአብሔር ያሰበውን ሥርዓት ወደነበረበት በመመለስ ሲሆን፥ ይህም እያንዳንዱ ሰው ሥርዓትን በማስተዋወቅ ሚናውን ሲያውቅ እና ሲወጣ ነው። ግጭት እና ሁከትን ለመከላከል ሁሉም የፖለቲካ ማኅበረሰብ ተሳትፎ እስከሚያደርግ ድረስ ሰላም በእያንዳንዱ ግለሰብ ልብ ውስጥ ሥር ሰድዶ በቤተሰብ እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ማኅበራት ዘንድ እንዲስፋፋ መደረግ አለበት። ፍትህን በማክበር በሚታወቅ አውድ ውስጥ ብቻ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል ትክክለኛ የሰላም ባሕል ማዳበር ይቻላል። በእርግጥ የግል ደኅንነት ካልተጠበቀ እና ሰዎች በነፃነት እና በመተማመን ውስጣዊ መንፈሳቸውን እና ችሎታቸውን እርስ በርስ እስካልተጋሩ ድረስ በምድር ላይ ሰላም ሊገኝ አይችልም።
ሰላምን መፍጠር ማለት ለውይይት እና ለእርቅ ሲባል ጥላቻን እና በቀልን መተውን ይጠይቃል። "ለጋራ ጥቅም መሥራት፣ ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሚበጀውን ሰላም ፈጣሪ መሆን አሁን ካለው በላይ አጣዳፊ ሆኖ አያውቅም። ቅድስት መንበር በሰላማዊ መንገድ እርስ በርስ የሚገናኙበትን ድልድይ የሚገነቡትን ታመሰግናቸዋለች። ድፍረት የተሞላበት ተግባራቸው ወደ ወንድማማችነት ለሚወስደው መንገድ ብርሃን ይሆናል። በዚህም ሁሉም በግንኙነት ባሕል ውስጥ ሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ተጠርተዋል።
ስለሆነም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከልዩነት ይልቅ ዲፕሎማሲውን በማስቀደም ሃብትን ለጦር መሣሪያ መግዣነት ከሚያውል ወደ ፍትህ፣ ውይይት፣ ድሆችን እና እጅግ የተቸገሩትን ወደ መርዳት ማዞር ይኖርበታል። ቅድስት መንበር ድህነትን እና ረሃብን ለማጥፋት፣ ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት እና የአየር ንብረት ለውጥን መቅረፍ እንዲቻል ከወታደራዊ ወጪዎች ተቀንሶ በጥቂቱ የሚደገፈውን ዓለም አቀፍ ፈንድ ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ሃሳብ አድሳለች። እነዚህ የማይታለፉ የዘላቂ ሰላም መሠረቶች ናቸው።
የጦር ትጥቅ ማስፈታት
ሰላምን ለማስፈን ከሚደረጉት የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች መካከል አንዱ መተማመንን መፍጠር ነው። አዲስ ማስፈራሪያን ስለሚፈጥር እና በሰዎች መካከል ስጋትን የሚያባብስ በመሆኑ ዳግም የጦር መሣሪያ ትጥቅ ይህን ግብ ያበላሸዋል። ትጥቅ እውነት እስካልፈታ ድረስ ሰላም ሊመጣ አይችልም። እያንዳንዱ ሕዝብ ራሱን እንዲከላከል የሚጠይቀውን መስፈርት ወደ ጦር መሣሪያ ትጥቅ ውድድር መቀየር የለበትም።
ትጥቅ ማስፈታት የፖለቲካ ወይም የስትራቴጂ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ የሞራል ግዴታ ነው። ይህም የሚገለጸው ለሰው ልጅ ሕይወት ቅድስና እና ለሰብዓዊ ቤተሰብ ትስስር እውቅናን በመስጠት ነው። በርካታ ሀገራት ለዓለም አቀፍ ትጥቅ ማስፈታት ስምምነቶች የገቡትን ቃል ማንሳታቸው እጅግ ያሳስባል። ቅድስት መንበር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የባለብዙ ወገን ትጥቅ የማስፈታት ስምምነቶች አስፈላጊነትን እንዳይዘነጋ፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ክምችትን ለመቀነስ መጣርን እና እንዲሁም መስፋፋትን የሚከልክሉ ዘዴዎችን በማጠናከር የጋራ ደኅንነት ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመታከት እንዲሠራ አስቸኳይ ጥሪ አቅርባለች።
ስለዚህ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች መስፋፋት፣ አጠቃላይ የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራ ክልከላ ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት የተደነገጉትን ሕጋዊ ሥርዓቶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርግ እና እንዲያጠናከር ቅድስት መንበር ትጠይቃለች።
በተጨማሪም የኒውክሌር ባለቤት የሆኑ ሀገራት የኒውክሌር ክምችቶቻቸውን ለመቀነስ፣ የጦር መሣሪያ ማከማቻዎቻቸውን ዘመናዊነት ለማስቆም እና በአገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር ግልፅ የሆነ ውይይት ለማድረግ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው። ከኒውክሌር ነፃ የሆነች ዓለምን የመገንባት የመጨረሻ ግብ ይዘን ሃብቶች ለትምህርት፣ ለጤና አጠባበቅ እና ለዘላቂ ልማት መዋል አለባቸው።
የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማምረት እና ማከማቸት ከሰላም ጋር የሚጋጭ ትልቅ ጥፋት ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅን ሁለንተናዊ ልማት ከማስፋፋት ይልቅ ጥፋትን የሚያስከትል በመሆኑ ነው። 1.5 ጊጋቶን ፈንጂ መሣሪያዎች ጋር በዓለማችን ውስጥ በድምሩ ከ12,000 በላይ ከባድ ሚሳይሎች እንዳሉ ይገመታል። ይህም በሂሮሺማ ከፈነዱ ከ100,000 በላይ ቦምቦች ጋር እኩል ነው።”