ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ 

አቡነ ጋላገር፥ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ ማንኛውም ዓይነት ጥቃቶች እንዲያቆሙ አሳሰቡ

በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ የቤጂንግ መግለጫ 30ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ብጹዕነታቸው በንግግራቸው፥ ጉልህ መሻሻሎች ቢኖሩም በሥራ ላይ ያለው አድልዎ፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሰናክሎች ከፍተኛ እንደሆኑ ተናግረው፥ መንግሥታት ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው፥ እንደ ውርጃ ያሉ የውሸት መፍትሄዎች ውድቅ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ “መንግሥታት የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ እና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ክብር ለማስጠበቅ የገቡትን ቃል መወጣት አለባቸው” ብለው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመስከረም ወር 1995 ዓ. ም. በቤጂንግ የተካሄደው አራተኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ 30ኛ ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ሰኞ መስከረም 12/2018 ዓ. ም. በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀ ከፍተኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ በቤጂንግ መግለጫ እና የድርጊት መድረክ ላይ የተጠቀሱ አንዳንድ ጉዳዮች ያልተፈቱ መሆናቸውን ገልጸው፥ ከፍተኛ የድህነት ቁጥር መኖሩን፣ ሴቶችን ጥራት ካለው የትምህርት ዕድል ማግለል እና ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያን ጨምሮ እነዚህ በሙሉ ሴቶች ክብራቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳያገኙ የሚያደርግ እና በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ያላቸውን አቅም እውን ለማድረግ የሚከለክሉ ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማንኛውም የጥቃት ዓይነት ተቀባይነት የለውም

“በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መበራከታቸው፣ ክብራቸውን የሚነኩ፣ በአገር ውስጥ፣ በግጭቶች ወይም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወቅት የሚደርስባቸው ከባድ ኢ-ፍትሃዊነት መበራከታቸው ቅድስት መንበርን እጅግ እንዳሳሰባት ገልጸው፥ “ይህ በደል በቴክኖሎጂው በኩልም እየተባባሰ የመጣ ቢሆንም፥ ነገር ግን በሴቶች ላይ የመፈጸም ጥቃት የቅድመ ወሊድ ጾታ ምርጫ እና የሴት ልጅ ግድያን ያካትታል” ብለዋል። “በቤጂንግ መግለጫ እና የድርጊት መድረክ ላይ የተወገዙ እነዚህ ድርጊቶች በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጃገረዶችን ለሞት መዳረጋቸውን ቀጥለዋል፤ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ መቆም አለበት” ብለዋል።

የጤና አጠባበቅ ዕርዳታ አለመመጣጠን

“ከአካላዊ ጥቃት በተጨማሪ ሴቶች አሁንም እኩል ያልሆነ የጤና እንክብካቤ ሰለባዎች ናቸው” ያሉት  ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ የተረጋገጠው የእናቶች ሞት መጠን መቀነስ በዚህ አካባቢ ካለው ጉልህ ዕድገት ጋር ሊመጣጠን አልቻለም’ ብለዋል። "የቅድመ ወሊድ እንክብካቤ እና ብቁ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የጤና ሥርዓቶች እና መሠረተ ልማት ተደራሽነት መጨመር አለበት” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር አጽንዖት ሰጥተዋል። “እንደ ፅንስ ማስወረድ ያሉ የውሸት መፍትሄዎች ውድቅ መደረግ አለባቸው” ብለው፥ ሌሎች መሠረታዊ መብቶችን የሚደግፍ በመሆኑ የሕይወት መብትን መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።     

በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ቤጂንግ የሴቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ ያነሷቸው ቁልፍ ጉዳዮች ችላ መባላቸውን አምነው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሴቶችን ለማይጠቅሙ ከፋፋይ ጉዳዮች ትኩረት እንደማይሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

 

23 Sep 2025, 17:06